Wednesday, September 19, 2012

በየመን ሁለት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ታሰሩ፣ ቤቴ ሌሊቱን ሲፈተሽ አደረ



(በግሩም ተ/ሀይማኖት)
ሀበሻ በየመን
Girum Teklehaimanot
   ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የአትሌቲክስ ፊዴሬሽን ችግር ምክንያት በርካታ አትሌቶቸ በየሀገሩ መሰደዳቸው የሚታወቅ ነው፡፡ አትሌት ከበደ ይልማ ከእነዚህ አትሌቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ የመን በከፍተኛ ችግር ውስጥ ስለገባ መርዳት አለመቻሌ በቁጭት ያርመጠምጠኛል፡፡ ትሬኒንግ ሰርቶ የሚበላው ከማጣት ጀምሮ ብዙ ስቃይ ስለደረሰበት በቪዲዮ የተደገፈ ቃለ-ምልልስ አድርጌለት ለተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ለመበተን አቀድኩ፡፡ የሚረዳው ወገና ካለ እንዲረዳው እና ከልምምድ እንዳይርቅ ለማድረግ ማለት ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ምን አቅም አለኝ? በዚሁ ጉዳይ ተነጋግረን ሌላ ጓደኛውን ይዞ ቅዳሜ ጳጉሜ 3 ቀን የምሰራበት ሱቅ መጡ፡፡ እዛ ቃለ-ምልልስ ለማድረግ አላመቺ በመሆኑ ስራዬን ስጨርስ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ወደ መኖሪያ ቤቴ ይዣቸው ሄድኩ፡፡
     በእርግጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ ክትትል እየተደረገብኝ እንዳለ አውቃለሁ፡፡ ግን ገፍቶ እንዲህ ይመጣል ብዬ አላሰብኩም፡፡ ወይም ከእኔ ተርፎ ከእኔ ጋር ለሚገናኙ ሁሉ ጦስ ይሆናል ብዬ አልገመትኩም እና ስህተት ሰራሁ፡፡ ወደ ቤቴ ከገባን ጊዜ ጀምሮ ዘና ብለን ቃለ ምልልሱን ሰራን፡፡ በዚህ መሀል በሀገሪቱ ውስጥ ካለው ችግር አንጻር መብራት ስለሚጠፋ የጠፋው መብራት እስኪመጣ መጠበቅ ግድ ነበረና የቆየውን ያህል ቆይተው ጨረስን፡፡ ክትትል እያደረገብኝ ያስቸገረኝ ሲበል ለባሽ ፖሊስ ሁለቱ ካለሁበት ፎቅ ላይ ሲወርዱ ስልክ እየደዋወለ ተከታተላቸው እና በግምት 75 ሜትር ርቀት ላይ ለቆሙ ፖሊሶች አስያዛቸው፡፡ በዚህን ሰዓት የሰማሁት ነገር የለም፡፡ ሀገር ሰላም ብዬ የቀረጽኩትን ቪዲዮ ድምጽ ቼክ አደርጋለሁ፡፡
    ይህ የሆነው ረቡዕ ጳጉሜ ሶስት ቀን ነው፡፡ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ጀምሮ ያለሁበት ጊቢው በር በሀይለኛው ይደበደብ ጀመር፡፡ የቤቱ ባለቤት ትውልደ ኢትዮጵያዊው ፎዚ ‹‹ሳዕዱኒ..›› /እርዱኝ/ እያለ ጩኸቱን ሲያስተጋባ መስኮቴን ከፍቼ ወደ ውጭ ማየት ጀመርኩ፡፡ ብወርድስ ምን መርዳት እችላለሁ? አልኩና ስራዬን ቀጠልኩ፡፡ ግን ሁለት የፖሊስ መኪና መቆሙን አየሁ፡፡ ፈጽሞ እኔን ፍለጋ ይሆናል ብዬ አልጠበኩም፡፡ ምን ሰርቼ ይፈልጉኛል ብዬ ላስብ? መያዝ ቢፈልጉ የትኛውም ቦታ መያዝ ይችላሉ፡፡ በዚህ ሰዓት ሌሊት ይመጣሉ ብሎ ማሰብ ለእኔ ግራ ነው የመሰለኝ፡፡ በቤቱ ባለቤት ጩኸቱ የአካባቢው ሰው ተሰበሰበ፡፡ ፖሊሶቹ ወደ ግቢ መግባት ነበር እና የፈለጉት ገቡ፡፡ ቤቴ ተንኳኳ..ግራ ብጋባም መክፈት ነበረብኝ እና ከፈትኩ፡፡ የሀገሪቱ ፖሊሶች እና ከፍተኛ ባለ ማዕረጎች ቤቴ ሲፈተሸ አደረ፡፡ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ብጠይቅም ከቤትህ የወጡት ልጆች ሀሺሽ ይዘው ተይዘዋል እና አንተ ነህ የሰጠሀቸው ተባልኩ፡፡ በማግስቱ ለUNHCR ቢሮ አሳወኩኝ፡፡ ቢሮው ጠበቃ አቁሞልን ያሉበትን ማፈላለግ ጀመርን፡፡ ማንም ያሉበትን ሊያውቅ አልቻለም፡፡ ለአራት ቀን ከተያዙት ልጆች ጋር መገናኘት አልቻልኩም፡፡ ከሰባት በላይ የተለያየ ፖሊስ ጣቢያ ቢያዞሩዋቸውም የተለያየ መርማሪ ቢመረምራቸውም የተገኘባቸው ነገር ስለሌለ በዋስ እንዲወጡ ተባለ፡፡ የተያዙበት ሁኔታ አግባብ ባልሆነ እና ሀሺሽ ይዘዋል በሚል ቢሆንም ምንም ስላልተገኘባቸው ትላንት እሁድ መስከረም6 2005 ተፈቱ፡፡ እስከአሁን ይፋ አድርጌ ለማሳወቅ ያልፈለኩት በእስር ላይ ስለነበሩ ያሉት ያጠብቁባቸዋል ብዬ በመፍራት ነው፡፡
    ሙሉ ቤቴን ፈትሸው ሄዱ፡፡ ከቤትህ የወጡት ልጆች ሀሺሽ ይዘዋል ተብሎ ቢሆንም የፈተሹት የተገኘ ነገር ባለመኖሩ ይዘውኝ መሄድ አልቻሉም፡፡ እኔም እስከአሁን ከቤቴ ርቄ ሁኔታውን ስከታተል ነበረ፡፡ ቤቴን በተደጋጋሚ ለመፈተሸ ተመላልሰው ቢሞክሩም ሸሽቼ ስለሆነ ያለሁት በሩን ሰብረው እንዳይገቡ የቤቱ ባለቤት ስለከለከለ ከመበርበር ተጠብቆ አለ፡፡ የUNHCR ቢሮ ጠበቃም ቤቱ እንዳይፈተሸ እና በኪሳቸው ይዘው መተው አንዱ ቦታ በመደበቅ አገኘን ብለው የማልወጣበት ዘቅጥ ሊከቱኝ እንደሆነ ነግሮኝ የሰጡኝ መፍትሄ ቤት እንድቀይር ብቻ በመሆኑ ደህንነቴ አደጋ ውስጥ መሆኑን ተረዳሁ፡፡ ቤት በምቀይር ሰዓት የራሳቸውን የህግ ጠበቃ ለእማኝነት በማቆም ብቻ እንደሚተባበሩኝ ነው ከቢሮው ያገኘሁት ምላሽ፡፡ የሚያሳዝነው ነገር በዚህ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር ሁለቱን አትሌቶች ጨምሮ ከአራት ወር በኋላ እንድቀርብ ነው ቢሮው ቀጠሮ የሰጠን፡፡ አራት ወር ድረስ እንዴት ልሆን እንደምችል የሰጡኝ ምክርም ቤቱን ባወቁ ቁጥር ቀይር የሚል ብቻ ነው፡፡ የፍትህ ያለህ!!!!!…የሚባልበት አካል አጥተን በሰቀቀን ለመኖር ተገደናል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ወገን ብሎ ሊረዳን ያሰበ ካለ አረቢኛ በሚናገር ሰው ስለጉዳዩ እየተከታተለ ያለውን ጠበቃ ከታች ባሰፈርኩት ቁጥር ማነጋገር የሚችል ካል እርዱን፡፡ ካልሆነም አማርኛ አስተርጓሚ ስለሚኖር እንዲያቀርብላችሁ ጥይቁ፡፡   00967770676763 ወይም 0096776450945 ጣሪቅ ሙኸነድ
ይባላል የIDF ጠበቃው፡፡

No comments:

Post a Comment