Friday, August 24, 2012

የሰሜን ኮርያው ሞዴል??


በቅሎ እጸዳዳለሁ ብላ ሃፍረቷን አሳየች !!

ከብስራት ኢብሳ
በተፈጥሮዬ ለሁለት ነገር አልታደልኩም ፡፡ የመጀመርያው ፣ በንግግር ሃሳቤን መግለጽና ፣ ሁለተኛው ድምጽ እያሰሙ የእውነትም ሆነ የውሸት ማልቀስ አልችልም ፡፡ ጨካኝ ሰው ነኝ ብዬ እንዳልደመድም ፣ አንዳንዴ አሳዛኝ መጽሃፍም ሆነ ፊልም ሳይ እንባዬ ይቀራል ፡፡ አንዳንዴም ሕዝብ የአንባ ገነን ገዢዎቻቸውን ታግለው አሸንፈው ፣ በደስታ ሲፈነጥዙ ሳይ ፣ እኔም ስለሃገሬ መንፈሳዊ ቅናት ያድርብኝና ፣ ድንገት ስሜታዊ ሆኜ ፣ ሲቃ ይዞኝ ፣እንባዬ ዱብ ዱብ የሚልበት ወቅት ስላለ ጨካኝ ነኝ ለማለት ይቸግረኛል፡፡ ሟች የቅርብ ዘመዴም ቢሆን ፣ የሆነ የሚያስተሳስረን ፣ ወይ አብረን ያሳለፍነው የማስታውሰው ነገር ከሌለ ፣ ስሜቴ ላይ ለውጥ አያመጣም፡፡ እንደ ፊልሙና ፣ መጽሃፉ ከሆነ ስሜት ጋር ሲያያዝ ብቻ እንጂ ፣ በተለይ ጮክ ብዬ ላልቅስ ብዬ እራሴን ባስገደድኩኝ ቁጥር ፣ የኮረኮሩት ያህል ነው ሳቄን የሚያመጣው ፡፡
በጎልማሳ ዘመኔ አንድ የቅርብ ዘመዴ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተው ለቅሶዋቸውን ሳልሰማ ስለሰነበትኩኝ እናቴ ለሰልስቱ አብሬያት እንድሄድ ትጠይቀኛለች ፡፡ እኔም ጮሆ ማልቀስ ስለማልችል ይቅርብኝ እላታላሁ ፡፡ እናቴም ነገሩን ቀለል አድርጋ ፣ `` ችግር የለውም ፣ ግቢው ውስጥ ስንገባ ፣ እኔ እጀምርልሃለሁኝ ፣ ከዛ አብረን እናለቅሳለን `` ትለኛለች ፡፡ ችግሬን ለማሳመን ብዙ ከሞከርኩኝ ቦኋላ ስላልተሳካልኝ ፣ ``መሄዱን እሺ ግን አላለቅስም `` አልኳት ፡፡ እናቴ ልታስለቅሰኝ ቆርጣ ስለተነሳች ፣ ``ልጄ ዘመድህ ሞቶ ፣ ያውም በጉራጌ ባህል ፣ ኡ ኡ ኡ ብለህ ካልገባህ ፣ የመርካቶ ዘመዶቻችን ቀርቶ ሳር ቅጠሉ ይታዘበናል .`` .ብላ ስላስቸገረችኝ፣ ``እንሂድ የሚሆነውን እናያለን`` ፣ ብያት ታክሲ ተሳፈርን ፡፡
እንደፈራሁኝ ከታክሲ ወርደን ወደ ድንኳኑ ስንገባ ፣ እናቴ በል በርታ ብላ ለቅሶዋን ጀመረችልኝ ፡፡ እናቴን ማሳፈር አልፈለኩም ፣ ማልቀሱም አልሆነልኝም፣ በመጨረሻ በዚህ ጭንቀት መሃል ፣ ያበጠ ይፈንዳ ብዬ ፣ ጮኬ ማልቀስ ስጀምር ፣ ፍራሽ ላይ ተሰብስበው የተቀመጡት ፣ የሟች ልጆችና ፣ ሌሎች የዘመድ ልጆች መሳቅ ይጀምራሉ ፡፡ ምክንያቱም ጮኬ ማልቀስ ስጀምር ፣ ድምጼ በሚያስገርም ሁኔታ ፣ አንዴ እንደ በሬ ፣ ሌላ ጊዜ እንደ ድመት .... የማይሆን አይነት ያልተለመደ ድምጽ ይወጣኝ ስለነበር ፣ የመርካቶ አራዶች ዘመዶቼ ፣ ቲያትር መሆኑ ገብቷቸው ኖርዋል ፣ አንደኛዋ ሴት ልጃቸው ፣ ስሜን ጠርታ ፣ `` ና እባክህ እኛ ዘንድ ተቀምጠህ ተጫወት ፣ ይቺ አባዬ ናት አልቅስ ብላ የምታስቸግርህ`` ብላ ጠራችኝ ፡፡ 


እኔም እንዳልተሳካልኝ ስለገባኝ ፣ ጩኅቴን አቁሜ `` ተይ ይቅርብኝ ብያት ነበር አልሰማ አለችኝ `` ስላቸው እናቴ ሰምታ ፣ ``ይሄ ሞኝ ፣ ደግሞ አፍ አለኝ ብሎ ይናገራል ብላ ፣`` ለቅሶዋን ትታ ፣ ቀና ብላ አይታኝ ፣ ገረምኳት መሰለኝ እሷም ሳቅዋን ጀምራ ፣ ድንኳን ውስጥ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉት በሙሉ ፣ ሳቅ በሳቅ ሆኑ ፡፡ በታክሲ ወደቤታችን ስንመለስ ፣ ወቀሳዋን ከመጀመሯ በፊት ፣ ቀደም ብዬ እራሴን ለመከላከል `` ሰውን ማጽናናት ማለት እውነቱን ተናግሮ ማሳቅ እንጂ ፣ የውሸት አልቅሶ የእውነት ማሳዘን አይደለም`` ብያት ፣ ከዚህ ጊዜ ቦኋላ ፣ እንኳን አልቅስ ብላ ልታስቸግረኝ ፣ የተገላቢጦሽ ፣ `` እሱ ይጨነቃል ለቅሶ አትንገሩት`` እያለች ትከላከልልኝ ነበር ፡፡
በዚህ ድክመቴ የተነሳ ፣ ምናልባት የሚያለቅሱ ሰዎችን ልምድ ብጠይቅ ፣ የተሻለ ያለቃቀስ ዘዴ እማር ይሆናል በሚል ፣ ማልቀስ የሚችሉ ሰዎችን ፣ እንዴት ማልቀስ እንደሚሆንላቸው መጠየቅና ፣ መረዳት አለብኝ ብዬ ወሰንኩኝ ፡፡ መጀመርያ የጠየኩት ፣ የቅርብ ጓደኝዬን ነበር ፡፡ አንዴ የቤተሰቦቼን ደህንነት ለመስማት ወደ ሃገር ቤት ስልክ ደውዬ ፣ አንድ የማላውቀው ዘመዴ ሞቶ በሙሉ ለቅሶ ሄደዋል ብለው ቤት ጠባቂዎች ነግረውኝ ፣ ሳላገኛቸው ቀረሁ ብዬ ለስደት ጓደኛዬ ደውዬ እነግረዋለሁኝ፡፡
ጓደኛዬም ግማሽ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ቤቴ ለቅሶ ሊደርስ መጥቶ ፣ እንባውን እንደጎርፍ ያፈሰው ጀመር ፣ ተደናግጬ እኔው አጽናኚ ሆንኩኝ ፡፡ ለቅሶ የተቀመጥኩኝ መስሎት ወደየሰው ስልክ እንዳይደውል ስለሰጋሁኝ ፣ በስልክ ስነግረው ፣ እግረ መንገዴን አነሳሁት እንጂ አዝኜ ወይም ለቅሶ ለመቀመጥ ፈልጌ እንዳልሆነ አስረግጬ ላስረዳው ሞከርኩኝ ፡፡ ማልቀሱ ትንሽ ይቀንስ እንጂ አልፎ አልፎ መንሰቅሰቁን አላቆመም ፡፡ እኔም ባኮ ሙሉ የወረቀት መሃረብ ፊቱ ከምሬ ፣ አንዱ ሲረጥብ ሌላውን አቀብለው ጀመር፡፡
ታዲያ እንደምንም አረጋግቼው ፣ እህል ወሃ ከቀማመስን ቦኋላ ፣ በጨዋታ መሃል በማልቀስ እንዴት የታደለ እንደሆነና ፣ እኔንም እንዲያስተምረኝ እጠይቀዋለሁኝ፡፡ እሱም ቀለል አድርጎ ፣ `` እኔ እኮ ለቅሶ ስሄድ የማለቅሰው ፣ የራሴን የሞቱብኝን ሰዎች እያስታወስኩኝ እንጂ ፣ አብደሃል እንዴ ፣ አንተ እራስህ ለማታውቃቸው ዘመድህ እኔ የማለቅሰው `` ብሎ እውነቱ ነገረኝ ፡፡ አንዳንዴ በደብዳቤ ለሚያረዱት ዘመዶቹ ፣ በደንብ የሚያለቅሰው በዚህ አጋጣሚ መሆኑን አልደበቀኝም ፡፡
መልሱ በጣም ስለገረመኝ ፣ ``ታዲያ ዛሬ ለየትኛው ዘመድህ ነው ዛሬ ያለቀስከው ? እውነቱን ንገረኝ`` አልኩት ፡፡ ቆፍጠን ብሎ ፣ ``ዛሬ ያለቀስኩት ለኔና ላንተ ነው `` ብሎኝ አረፈ ፡፡ ጆሮዬን ስላላመንኩት ፣ `` ሙተናል እንዴ ?`` ብዬ ስጠይቀው ፣ እጁን በእጁ እያሻሸ ፣ እንደመሳቅም ፣ እንደ መሽኮርመምም አድርጎት ፣ ከኪሱ ከአንድ ቀን በፊት ፣ ከዘመዶቹ ፣ እናቱ በጠና ስለታመሙ ፣`` ብር ባስቸኳይ ለህክምና ላክ ፣ ይህንን ሳታደርግ እናትህ ብትሞና ብታለቅስ ዋጋ የለውም`` ብለው የጻፉለት ደብዳቤ ነበር፡፡ ``ታዲያ እኔ እናትህ ነኝ ወይ ?`` ብዬ ጠይቄው ፣ ``ጠዋት በስልክ ስለ ዘመድህ ስትነግረኝ ፣ የኔንም ደብዳቤ አንብበህ እንደምትቸገርልኝ ስለማውቅ ፣ በሃዘንህ ላይ ሌላ ችግር ስፈጥርብህ አሳዝነኅኝ ነው ያለቀስኩት ፡፡ ለራሴ ደግሞ የማለቅሰው ፣ እናቴ ዘጠኝ ወር በሆድዋ ተሸክማ ፣ አብልታ ፤ አጠጥታኝ ፣ ለፍታ አሳድጋ ለወግ ማዕረግ አድርሳኝ ፣ በዚህ አስችጋሪ በመጨረሻ ጊዜዋ ፣ እናቴን ልረዳ የማልችል ምስኪን ፍጡር በመሆኔ ፣ ሳዝን ሁሌ አለቅሳለሁ ፡፡`` ብሎኝ ፣ እንደገና የውሸት አልቅሶ ፣ እግረ መንገዱን ፣ ከለቅሶው ጀርባ የሚፈልገውን መልዕክት አስተላልፎ ፣ የውነት አሳዝኖኝ ሊያስለቅሰኝ ነበር ፡፡
በሃገራችንም ይሁን በዓለም ፣ ለቅሶ በተለያየ ባህላዊ መልክ ይገለጻል ፡፡ ሰው ሲያለቅስ ሁልጊዜ ለሃዘን ብቻ አይደለም ፡፡ ሳቅ ሲበዛ ያስለቅሳል ፡፡ ደስታ ያስለቅሳል ፡፡ ፍርሃት ያስለቅሳል ፡፡ ሕጻናት አንዳንዴ ሲዋሹ ያለቅሳሉ ፡፡ እርካታ ያስለቅሳል ፡፡ ህመም ያስለቅሳል ፡፡ ማቸነፍ ፣ መቸነፍ ሁሉ ያስለቅሳል ፡፡ እንዲህ እያልን ብዙ አስለቃሽ ነገሮች ማሰብ እንችላለን ፡፡
በሃገራችን ለቅሶ ይከበራል፡፡ ለቀስተኛ ፣ እሬሳ ይዘው ወደ ቀብር ሲሄዱ ፣ የሞተውን ባናቀውም ፣ ወሬያችንን አቁመን ፣ እጃችንን ለክብሩ ወደ ኋላ አድርገን እንደ እምነታችን እናማትባለን ፡፡ ዝቅ ብለን እጅ እንነሳለን ፡፡ የሞተው ጠላት እንኳን ቢሆን ፣ ንፍሮውንና ቡናውን አንቀምስም እንጂ ፣ ለቅሶ ይደረሳል፡፡
ወደ መጨረሻው ቤቱ ስለሄደ ጠላትም ቢሆን ፣``ነብስ ይማር`` ተብሎ አፈር ጉድጓድ ውስጥ ይበተናል ፣ ሌላም ሌላም ብዙ የምንኮራባቸው የራሳችን ባህሎች አሉን ፡፡ በሃገራችን ብዙ ሰዎች በተፈጥሮዋቸው ሩህሩህ ከመሆናቸው በላይ ፣ ለማንም ለማያቁት ሰው ለቅሶ መድረስ የተለመደ ነው ፡፡ ሲሞት ያለቅሳሉ ፡፡ ሟቹን ሳያውቁት ደርት እየመቱ ያዙኝ ልቀቁኝ ብለው ሲወድቁ ፣ እራሳቸውን ሲጎዱ ቆይተው ፣ የሟችን ስም የሚጠይቁ ፣ ወንድ ይሁን ሴት ? በአደጋ
ይሁን በተፈጥሮ እንዴት እንደሞተ ለማጣራት የሚሞክሩ ብዙ ሰዎች እንዳሉ ይታወቃል ፡፡ ሞት ሁሉም ቤት በተራ ስለሚደርስ ፣ የቋሚውን ሃዘን ነው የምንካፈለው ፡፡
በሃገራችን ሰው ሲሞት ብዙ አይነት ያለቃቀስ አይነቶች አሉ ፡፡ ከጉራጌ ``ዓለም ገፈረም በዋሻ`` (ዓለምን ትቶ ዋሻ ውስጥ መኖር መረጠ)፣ የዳንስ አይነት ውዝዋዜ ፣ እስከ የዶርዜ የዝላይ የመገለባበጥ ትዕይንት፣ ጸጉር ከመንጨት ፣እስከ ሰውነትን ማድማት የመሳሰሉት ሁሉ አይነት ፣ ሃዘንን የመግለጫ መንገዶች አሉ ፡፡ ለእንደኔ አይነት ማልቀስ ለማይችል ፣ ልበ ደረቅም አማራጭ ፈጥረውለት አስለቃሽ፣ አስረጋጅ ፣ አስተዛዛኝ፣ ማማረጥ ይቻላል እንደውም እዚህ የሰለጠነ ዓለም ፣ ለብዙ ዓመታት ማልቀስ ወይም መሳቅ ለተቸገሩ ሰዎች የሚሰጥ ኮርስ (ቴራፒ) እንዳለ ሰምቻለሁኝ ፡፡ እነዚህ የሃገራችንን አስለቃሾችን ጠጋ ብላችሁ አይናቸውን ብታዩት ፣ ግጥም እየደረደሩ ያን ሁሉ ሕዝብ በእንባ ሲያራጩት ከዓይናቸው አንዲት ጠብታ እንባ አትወጣም ፡፡ ለእነሱ እንደ ሙያ እንጂ ፣ ስሜት የሚለውን ነገር ከውስጣቸው አውጥተውታል ፡፡ ስለዚህ የውሸት እያለቀሱ የውነት የሚያስለቅሱት እንጀራቸው ስለሆነ ነው ፣ ያን ካላደረጉ ነገ የሚቀምሱት የላቸውም፡፡
ዛሬ ለቅሶ እንደ ድሮ ፣ በፈረስ ፣ በባቡር ፣ በግር እየተሄደ የሚደረሰው ያው ሃገራችን እንጂ ፣ በተለይ ቴክኒዎሎጂው በሰለጠነበት ዘመን ብዙ መጓዝ እየቀረ ነው ፡፡ በስልክ መላቀስ ፣ በሞባይልና በትዊተር መርዶ ማርዳት ፣ በእስካይፒ እና በፓልቶክ ለቅሶ መድረስ ....እይተለመደ ነው ፡፡ ለቅሶ ፣ተዝካር ፣ የሃውልት ምራቃት .....ወዘተ አንድ ሰው ካልተመቸው ፣ ወይም ያለበት ቦታ እንዲያዝን ፣ እንደ ሰርግ ፣ በፊዲዮ ተቀርጾ ይላካል፡፡የሕዝቡ ብዛት ፣ የምግቡ አይነት ፣ የታረደው የሰንጋ ብዛት ፣ ይስጋው ጮማነት ..ሁሉ እየተደነቀ ወደ ድግስነት እየተጠጋ ነው ፡፡
ለቅሶ በምዕራቡ ዓለምና በምስራቁ ዓለም የሚጫወተው ራሱን የቻለ ፖለቲካዊ ገጽታ አለው ፡፡ በተለይ የኮሚኒስቱ ሃገር መሪዎች ፣ ምዕራቡ በአንባ ገነንነት የሚከሷቸውን ስሞታ መሰረት ለማሳጣት ፣ ለመሪዎቻቸው ቀብር በሚወጣው ሕዝብ ብዛት ፣ ለሕዝባቸው ተወዳጅ እንደነበሩ ለማሳየት ፣ ለቀብር የሚያሰልፉት ትዕይንተ ሕዝብ ፣ ብቻ ሳይሆን ፣ ትዕይንተ ለቅሶ ፣ ከማስገረም አልፎ ያስፈራል ፡፡
በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ፣ እንደ አንድ ቤተሰብ ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ ፣ ካሜራው ቀረብ ሲልና ፣ ሲርቅ ፣ የለቀስተኛው ድምጽ የሚጨምርና ፣ የሚቀንስ ከሆነ ? ተአሚነቱን ይቀንሰዋል ፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ የኅብር ለቅሶ ያየሁት በ1976 በሊቀመንበር የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ሲሆን ፣ የመጨረሻውን ያየሁት ፣ ከዓመት በፊት የሰሜን ኮርያውን የኪም ዮንግ ሁለተኛውን ነው ፡፡
የሁለቱንም ቀብር ይህንን ጽሁፍ ላዘጋጅ ስል ፣ ጉግል ላያና ፣ ዊኪ ፒዲያ ውስጥ ገብቼ ከነ ምስሉ ስመለከት ፣ አንድ በደንብ የገባኝ ነገር ፣ ያ ሁሉ ሚሊዮን ሕዝብ የሚያለቅሰው ልዩ ጥቅም ተሰጥቶት ወይም ተገዶ ሳይሆን ፣ ለመሪው እንዲያለቅስ አሳምነውት ነው፡፡ በስሜት ተነሳስቶ ፣ ከውስጥ በተቀሰቀሰ ስሜት ማልቀስና፣ እንዲያለቅስ አሳምነውት ማልቀስ ይለያያል ፡፡
በእርግጥ በዛ ሥራዓት የተጠቀመ ፣ ከመንገድ አንስተውት የሾሙት ፣ ህልውናው ከዛ ሥርዓት ጋር የተያያዘ ፣ ያለአግባብ የበለጸገ ፣ ለሰራው ወንጀል ፍርሃት ያለበት ለሚቀጥለው የስልጣን ሽግሽግ ጎልቶ ለመታየት የሚፈልግ ፣ ብዙ ብዙ ከኋላ የተደበቁ አጀንዳዎች ከለቅሶው ጀርባ አሉ ፡፡
በእንደዚህ አይነት የኮሚኒስት ሃገር ፣ መሪው ያንን ሃገር ሊያስተዳድር ከአንድ ትልቅ ሊታይ ሊዳሰስ የማይችል ሃይል ተመርጦ እንደሆነ አድርገው እንዲያምኑ ፣ ለአመታት አዕምሮዋቸውን በማጠብ በውስጣቸው የተገነባ ዕምነት ነው ፡፡ ይህ መሪ አልፎ አልፎ በአደባባይ በሚያሳየው ጠንካራ የጦር ሰራዊቱንና ፣ ዘመናዊ ያጦር መድፎቹን ፣ ሃያ አራት ስዓት ሙሉ ፣ ብቸኛ ከሆነው አንድ ቴሌቪዥና የራርዲዮ መስመር ፣ሕዝባቸውን ታላቁ መሪያቸው እንዴት ከኢንፔርያሊስቶች እንደጠበቋቸው ....በመሳሰሉት፣ ፕሮፓጋንዳ እንዲያምኑ የተደረጉ ፍጥረቶች ናቸው ፡፡
በዚህም ላይ ጠንከራ የስለላ መረብ የእያንዳንዱን ቤት የሚሰልል እንዳለ ስለሚያውቁና ፣ አንዳንዴ የራሳቸውን ህሊና ተጠቅመው ፣ የፓርቲውን መስመር የማይከተሉ ``እንቢተኞች`` ፣ ሕዝብ በተሰበሰበበት ፣ በአደባባይ አንገታቸውን ስለሚቆረጡ ፣ እያንዳንዱ የሃገሪቷ ነዋሪ ፣ እኔም ከዚህ መስመር ብወጣ ፣ ይሄ ይደርስብኛል ብሎ ፈርቶ አንገቱን ደፍቶ ፣ የእውነት ለቅሶ ተምሮ ፣ ህይወቱን ለማሰንበት ያለቅሳል ፡፡
እንደዚህ አይነት ሕብረተሰብ ፣ አለቃቸው ፣ ካሁን ቦኋላ መኖር አያስፈልጋችሁም ፣ እራሳችሁን በመርዝ ግደሉ ፣ በስለት ቆራርጡ ፣ ከገደል ዘላችሁ ሙቱ ፣ ብሎ ቢነግራቸው፣ የታዘዙትን ያደርጋሉ፡፡ ለዚህም የነ ጂም ጆንስ አሳዛኝ
የእልቂት ታሪክ በሳባዎቹ ዓመታትና ፣ በተለያዩ ሃገራት የተደረጉትን ፣ አሰቃቂ ታሪኮች መለስ ብሎ ማስታወሱ ጠቃሚ ነው፡፡
ይህ የሰሜን ኮርያ ሞዴል፣ እንደ ግል ማሰብ ፣ መመዘን ፣ መቃወም ......አይነት ተፈጥሮ የቸረን ስጦታ ተደምስሶ፣ በመሪዎች ጭንቅላትና በፓርቲ መስመር እንደ ሴክት እንድናስብ እዕምሮን ማጠብ የበሽታ አዝማምያ ወደ ሃገራችንም እየቀረበ ስለሆነ ፣ካሁኑ ይህንን አስፈሪና ፣ አደገኛ አዝማሚያ ሳይቃጠል በቅጠል ልንለው ይገባል ፡፡
በቅርቡ በአቡነ ጳውሎስ እና በጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ምክንያት ፣ በአንድ በኩል ከላይ ከጠቀስኩት ባህላችን ውጪ ፣ ለሞተ ሰው ሊሰጥ የሚገባውን ተዘንግቶ፣ ከመስመር ውጪ ተኪዶ አላስፈላጊ ሊያስገምቱን የሚችሉ ቃላቶች መጠቀምና፣ አላስፈላጊ ድርጊቶች መፈጸም ቀርቶ ፣ በሌላውም አንጻርም ፣ ማንም ሰው ያለ ማዘን መብት እንዳለው ዘንግተው ፣ እኛ ስናለቅስ እናንተ ለምን ደረት አልመታችሁም ፣ ብለው ፣ የሰሜን ኮርያን አይነት ሞዴል፣ በአፍሪካ እንደ የጎጡ ፖለቲካ ሊጭኑብን ለሚሹት ነቅተን ልናሳፍራቸው ይገባል፡፡
ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይጠብቃታል !! 

ብስራት ኢብሳ
23-08-12 

No comments:

Post a Comment