Tuesday, September 11, 2012

በሟቹ የወያኔ ቁንጮ መለስ ዜናዊ ሞግዚቲነት ሥር የነበረው የህወሃት/ ኢህአደግ አመራር ህብረተሰቡን “ የመለስ ዜናዊን ራዕይ ለማሳካት እንተጋለን “በሚል መፈክር ሥር ለማንቀሳቀስ ከፍተኛ ዘመቻ መክፈቱ ታወቀ


ህወሃት /ኢህአደግን በራሱ አምሳልና አመለካከት ቀርሶ ያሻውን ፖሊሲ እየነደፈ ያለምንም ተቃውሞ ሲተገብርና ሲያስተገብር የኖረው መለስ ዜናዊ ከዚህ አለም በሞት ከተለየ ወዲህ ብቸኛ አውራውን የተነጠቀው አመራር “የክቡር ጠቅላይ ሚንስቴራችንን ራዕይ ለማሳካት እንተጋለን” የሚል መፈክር ቀርጾ ህዝቡን በመፈክሩ ዙሪያ ለማሰለፍ ከፍተኛ የሆነ ዘመቻ እያካሄደ መሆኑን ለማወቅ ተችሎአል።
ወያኔ ኢህአደግ ላለፉት 21 አመታት አስመዝግቤያለሁ የሚላቸውን ድሎች ሁሉ በመለስ ዜናዊ አድራጊና ፈጣሪነት የተመዘገቡ እንደሆነ ያለምንም ሃፍረትና መሸማቀቅ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በመናገር ላይ ያሉ የኢህአደግ አመራሮች አውራቸውን በሞት ከተነጠቁ ወዲህ እያስተጋቡት ያለው “የቀድሞ አለቃቸውን ራዕይ ለማሳካት እንተጋለን” መፈክር የአመራሩን አቅመ ብስነት ከመግለጽ አልፎ መለስ ዜናዊ  በህይወት ዘመኑ ከምዕራባዊያን መንግሥታት ጋር ሲላተምባቸው የኖረው የዲሞክራሲና የሰብ አዊ መብት ጉዳይ ያሳሰባቸው እንደማይመስል ምልክቶች መታየት መጀመራቸው እየተዘገበ ነው።
በአገሪቱ ውስጥ ብቸኛ የሆነው ነጻ ጋዜጣ ፍትህና የአንድነት ፓርቲ ልሳን የሆነው ፍኖተ ነጻነት እንዳይታተም የታገደው መለስ ዜናዊ ከዚህ አለም በሞት ከተለየ ወዲህ መሆኑ ይህ አውራው እንደሞተበት ንብ ግራ የተጋባው የኢህ አደግ አመራር ገና ከጅምሩ እየገባበት ያለውን አጣብቂኝ ያሳያል የሚሉ ፖለቲካ ተንታኞች አሉ።
በመለስ ዜናዊ መቃብር ላይ የተገኙ የአፍሪካ መሪዎችም ሆኑ የምዕራባዊያን ተወካዮች ያለገደብ ወደ አገሪቱ ይጎርፍ በነበረው የእርዳታና የብድር ገንዘብ የተገነቡትን መንገዶችና ህንጻዎችን እንደልማትና እድገት በመቁጠር ሟቹን መለስ ዜናዊ ሲያወድሱ በመልካም አስተዳደር፤ የሰብአዊ መብት አያያዝና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን በተመለከተ አንዳቸውም ሳት ብሎአቸው እንኳ ለመለስ ዜናዊ ውዳሴ አለማቅረባቸው ወይም እውቅና ለመስጠት አለመፈለጋቸው ለአዲሱ የወያኔ አመራር ምን መልዕክት ለማስተላለፈ ፈልገው እንደሆነ ወያኔዎች እስከዛሬዋ ቀን ድረስ የተረዱት አይመስልም ተብሎአል።
“የመለስ ዜናዊን ራዕይ ለማሳካት እንተጋለን” በሚለው የአዲሱ  ኢህአደግ አመራር መፈክር ሥር ለተለያዩ የግል ጥቅሞች አገር ቤት የሚመላለሱ የዲያስፖራ ኮሚኒቲ አባላትም ተሳታፊ እንደሚሆኑ በተለያዩ አገራት የተመደቡ የወያኔ ዲፕሎማቶች በልዩ ጥንቃቄ መርጠው ለዚሁ ተግባር አገር ቤት የላኩዋቸው ግለሰቦች በፈረደበት የኢትዮጵያ ቴለቪዝን ቃል ሲገቡ ታይተዋል።

    No comments:

    Post a Comment