Saturday, May 19, 2012

ክብር ጠቅላይ ሚኒስትር አሜሪካ ያሉ ኢትዮጵያውያን “እየደገሱልዎ” ነው!



በአቤ ቶኪቻው
የዚህ ፅሁፍ አላማ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን በአሜሪካ እየተዘጋጀባቸው ያለውን ታላቅ ተቃውሞ “ማሳበቅ” ሲሆን ቢቻል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዞውን እንዲሰርዙት ባይችሉ ደግሞ ሌሎች ዘዴዎች በመጠቆም ለጠቅላይ ሚኒስትራችንን ያለንን ተቆርቋሪነት ማሳየት ነው። (መቼም ይቺን አንቀፅ ያነበበ የኢንሳ “ዘጊ” ብሎጋችንን በሰፊው እንደሚከፍተው እርግጠኛ ነኝ!)
ሰሞኑን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከአሜሪካው ፕረዘዳንት ባራክ ኦባማ ጋር አሜሪካ ሊገናኙ ተቀጣጥረዋል። በነገራችን ላይ ኦባማ ናቸው የጋበዟቸው። (ለነገሩ ሰላም ከተመለሱ ኢቲቪ “ሀገራችን አስራ አንድ ነጥብ ሁለት በመቶ የግብዣ እድገት አሳየችች።” ብሎ እንዴት እንደተጋበዙ በዝርዝር ሳይነግርዎ ልሽቀዳደም ፈልጌ እንጂ ጆሮዎ “ስትራፖ” እስከሚይዘው ድረስ ይሰሙታል። በርግጥ ኢቲቪ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን የተጋበዙት በሀገሪቱ ያለውን የምግብ እጥረት አስመልክቶ ምን ብናደርግላችሁ ነው የሚሻላችሁ? በሚል ለመማከር መሆኑን አይነግረንም።(“ይደብቁናል እኮ አባዬ…” አለ ያ ቀልደኛ)
ለማንኛውም በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ በዋሽንግተን ካምፕዴቪድ አቶ መለስ ከግሩፕ ስምንት “ጂ8” ሀገራት ጋር ስብሰባ ይቀመጣሉ። ይሄ በርሳቸው ለምናምን ለኛ ታላቅ እመርታ ነው…! ቀኑንም እንደ ብሄራዊ በዓል ልናከብረው ይገባል። ችግሩ ግን ወዲህ ነው…
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሜሪካ ለዚህ ስብሰባ ሲመጡ በርካታ ኢትዮጵያውያን በዛ ተሰለፈው ይጠብቋቸዋል። ሰልፉ የእንኳን ደህና መጡ አይደለም። የተቃውሞ እንጂ ሰልፈኞቹ እቅፍ አበባ ይዘው አይደለም የሚጠብቋቸው እንቅልፍ የሚነሳ መፈክሮችን እንጂ! ምስኪን ጠቅላይ ሚኒስትር ሰልፍ ወደ እርሳቸው ሳይመጣ እርሳቸው ወደ ሰልፉ ሲሄዱ በእውነቱ አንጀቴን በሉት።
በነገራችን ላይ ዛሬ አውራምባ ታይምስ ዌብ ሳይት ላይ ቀርበው የነበሩት ዶክተር ፍስሀ እሸቱ እንደነገሩን ከሆነ በርካታ ኢትዮጵያውያን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ሊጮሁባቸው በቂ ዝግጅት አድርገዋል። (እዝች ጋ እናጋነው ካልን አንዳንዶቹም ድምፃዊያን የሚሰሩትን “ቮካል ኤክሰርሳይስ” ሰርተው ሁሉ ነው የሚጠብቋቸው) አሜሪካ እና አካባቢዋ የሚኖር ግለሰብ በዚህ ሰልፍ ላይ የሚቀር የለም ተብሏል። ለዚሁ የሚሆኑ በርካታ አውቶብሶችም እንደተዛጋጁ ሰምተናል።
በእውኑ ለጠቅላይ ሚኒስትሬ ተጨነቅሁ እናም ይህንን ምክር ልመክራቸው ወደድኩ
ይሄውልዎ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እውነቱን ለመናገር እንደሰማነው ዝግጅት ከሆነ የሚገጥምዎትን ተቃውሞ መቋቋም የሚችሉ አይመስለኝም። እና “ምናባቴ ይሻለኛል…?” ያሉ እንደሆነ እንደሚከተለው እመክራለሁ፤
ዘዴ አንድ
ራስዎን ይቀይሩ። እልም ያለ አሜሪካዊ ራፐር ለመምሰል ሙከራ ያድርጉ። ከዛ ማንም ሰው ወደ እርስዎ አያይም ወይም አይጠቋቆምብዎትም ከዛ… ከዛ ደግሞ በጆሮዎ ሁነኛ የሙዚቃ ማዳመጫ “ኤር ፎን” ያድርጉ። ያው የተቃዋሚዎቹ ጩኸት የማይቀር ስለሆነ “መለስ በቃ!” “ኦባማ ከአምባገነኖች ጋር መቀመጥህን አቁም” “መለስ ዜናዊ ወንጀለኛ ነው” “መለስ ዜናዊ ወዘተ ነው…” በሚሉ መፈክሮች አይምሮዎ እንዳይነካ እና እርዳታውን በሙሉ ልብዎ ከመጠየቅ እንዳያቅትዎ በኤር ፎኑ “አይበላንዶ” የሚል ሙዚቃ ከፍ አድርገው ይክፈቱ።
ዘዴ ሁለት
የእንቅልፍ ኪኒን ይወሰዱ። የምሬን ነው የምልዎ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሰዉ አምርሮብዎታል። “በሰልፉ ላይ ዕድሜው ለአቅመ ተቃውሞ የደረሰ አንድ እንኳ የሚቀር ሰው የለም!” ብለው ሲመካከሩ በጆሮዬ ሰምቻለሁ። እርግጠኛ ነኝ የሚነሳብዎን የተቃውሞ መፈክር ሰምተው ሰው ይሆናሉ ብዬ አልገምትም። ስለዚህ በእውቅ ባለሞያ ተሰልቶ፤ ልክ ስብሰባው ቦታ ሲደርሱ ሊነቁ በሚችሉ መልኩ የተሰናዳ የእንቅልፍ ኪኒን ይውሰዱ። ከስብሰባውም ሲወጡ ያቺኑ ኪኒን የተቃውሞን ቦታ እስኪያልፉ ድረስ ታስተኛዎ ዘንድ ደግመው ይውሰዷት። ከዛም እኛ ራታችንን በእንቅልፍ እንደምንሸውደው እርስዎ ደግሞ ተቃውሞን በእንቅልፍ ሸወዱት ማለት ነው።
ዘዴ ሶስት
ከስብሰባው ይቅሩ። በበኩሌ በተቃዋሚዎቹ ብዛት እና በተቃውሞ ቃላቸው የተነሳ ያቺ በብስጭት ግዜ የምትነሳ ህመምዎ ተነስታብዎ አጓጉል ሆነው ከሚቀሩ ሶስተኛው እና የመጨረሻው ምክሬ ከስብሰባው ቢቀሩ ይሻላል የሚል ነው። አዎና… የእነሱ እርዳታ በአፍንጫዎ ጥንቅር ብሎ ይውጣ… ይሄንን ያህል እኛ ርሃብ ብርቃችን ነው እንዴ!? በብስጭት ርስዎ አንድ ነገር ከሚሆኑብን ርሃብ በስንት ጣዕሙ!
በመጨረሻም
ሁሉም ነገር ካልተሳካ ይቺን ምርቃት እነሆ… “እግዜር የስራዎን ይስጥዎ!”

No comments:

Post a Comment