አሁን በቤተ መንግስት ዙሪያ ከሚሸከረከሩ ቡድኖች የምንሰማው ድምጽ “የመለስ ራእይ” የሚል ነው።የመለስ ራእይ “ሳይበረዝ ሳይከለስ” ይፈጸማል የሚለውም አውራ መፈክራቸው ሁኗል።
አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትርም ድምጹን ከፍ አድርጎ እኔ የማስፈጽመው የመለስን ራዕይ ነው ብሎናል።እንግዲህ የራሱ ራእይ ከሌለው ግለሰብ የሚጠበቅ አዲስ ነገር ይኖራል ብሎ ማሰብ ከስህተት ይጥላል።
ኢትዮጵያችን አዲስ ራዕይ ያለውን መሪ ትፈልጋለች።አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ሃ/ማሪያም ደሳለኝ አሁን ኢትዮጵያ የምትፈልገው ዓይነት መሪ ለመሆን ራሱን ያዘጋጀ አይመስልም።ዘመኑና አገሪቷ የምትፈልገው የራሱ የሆነ አዲስ ራዕይ ያለው ሰው ሆኖ ሳለ የአንድን ዘረኛ ግለሰብ ራዕይ አስፈፅማለው ማለት የአገራችንን ችግር ከማባባስ በቀር የሚፈይደው መልካም ነገር የለም።ሃ/ማሪያም በተሾመ ወይም በተመደበ ግዜ ያደረገው ንግግር ደግሞ ሰውየው ኢትዮጵያን የመሰለች ፈረጀ ብዙ ችግር ያለባትን አገር ለመምራት ራሱን እንዳላዘጋጀ የሚያሳይ ነው።”እኔ እየተከተልኩ እናንተ እየመራችሁኝ” እንዘልቃለን ማለቱ አለመዘጋጀቱን የሚያመለክት ነው።ራሱ መሪ ሁኖ ሳለ ሌላ የሚመራውን የሚፈልግ ኢትዮጵያችንን ከታሰረችበት የዘረኝነት እና የዝሪፊያ ሰንሰለት ያላቅቃታል ብሎ መጠበቅ አዳጋች ነው።
”እናንተ እየመራችሁኝ” የሚለው ትህትና ያለው ንግግር በመምሰሉ ሊያሳስት ይችላል።ይሄ ትህትና አይደለም።ትህትና ሊሆን የሚችለው “እናንተ” የሚለው የኢትዮጵያን ህዝብ ቢሆን ኑሮ ነበር።”እናንተ እየመራችሁኝ” የሚለው ከመጋረጃው ጀርባ የተሰለፉ የሰይጣን ልጆችን ሌሎች እነመለስ ዜናዊዎችን እንጂ የኢትዮጵያን ህዝብ አይደለም።ሌሎች ጨካኞች፤ሌሎች ከእውነት ጋር የማይተዋወቁ ሃሰተኞች፤ሌሎች አገራዊ ስሜት የሌላቸው ዘረኞች ከመጋረጃው ጀርባ ያሉ የሰይጣን ልጆችን ነው የራሱ መሪ አድርጎ የሾማቸው እና “እናንተ እየመራችሁኝ” የሚለው። ሃ/ማሪያም ደሳለኝ የብዙሃን መሪነቱን ትቶ ፤ጥቂቶችን ለመከተል የመረጠ ስለሆነ ከእርሱና እርሱ ካለበት ድርጅት ነጻነትን፤ፍትህንና እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መጠበቅ አይቻልም። ኢሕአዴግ/ህወሃት ነፃነትን ሳያውቅ ስለነጻነት በባዶ የሚጮኽ፤የፍትህ ውብት ያልገባው ግን ደግሞ ስለፍትህ ከማንም በላይ ለማስተማር የሚሞክር፤ የዴሞክራሲን ዋጋ ሳያውቅ ዴሞክራሲን አመጣሁላችሁ ማለትን ብቻ የሚያውቅ ሃሰተኛ ድርጅት ነው። ህወሃትን ከውሸት፤ ውሸትን ከህወሃት መለየት የማይችልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።ህወሃት ወይም የመለስ ዜናዊ ደቀመዝሙራን በውሸት ዓለም ውስጥ የኖሩ የጭለማው ንጉሶች እንጂ ለኢትዮጵያችን በጎ ራዕይ ያላቸው አይደሉም።
የመለስን ራዕይ ማስፈፀም ማለት እኔ ብቻ ባይነትን፤ ሃሰተኝነትን፤ በዘር ላይ የተመሠረተውን አድልዎ፤የተጀመረውን የመሬት ንጥቂያ፤ ዜጎች በነፃነት እንዳያስቡ የሚደረገውን አፈና አስፋፍቶና አጉልቶ ማስፈፀም ማለት ነው እንጂ ሌላ በጎ ነገር የለም። መለስ ዜናዊ ከጨቅላነቱ ዘመናት ጀምሮ በጥላቻ ተኮትኩቶ ያደገ እንጂ በፍቅር ታንፆ ያደገ ሰው ባለመሆኑ ትቶት ያለፈውም ከቅምና ጥላቻ የጸዳ ነገር አይደለም ። ገና ህፃን ሳለ የመሃል አገር ህዝብ በተለይም አማራ ጠላት እንደሆነ እየተነገረው ያደገ፤ ያንንም ህዝብ ለመበቀል በቂም ዕዳ አገሪቷንና ህዝቧን ዋጋ ሲያስከፍል ኖሮ ለይቅርታና ለንሰሃ ሳይታደል ያለፈ ግለሰብ ነው። መለስ ዜናዊ በህይወት ዘመኑ ከቀደሙት ነገስታት መካከል አፄ ቴዎድሮስንና አፄ ምንሊክን ሲያንቋሸሽ ብዙ ጊዜ ተደምጦአል። ”አፄ ቴዎድሮስን ሲከሳቸው ኢትዮጵያን አንድ ሊያደርጉ የሄዱበት መንገድ በጉልበት ስለነበር ኢትዮጵያን አንድ ሳያደርጉ አልፈዋል” ይል ነበር። የዚህ ዋና ዓላማ አፄ ቴዎድሮስን በማንቋሸሽ የእርሱን የረከሰ ስብዕና መገንባት ነበር። እርሱ በዚህ ዘመን በዚያች አገር ላይ እኔ ያልኩት ብቻ ካልሆነ ብሎ የገደላቸውን ዜጎች፤በእርሱ እምቢ ማለት አገራቸውን ትተው የተሰደዱ የአገሪቷን ዜጎች፤በርሱ ምክንያት በየእስር ቤቱ ታጉረው የሚሰቃዩ ዜጎችን በተመለከት ግን የሚጠይቀው እንዳይኖር ማድረጉን ዜጎች የሚያውቁ አይመስለውም። ስለ አፄ ምንሊክ ክፋት ሲናገር ደግሞ “ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት በውጭ አገር ሙያተኞች ላይ ማተኮራቸው አገሪቷን ለድህነት ዳርጓታል” ብሎ ነበር። የንጉሱ ድርጊት በፍጹም ሊያስመሰግናቸው የሚገባ ትልቅ ተግባር ቢሆንም መለስ ዜናዊ ግን ሊያራክሰው ሞክሯል። ይሄ አባባሉ የፍጹም ጥላቻው መገለጫ መሆኑን ከማሳየት በቀረ የፈየደው ቁም ነገር አልነበረም። አፄ ምንሊክ በዚያ ዘመን የመሠረቱትን ቴሌ ዛሬ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያዊያንን እየነቀለ ለውጭ አገራት ኩባኒያዎች ሰጥቷል። የሚያሳፍረውም አገርን ድሃ የሚያደርገውም የመለስ ዜናዊ ሥራ እንጂ የአፄ ምንሊክ በጎ ራዕይ አልነበረም። እንግዲህ ሌላው የመለስ ዜናዊ ራዕይ የአገሪቷን መሠረቶች ማፈርስና በፍራሹም ላይ የራሱን የተጠላ ስብዕና መገንባት ነበር።ይህን የመሰለውን ራዕይ “ሳልበርዝ ሳልከልስ” አስፈጽማለው ማለት ትልቅ ስህተት ነው። በታሪክም ያስወቅሳል።
የመለስ ዜናዊ ራዕይ በትግራይ ልጆች ግንባር ቀደም ተጋዳላይነት በተገኘው ድል ለርሱ ታማኝ የሆኑትን አባላቱን ልዩ ተጠቃሚ በማድረግ ከተቻለ ፓርቲው እስከ ወዲያኛው ትውልድ እንዲገዛ ማድረግ ነው። ለዚህም ስጋና ደማቸው እየተቆጠረ የኔ ነው የሚላቸውን ሁሉ የአገሪቱን ግዙፍ ተቋማት እንዲቆጣጠሩት ያደረገው። በተለይ እርቃኑን የወጣው በመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ ያለው ዘርን መሠረት ያደረገ አወቃቀር የመለስ ዜናዊ ዘረኝነት ደረጃ አመልካች እንጂ በአፍ ሲያወራና ተከታዮቹ እንደገደል ማሚቶ ተቀብለው ሲያስተጋቡት እንደኖሩት የብሄሮችን እኩልነት የሚያረጋግጥ አይደለም።የብሄሮችን እኩልነት አረጋግጣለው ብሎ ድምጹን ከፍ አድርጎ ጩኾ ሲያበቃ በብሄሮች መካከል በግልጽ የሚታይ አድልዎ የፈፀመ መለስ ዜናዊና እርሱ የሚመራው ህወሃት የተባለው ዘረኛ ድርጅት እንጂ ሌላ ማንም አይደለም።የመለስ ዜናዊ ራእይ ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊያን ጥቂቶችን ተሸክመው፤ራሳቸውን “ወርቅ እና ጀግና” ብለው የሚጠሩ ጥቂቶች ደግሞ ብዙሃኑን ተጭነው እንዲኖሩ ነው። ሃይለማሪያም ደሳለኝ ይሄንን ራዕይ ነው እንግዲህ “ሳልበርዝ ሳልከልስ” አስፈፅማለው በማለት ደጋግሞ ቃል እየገባ ያለው ። ይህ ደግሞ ሌላው ቀርቶ ለራሱ ክብር አለኝ ከሚል ተራ ዜጋ ረንኳ የሚጠበቅ አይሆንም። እንዴት ሰው መርጦ ባልተወለደበት ዘሩ ምክንያት ስብዕናው ሲዋረድ ተሸክሞ ይኖራል? እንዴትስ ቢሆን ነው በውክልና የራሱን ስብዕና ያዋረደውን ፖሊሲ ሳይከለስ ሳይበረዝ እተገብራለሁ ብሎ ቃል የሚገባው? ይሄንን ጥያቄ ለመመለስ ሃይለማሪያም ደሳለኝን መሆን ይጠይቃል።
ነገሮችን ለማሳጠር መለስ ዜናዊ ለአገርና ለወገን የሚበጅ በጎ ራዕይ ያልነበረው ግለሰብ ነበር። ይሄን ሃቅ ወደጎን ትተው ”አባይን የደፈረ” የሚል ባዶ ጩኸት የሚጮሁለት ሁሉ ሊያስተውሉት የሚገባው ቁምነገር አባይን ለመገደብ ቅንነቱ ከነበረ ሱዳን አፍንጫ ሥር ሂዶ ድንጋይ ማስቀመጥ ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲባል የተፈጸመ አጉል ጀብደኝነት እንጂ ለአገር ከማሰብ የሚመነጭ አለመሆኑን የሚገነዘቡበት ቀን ሩቅ አይሆንም። ”አባይን የደፈረ” ከሚለው ባዶ ጩኸት ባሻገር አባይ ተገድቦ ለልማት ሲውል ማየት የሁላችንም የዘመናት ራዕይ ሆኖ የኖረ ነው። ለመለስ “አባይን የደፈረ” ተብሎ በካድሬዎቹና የጥቅም ተከታዮቹ የሚጮኸው ባዶ ጩኸት ምን እንደሆነ ለሰሚው ቀርቶ ለጯሂዎቹም ግልጽ አለመሆኑ ይፋ እየሆነ መጥቶአል። እንኳን የውጪውን የአገር ውስጡንም ችግር ለመቅረፍ ፈቃደኝነትና ቀናነት ሳይኖር ምንም አቅምና የገንዘብ ጉልበት ሳይኖር በባዶ ሜዳ ስለ አባይ መደስኮር ጀብደኛ ያሰኝ እንደሆን እንጂ የሚያስወድስና የሚያስሞካሽ አይደለም።
መለስ ዜናዊ ለዚያች አገር በጎ ራዕይ ያለው መሪ ቢሆን ኑሮ ባለፉት 21 ዓመታት ውስጥ የፈሰሰው ደም በኢትዮጵያች ምድር ባልፈሰሰ ነበር። ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብትን ከሚረግጡ አገሮች ተርታ ባልተሰለፈች ነበር። እሥር ቤቶች በጋዜጠኞች እና በፖለቲካ ድርጅት አባላትና መሪዎች ባልተጨናነቁ ነበር። አገራችን ዘመኑ ከደረሰበት የኢንቴርኔትና የሳታላይት አገልግሎቶች ታግዳ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ኋላ ቀር ባልተባለች ነበር። ዜጎች ያለፍርሃት ሃሳባቸውን መግለጽ የሚችሉባት አገር በሆነች ነበር። የአገሪቱ አንጡራ ሃብት ለዘርፎ አስዘራፊ ክፍት ባልሆነ ነበር፤ ለም መሬታችን ከተወላጅ ተነጥቆ ለባዕዳን ባልተቸበቸበ ነበር። ኤረ ስንቱ ተዘርዝሮ ያልቃል? ታዲያ እነዚህ ቀላል ግን ደግሞ መሠረታዊ ጥያቄዎች መልስ ያላገኙባትን አገር ትቶ ያለፈ ግለሰብን ትልቅ ራዕይ ያለው መሪ አድርጎ መለፍለፍ ከትዝብት በቀር የሚጨምረው ነገር ከቶ ምን ይሆን?
እንግዲህ ሃ/ማሪያም ደሳለኝ በዚያች አገር ፈርጀ ብዙ ችግሮችን ፈጥሮ ያለፈውን የመለስ ዜናዊን ራዕይ ሳልበርዝ ሳልከልስ አስፈጽማለው ማለቱ ለአገራችን አይበጃትም። እርሱ ተመርጦ ሳይሆን በህወሃት ተመድቦ ነው ሥልጣን የያዘውና ከመጋረጃ በስተጀርባ ሆነው ሊያሽከረክሩት ከሾሙት ጥቂት የህወአት ማፊያዎች ጥቅም አስከባሪነት ያለፈ ተግባር ሊያከናውን ይችላል ተብሎ መታሰብ የለበትም። እናም እኛ ብዙሃን ያለን ብቸኛ አማራጭ ህወቶች ሃ/ማሪያም ደሳለኝንና መሰሎቹን አስከትለው ሊነፍጉን የሚሞክሩትን ነፃነታችንን ለማስመለስ ቀበቷችንን ጠበቅ አድርገን ግንባራችንን ሳናጥፍ የጀመርነውን ትግል መቀጠል ብቻ ነው።
ግንቦት ሰባት ለፍትህ፤ለነፃነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ ለእኩልነት እና ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ግንባታ የጀመረውን ትግል አጠናክሮ ይቀጥላ። ከሌሎች የህግ የበላይነት ተመስርቶ፤ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ሁኖ፤ የፀጥታውና የአገር መከላከያ ኃይሉ ከተያዘበት የዘረኝነት ሰንሰለት ተላቆ፤ ዜጎች በአመለካከታቸው ብቻ አሸባሪ መባላቸው ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ አብቅቶ፤ የሙያ ማህበራት ያለ መንግስት ጣልቃ ገብነት መደራጀት ችለው ለማየት ከምር ፍላጎት ካላቸው ድርጅቶች ጋርም የጀመረውን አብሮ የመታገል ስልት በረቀቀ ዜዴ አጠናክሮ ይቀጥልበታል።
በመጨረሻም እንዲህ ያለ ሥርዓት በኢትዮጵያ ተመሥርቶ ማየት የምትፈልጉ ሁሉ ከትግሉ ጎራ እንድትቀላቀሉ የትግል ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !
No comments:
Post a Comment