Saturday, June 2, 2012

በግንቦት 20 የሚነሱ ያልተመለሱ ጥያቄዎች


ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ደርግን ከሥልጣን ያስወገደበትንና ሥልጣን የያዘበትን 21ኛ ዓመት በአንድ ላይ ነገ ያከብራል፡፡ ኢሕአዴግ ግንቦት ሃያን ባከበረ ቁጥር ‹‹የዘንድሮውን በዓል ለየት የሚያደርገው›› የሚል ቃላት በመጠቀም በዓሉን በጐ ከሚላቸው ሌሎች ክስተቶች ጋር ማያያዙ የተለመደ ነው፡፡ ነገ የሚከበረው የግንቦት ሃያ በዓልም የዓባይ ግድብ ግንባታ በተጀመረ ማግስት መከበሩ በዓሉን ለየት እንደሚያደርገው እየተገለጸ ነው፡፡

ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ አገሪቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚና የዴሞክራሲ ዕድገት እየስመዘገበች መሆኗን መንግሥት ሲገልጽ፣ ገለልተኛና ተቃዋሚ ወገኖች በበኩላቸው ግንቦት 20 ያልመለሳቸው በርካታ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎች መኖራቸውን ይገልጻሉ፡፡

በርካታ ችግሮች በሚታዩባትና በሚደመጡባት አንድ አገር ውስጥ አንድ ፓርቲ የሁሉንም ዜጐች ይሁንታ አግኝቶ ለሃያ አንድ ዓመት ማስተዳደር መቻሉ እንቆቅልሽ የሚሆንባቸው ታዛቢዎች፣ ኢሕአዴግ ለዚህን ያህል ጊዜ ሥልጣን ላይ የተቀመጠው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዳይካሄድ የመወዳደሪያውን ሜዳ ያጠበበው በመሆኑ ነው ብለው ያምናሉ፡፡

ደርግን ከሥልጣን በማስወገድ የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ያስጠበቀና የእኩልነት ጥያቄ መመለስ የቻለ መሆኑን የሚገልጸው ኢሕአዴግ በበኩሉ፣ በየጊዜው በሚካሄድ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሥልጣን መያዙን ይገልጻል፡፡ በተለይም ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ በአገሪቱ ውስጥ ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገቡን፣ በሒደትም ሕዝቡን ከድህነት አረንቋ እያወጣ መምጣቱን ገዢው ፓርቲ በልበ ሙሉነት ይገልጻል፡፡ በዴሞክራሲውም ረገድ መልካም አስተዳደርን በማስፈንና ሰብዓዊ መብትን በማስጠበቅ በርካታ ለውጦች እየተመዘገቡ መምጣታቸውን ይጠቅሳል፡፡

የኢሕአዴግን ሃያ አንድ የሥልጣን ዓመታት የሚገመገሙ የፖለቲካ ተንታኞች በበኩላቸው ገዢው ፓርቲ መሠረተ ልማትን በማስፋፋት ረገድ እየሠራቸው ያሉ ሥራዎች በበጐ መልኩ የሚገለጹ ቢሆንም፣ አብዛኛው ኅብረተሰብ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ተጠቃሚ አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡ የአገሪቱን የዴሞክራሲ ዕድገት ሲገመግሙም በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ የዜጐች መብቶች ቀስ በቀስ በአዋጆች፣ በመመርያዎችና በደንቦች እየተሸረሸሩ መምጣታቸውን ያስረዳሉ፡፡ ሙስናም የሥርዓቱ ዓይነተኛ መገለጫ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ሕወሓት/ኢሕአዴግ የትጥቅ ትግሉን ሲያካሂድ በነበረበት ወቅት ምን ዓይነት ዓላማዎችን አንግቦ ነበር? በ1983 ዓ.ም. ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ የትኞቹን የሕዝብ ጥያቄዎች ለመመለስ ቻለ? በዴሞክራሲ ግንባታ፣ በሰብዓዊ መብት አጠባበቅ፣ በመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መበትን በተመለከተ ድርጅቱ በረሃ ወቅት በነበረበትና ከሃያ ዓመት በኋላ የያዘው አቋም ምንድን ነው? የሚሉት ጉዳዮች አሁንም በበርካቶች ዘንድ መነጋገሪያ ናቸው፡፡

የሕወሓት የተምታታ አስተሳሰብ
ኢሕአዴግ አገሪቱን ባስተዳደረባቸው ባለፉት ሃያ አንድ ዓመታት በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ መብቶች አልተከበሩም፣ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እንዳይፈጠርም ገዢው ፓርቲ እንቅፋት ሆኗል የሚል እምነት ያላቸው ከሕወሓት አሥራ አንድ መሥራቾች አንዱ የሆኑት አቶ አስገደ ገብረ ሥላሴ፣ ችግሩን ሕወሓት ሲመሠረት ጀምሮ ከነበረው የተምታታ ርዕዮተ ዓለምና ከድርጅቱ የውስጥ ዴሞክራሲ ጋር ያያይዙታል፡፡

ሕወሓት ለትጥቅ ትግል ሲነሳ የትግራይ ሪፐብሊክን መገንባት የሚል የጠባብነት መንገድ መከተሉን የሚናገሩት አቶ አስገደ፣ በትጥቅ ትግሉ ወቅት በድርጅቱ የሚታዩትን ችግሮች በውስጥ ዴሞክራሲ የመፍታት ችግር እንደነበረም ያስታውሳሉ፡፡

‹‹ሕወሓት የተምታታ አስተሳሰብ ነበረው፤ በአንድ በኩል ማርክሲዝም ሌኒንዝም፣ ማኦኢዝም መመሪያችን ነው ይል ነበር፡፡ ቆየት ብሎ ደግሞ የማኦን አስተሳሰብ ተወና የስታሊንን አቋም ያዘ፡፡ የኮሙዩኒስት ሥርዓት ሲፈረካከስ ደግሞ ቀይ የኮሙዩኒስት ካባ ለብሰን ልንሄድ አንችልም አሁን የካፒታሊዝምን ካባ ለብሰን ቀስ በቀስ ዓላማችንን ማሳካት እንችላለን፤›› በማለት ሕወሓት በየጊዜው አቋሙን ይቀያይር እንደነበር የሚናገሩት እኚሁ አንጋፋው የሕወሓት ታጋይ፣ በወቅቱ የነበረው የሕወሓት አስተሳሰብ ከሕወሓት አስተሳሰብ ውጪ የነበሩ ኢሕአፓን የመሳሰሉ ኃይሎች ከትግራይ እንዲወጡ ያደረገ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በድርጅቱ ውስጥ ይነሱ የነበሩ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎችንም በውይይት ከመፍታት ይልቅ ሌላ ትርጉም በመስጠት በኃይል ይፈታ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት የትግራይ ሪፐብሊክን ለመመሥረት ለአሥራ አምስት ዓመታት ያህል ሲታገል የነበረው ሕወሓት ‹‹የብሔር ብሔረሰቦች የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል ድረስ፣ የዜጐች አጠቃላይ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይጠበቁ›› የሚሉ ዓላማዎችን አንግቦ ሲንቀሳቀስ የቆየ ቢሆንም፣ ማሌሊት በ1977 እስከተመሠረተበት ጊዜ ድረስ ‹‹የትግራይ ሪፐብሊካን መገንባት›› የሚለው አስተሳሰብ ስህተት ነበር የሚል ጉዳይ በኮንፈረንስም ሆነ በሕወሓት ልሳኖች ተነስቶ አያውቅም ነበር፡፡ ማሌሊት በተመሠረተበት ጊዜም ‹‹የጠባብነት ዝንባሌ ነበር›› ተብሎ ነው የታለፈው፡፡

በሽግግር መንግሥቱ ማግስት
በ1983 ዓ.ም. ደርግን የገረሰሰው ኢሕአዴግ ‹‹ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች የተሳተፉበት የሽግግር መንግሥት መሥርቻለሁ›› የሚለውን የገዢውን ፓርቲ ሐሳብ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ባይቀበሉትም፣ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት በ1987 ዓ.ም. ከፀደቀ በኋላ በተወሰነ ደረጃ ዜጐች ሕገ መንግሥቱ የሚፈቅድላቸውን መብት ማጣጣም ጀምረው እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ በወቅቱ የወጡትን አዋጆች መሠረት በማድረግም በርካታ የፕሬስ ውጤቶች ይታተሙ ነበር፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ፈቃድ ተሰጥቷቸው መንቀሳቀስ መጀመራቸው በበጐ ጐኑ የሚገለጽ ተግባር ነበር፡፡ የኢሕአዴግ ተፎካካሪ እንሆናለን ብለው የተመሠረቱት እነኚህ ፓርቲዎች ግን ብዙም ሳይቆዩ እየተጠናከሩ በመሄድ ፋንታ እየተዳከሙ መጡ፡፡

አቶ አስገደ እንደሚሉት ብዙኅን ፓርቲዎች እየተፈለፈሉ በሄዱ ቁጥር ስጋት ያደረበት ኢሕአዴግ በየክልሎቹ በኢሕአዴግ ሳንባ የሚተነፈሱ ፓርቲዎች መመሥረት ጀመረ፡፡ ለመአሕድ - ብአዴን፣ ለኦነግ - ኦሕዴድ የፈጠረው ኢሕአዴግ ተቀናቃኞቹን እያፈነ እንቅስቃሴያቸውን በማጥበብ ተቀባይነት እንዳያገኙ አደረጋቸው፡፡ ‹‹በጋዜጠኞች ላይ በሚመሠረት ክስና የእስር ቅጣት ምክንያትም ከስልሳና ከሰባ በላይ የነበሩ ጋዜጦች ቀስ በቀስ እየከሰሙ መጡ፤ የነፃ ፕሬስ ነፃነት ጠፋ፤ የሰብዓዊ መብት ጥበቃም ተጣሰ፤›› ይላሉ፡፡

የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ አስተሳሰብ ብቻ በኢትዮጵያ እንዲኖር በአሁኑ ጊዜ በገጠርና በከተማ አንድ ለአምስት የሚል አደረጃጀት ኢሕአዴግ እየተገበረ መሆኑን የሚናገሩት አቶ አስገደ፣ ግንቦት 20 ይዞት የመጣው ሙስና፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ብልሹ አስተዳደር ናቸው ብለው ያምናሉ፡፡

‹‹የትምህርት ነፃነት የሚባል ነገር የለም፡፡ አንድ አስተማሪ የሚለካው በሙያው ሳይሆን የሕወሓት/ኢሕአዴግ አባል በመሆኑ ነው፡፡ ግንቦት 20 ሲከበር የሕግ የበላይነት አልመጣም፡፡ የሕግ ባለሙያዎች የማይከበሩባት፣ ሕግ ተምረው ሌላ ሥልጠና እንዲወስዱ የሚደረጉባት አገር ናት፤›› የሚሉት አቶ አስገደ፣ አምስት ዓመት ተምሮ የወጣን አንድ የሕግ ምሁር በየክልሉ የሁለት ዓመት ሥልጠና በመስጠት የአንድ የፖለቲካ ድርጅት አስተሳሰብ እንዲጠመቅ በሚደረግበት ሁኔታ ፍትሕ ይኖራል ብሎ መገመት እንደሚያስቸግር ይናገራሉ፡፡ በኢኮኖሚ ረገድም ኑሮ ውድነት ከአቅም በላይ በመሆኑ በልቶ የሚያድር ሕዝብ በጣም አነስተኛ መሆኑን፣ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ የወጣው ባለሙያም ለእሱ የሚመጥን ፕሮጀክቶች ስላልተከፈቱለት ለሥራ አጥነት መዳረጉን ይገልጻሉ፡፡

በኢሕአዴግና በደርግ መካከል ያለው ልዩነት ሲገልጹም፣ ‹‹ደርግ በግልጽ ይገድላል፡፡ ኢሕአዴግ ግን በጣም አደገኛ ነው፡፡ በአየር ላይ ዴሞክራሲ አለ በማለት በቴሌቪዥን ሕዝቡን ያደነቁረዋል፡፡ ነገር ግን የፕሬስ ነፃነት ለይስሙላ ነው፣ የሰብዓዊ መብቶች መከበር ለይስሙላ ነው፣ ምርጫ ለይስሙላ ነው፤›› ይላሉ፡፡

የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፣ የኢሕአዴግ የ21 ዓመታት የሥልጣን ዘመን ያመጣቸውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ለውጦች በተለየ መልኩ ነው የሚቃኙት፡፡ ኢሕአዴግ በ1983 ደርግን ከሥልጣን ሲያስወግድ አገሪቱን በሥርዓቱ ተቀብሎ ለማስተዳደር የተዘጋጀ አካል ስላልነበረ እንደ አገር ፈርሳለች የሚል አመለካከት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሙሼ፣ አገሪቱ እንደተፈራው ሳትፈራርስ አነሰም በዛ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ወጥቶ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት መተግበሩ በበጐነት የሚገለጽ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ኢሕአዴግ በትጥቅ ትግል አሸንፎ እንጂ የሕዝብ ውክልና አግኝቶ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሥልጣን አለመያዙ በወቅቱ የነበረ አንዱ መሠረታዊ ችግር መሆኑን የገለጹት አቶ ሙሼ፣ እንደ ጐበዝ አለቃ የተጠራሩት የሽግግር መንግሥቱ አካላት ሕገ መንግሥቱን ሲቀርፁ የዜጐችን ቀጥተኛ ተሳትፎ ያላስገቡ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

‹‹በወቅቱ የተሻለ አቅም የነበረው ፓርቲ ኢሕአዴግ ነው፡፡ ለዚህም ነው የራሱን ፕሮግራም በሕገ መንግሥቱ እንዲካተት ያደረገው፡፡ የሌሎች ኃይሎች ውክልና አልነበረበትም፤›› ይላሉ፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት ሕገ መንግሥቱ የተዘጋጀው ራሱን መልሶ ለመፈተሽ በሚያስችል መንገድ አይደለም፡፡ በመሆኑም ባለፉት 20 ዓመታት ሲደረግ የነበረው ጥረት ሕገ መንግሥቱ የሚፈቅዳቸውን መብቶች ለማግኘት የሚደረግ እንጂ፣ በሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻሉ የሚፈለጉ ጉዳዮችን እንዲሻሻሉ የሚችሉበትን መንገድ ለማስተካከል አልነበረም፡፡

‹‹ሕገ መነግሥቱን ማሻሻል ይቅርና በሕገ መንግሥቱ ላይ የሰፈሩ ነገሮችን እንኳን መተርጐም አልተቻለም፡፡ በፖሊሲ፣ በመመርያና በደንብ ተቀፍድደዋል፤ የፕሬስ ሕግና የሽብርተኝነት ሕግ ለዚህ ዓይነተኛ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ኢሕአዴግ ዴሞክራሲን በመተግበር ረገድ ኋላቀርና ቁርጠኝነት የጐደለው ነው፤›› በማለት የኢሕአዴግን የሃያ አንድ ዓመታት ጉዞ ይገልጹታል፡፡

ሕዝብ የሚፈልገው የመልካም አስተዳደር ጥያቄም ኢሕአዴግ ከሚከተለው አብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ጋር እንደማይሄድ አቶ ሙሼ ይገልጻሉ፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ የአገር ጥቅምንና የብዙኅንን ጥቅም ለማስጠበቅ በሚል የመንግሥትን ጣልቃ ገብነት የሚያበረታታ ርዕዮተ ዓለም መሆኑን የሚናገሩት አቶ ሙሼ፣ ገዢው ፓርቲ በሕዝብ ጥቅምና በልማት ስም የዜጐችን መብት እንዲጥስ በር እንደተከፈለት ያስረዳሉ፡፡

‹‹ሰዎች ከልማት ውጪ ሌላ ነገር የላቸውም? ዳቦ ከመብላት ውጪ ብዙ ሊሟሉላቸው የሚፈልጉት ነገር አለ፡፡ የኢሕአዴግ አካሄድ የግለሰቦችን መብት የሚጥስና ወደ መንጠቅ የሚያመራ ነው፤›› ይላሉ፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች በመንግሥት ሚዲያ ቀርበው በሚፈልጉት አጀንዳ ላይ ሐሳባቸውን እንዳይገልጹ መደረጉም ሌላው ችግር መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ኢሕአዴግ ለራሱ ወቅታዊ ጉዳይ ሲል ተቃዋሚ ፓርቲዎች በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ውይይት እንዲሳተፉ ማድረጉ ለተቃዋሚዎች የሚዲያ ዕድልን ሰጥቷል ሊያስብለው እንደማይችል የሚናገሩት አቶ ሙሼ፣ ከሃያ አንድ ዓመት በኋላም ዴሞክራሲ በእንጭጭ ደረጃ የሚገኝ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ኢኮኖሚውስ አድጓል?
አቶ ሙሼ እንደሚሉት በኢኮኖሚው ረገድ በጐ የሚባሉ እንቅስቃሴዎች ታይተዋል፡፡ ገዢው ፓርቲ መሠረተ ልማትን በማስፋፋት ረገድ አመርቂ ሥራዎችን መሥራቱን የሚናገሩት የኢዴፓው ሊቀመንበር መንግሥት በመንገድ ግንባታ፣ በትምህርት፣ በቴሌኮሙኒኬሽንና በጤናው ዘርፍ እየሠራው ያለው ሥራ በበጐነቱ የሚጠቀስ ቢሆንም፣ የአንድ አገር ኢኮኖሚ በመሠረተ ልማት መስፋፋት ብቻ ሊገለጽ እንደማይቻል ያስረዳሉ፡፡

‹‹ይህች አገር ምርታማነቷን ልታረጋግጥ የምትችልበት ሁኔታ መኖር አለበት፤ አቅርቦት ዝቅተኛ ከሆነ ግሽበት ስለሚመታ በዚህ በኩል መንግሥት እየሠራ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ኢኮኖሚ ደረጃ ለማምጣት የአቅርቦት ኢኮኖሚው በውድድር ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል፤›› የሚሉት አቶ ሙሼ፣ በአሁኑ ጊዜ ሥልጣን ላይ ያለው ኢሕአዴግ በሚከተለው ሶሻሊስታዊ አመለካከቱ የሚፈልገውን ወገንና የኢኮኖሚ ሴክተር ለይቶ በማውጣት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉ የሚፈለገውን የኢኮኖሚ ዕድገት ሊያስገኝ አለመቻሉን ይገልጻሉ፡፡ መንግሥት ብዙ ድምፅ አለው ብሎ ለሚያስበው አርሶ አደሩና በአነስተኛና ጥቃቅን ዘርፍ ለተሰማራው የኅብረተሰብ ክፍል የሚሰጠው የተለየ ድጋፍ ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡

‹‹ተገቢ ያልሆነ ተፅዕኖ በማድረግ አንዱን ማኅበረሰብ ለመጥቀም ሌላኛውን ማኅበረሰብ መጐዳት የለበትም፤›› ሲሉ ኢሕአዴግን ይተቻሉ፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን ትችቶች ግን ኢሕአዴግ አይቀበላቸውም፡፡ ባለፈው ረቡዕ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ ያካሄድት የኢሕአዴግ የሕዝብና የውጭ ግንኙነት መምርያ ኃላፊ አቶ ሴኮቱሬ ጌታቸው፣ በትጥቅ ትግሉ የተሰው ሰማዕታት ኢሕአዴግ ባለፉት 21 ዓመታት የሠራቸውን ሥራዎች ቀና ብለው የማየት ዕድል ቢያገኙ ይደሰታሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ሴኮቱሬ ገለጻ፣ በአገሪቱ ዴሞክራሲ ሰፍኖ ዜጐች የፈለጉትን አስተሳሰብ በነፃ የማራመድ መበት ተረጋግጦ፣ የተለያዩ ጋዜጦች በየመንገዱ የሚነበቡበትና ሐሳቦች በነፃነት የሚንሸራሸሩበት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራጅተው አለን የሚሉት ሐሳብ በነፃነት የሚስተናገድበት ሥርዓት በመፈጠሩ ለነፃነት ሲታገሉ የተሰው ሰማዕታት የተገኘውን ለውጥ የማየት ዕድል ቢያገኙ ደስተኞች ይሆናሉ፡፡

ኢሕአዴግ ወደ አዲስ አበባ ሲገባ ሌሎች በትጥቅ ትግል ያሸነፉ የፖለቲካ ኃይሎች እንደሚያደርጉት እኔ አሸናፊ ነኝ በማለት ሥልጣን ለብቻው ከመያዝ ይልቅ፣ የፖለቲካ ኃይሎችን አሰባስቦ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ማድረጉ ሊደርስ የሚችለውን ችግር ማስቀረቱን የሚገልጹት አቶ ሴኮቱሬ፣ ባለፉት ሃያ አንድ ዓመታት የተካሄዱት አገሪቱን ከድህነት የማውጣት፣ የሰብዓዊ መብቶችና የዴሞክራሲያዊ መብቶችን ለማጠናከር የወተሰዱ የፖሊሲ ዕርምጃዎች ነገሮች ቀስ በቀስ እንዲለወጡ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ እርሳቸውም እንደ አቶ አስገደ ሁሉ ሕወሓት/ኢሕአዴግ የተምታታ አስተሳሰብ የነበረው መሆኑን አልደበቁም፡፡ ‹‹[1983 ዓ.ም.] ዘመኑ ኮሙዩኒዝም እየወደቀ ካፒታሊዝም እየገነነ የመጣበት ወቅት ነበር፡፡ ከዚህም በላይ ካፒታሊዝም ብቸኛ አማራጭ ተደርጐ የሚወሰድበት ዘመን ነበር፡፡ የእኛ አመጣጥ ከኮሙዩኒዝም ሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም በመሆኑ፣ ይህን የሚከተሉ በውስጣችን የነበሩበትና ከዚህም አልፎ አደረጃጀት የነበረበት ሁኔታ ነበር የነበረው፡፡ በዚህም የተነሳ የአስተሳሰብ ጥራት ላይ ችግር ነበረብን፤›› ብለዋል፡፡

ኢሕአዴግ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ፣ አገሪቱ በፈጣን የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሒደት ውስጥ ብትገኝም ድህነትና ኋላቀርነት፣ የኑሮ ውድነት፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚታየው በአቋራጭ የመክበር አስተሳሰብና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሥርዓቱን የሚፈታተኑ ፈተናዎች መሆኑን አምኗል፡፡ እነዚህ ችግሮች ዘላቂ ልማትና መልካም አስተዳደር በማስፈን እንደሚፈቱ ፅኑ እምነት እንዳለው የገለጸው ኢሕአዴግ፣ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ ርብርብ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

ኢሕአዴግ የፖለቲካ ሥነ ምኅዳሩን በማጥበብና የተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅቶችን እንቅስቃሴ በማወክ ይተቻል፡፡ ተቃውሞ ማሰማት ወንጀል እየሆነ ነው የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢሕአዴግ ሰላማዊ ትግሉን እየኮላሸው ነው ይላሉ፡፡ ኢሕአዴግ ደግሞ ሕገ መንግሥቱን አክብረው የሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ያላቸውን አማራጭ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለማስተዋወቅ የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚደግፍ በዚሁ መግለጫው አስታውቋል፡፡ በጋራ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አማካይነት የተጀመረውን ምክክር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል፡፡

የኢሕአዴግ ያለፉት 21 ዓመታት የሥልጣን ቆይታ በርካታ ውጣ ውረዶች የታዩበት ሲሆን፣ ኢሕአዴግ እየተፈተነ ያለው ልማትን በማምጣት ብቻ ሳይሆን ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብትን ማስከበር ባለመቻሉ ነው እየተባለም ነው፡፡ የሕዝቡን የመልካም አስተዳደር ጥማት ለማርካት ብዙ መሥራት ይጠበቅብኛል ብሎ ቃል ቢገባም፣ ከዚህ በፊት የገባኸውን ቃል አላከበርክም ብለው የሚወቅሱት በርካቶች ናቸው፡፡ ኢሕአዴግ ሃያ አንደኛ ዓመት የሥልጣን በዓሉን ሲያከብር ያልተመለሱ በርካታ ጥያቄዎችን እያሰበ መሆን አለበት የሚሉም እንዲሁ ይበዛሉ፡፡   
 
  Source: Ethiopian reporter

No comments:

Post a Comment