Monday, August 27, 2012

የ21 ዓመታት መከራን ያላገናዘበ የወ/ሮ አዜብ መስፍን መሪር ሀዘን፡


በፍቅሬ ዘለቀው (ኖርዎይ)


የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ም/ቤት ታማኝ ምንጮችን ጠቅሰው የአቶ መለስ ዜናዊን ዜና እረፍት ካወጁ እነሆ ከአርባ ቀናት በላይ አለፈው። ይሁን እንጂ አቶ በረከት ስምዖን የሚመሩት የኮምኒኬሽን ሚኒስቴር ቢሮ ሲያቀናብረውና ሲያሰራጨው ከነበረው የውሸት ድራማ፣ አይቀሬነቱ ደርሶ እነሆ በ15/12/04 ዓ.ም ውዥንብር ውስጥ ከተውት ለነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ይፋ ተደርጓል። ይህንንም ተከትሎ የአቶ መለስ ቤተሰቦች፣ ዘመዶች፣ ወዳጆች፣ ደጋፊዎችና የስርዓቱ ተጠቃሚዎች መሪር ሀዘናቸውን እየገለፁና በማስገደድ እያስለቀሱን ይገኛሉ።
የኢህአዲግ አጋር የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የክልል መስተዳድር አካላት፣ በአምሳላቸው ተጠፍጥፈው የተሰሩ የተለያዩ የሲቪክ ማህበራት ሐላፊዎች፣ የመንግስት ሠራተኞች፣ ታዋቂ ነጋዴዎች፣ ግለሰቦችና ከመቼውም በላይ በሥርዓቱ ተጠቂ የሆኑውን ብዙሀን ማሕበረሰብ በካድሬዎች እየተገደዱ፣ እንደ ጣዖት ለሚያመልኩት መሪያቸው ሕዝቡን በማስፈራራት በርሀብ በጠበሰ አንጀት እያስለቀሱና ድራማ እያሰሩት ይገኛሉ። እጅግ በጣም የሚገርመው ደግሞ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ለማኞችና በሆስፒታል የተኙ በሽተኞች የመሪያችሁን ሀዘን ወጥታችሁ ግለፁ መባላቸው የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪሚል ሱንግ በሞተ ጊዜ ከተፈፀመው በከፋ ሁኔታ ከላይ ከመንግስት በወረደ ትዕዛዝ እምባ ለማውጣት ሲታገሉ ማየት የሚያሳፍርም የሚገርምም ነው።
እንኳን የሀገር መሪ ቀርቶ፣ አንድ ተራ ግለሰብ የተወሰኑ ወዳጆች ሊኖረው እንደሚችል የታወቀ ቢሆንም፣ በአንፃሩ ግን የሥርዓቱ መሪዎችና ካድሬዎች አቶ መለስን ከኢትዮጵያ ሕዝብ አልፎ በአፍሪካና በዓለም ህዝብም ዘንድ የተወደደ፣ የተከበረና እንከን የለሽ እንደነበረ አድርጎ ለማቅረብ እንዲሁም ከንቱ ድርጅታቸውን በሕዝብ ዘንድ የተወደደ ለማስመሰል ሲጥሩ መታየት፣ ግብዞች መሆናቸውን ከማሳየት ባሻገር በምንም መለኪያ የኢትዮጵያን ሕዝብ ልብ ሊያማልሉ እንደማይችሉ የ1997 ዓ.ም ሕዝባዊ የተቃዋሚዎች ድጋፍ ሰልፍና የምርጫ ውጤት ሕዝቡ ምን ያህል እንደጠላቸው የሚያሳዩ የጎሉ ምስክሮች ለመሆናቸው የሚያውቁት ሐቅ ነው። የአቶ መለስ ዜናዊ ቅርስ በጥቂት የሕወሓት አቀንቃኞችና እንደ ወርቅ በቆጠሩት እፍኝ በማይሞሉ የትግራይ ቁንጮዎች ይሆን እንደሆን እንጂ ከዚያ የበለጠ ሊሆን አይችልም።
እንደ ሰብዓዊ ፍጡር በተለይም እንደ ኢትዮጵያዊያን እምነትና ባህል የየትኛውም ሰው ሞት ለማንም ደስታን አይሰጥም። በተለይም ለአፍቃሪው፣ ለኑሮ አጋሩ፣ ለቤተሰቡ፣ ለወዳጅ ዘመዱ በጣም የሚመር ሀዘንን፣ ብቸኝነትን፣ ጎደሎነትንና ረዳት አልባነትን ስለሚፈጥር እጅግ ቢበድል እንኳን ሲሞት በቀብሩ ወይም በማስተዛዘኛ ቦታ ላይ ቢያንስ ይገኛል አለበለዚያም ለእግዚያብሔር አሳልፎ ይሰጣል እንጂ ማንም ለማንም ምኞቱ አይሆንም።
page1image16704
ታዲያ በእግዚያብሄር ሐይል ባለቤታቸው የተወሰደባቸው የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍንን የመረረ ሀዘን ለተመለከተ እንደሰብዓዊ ፍጡርና እንደ ቤተሰብ አባልነት የማያዝን አይኖርም።
የአቶ መለስ አስከሬን ለአንድ ወር ሙሉ ከተቀመጠበት ማቀዝቀዣ ፍሪጅ ውስጥ አውጥተው አዲስ አበባ በገባበት ምሽትና ወ/ሮ አዜብ የባለቤታቸውን አስከሬን በተረከቡበት ወቅት፣ ....... ወይኔ ተቀጣሁ፣ እንኳን ደህና መጣችሁ፣ ...... መለስ ግን የለም፣ ..... ቤታችን ቀዝቅዟል፣ ...... አልጋው ባዶ ነው፣ ሲሉ የተሰሙት ትራሱን በእጃቸው አቅፈው ይዘው ነበር።
በመሪር ሀዘን ውስጥ ለምትገኙት ለአቶ መለስ ዜናዊ ቤተሰቦች፣ ዘመዶች፣ ጓደኞችና ወዳጆች የማቀርበው አንድ መሠረታዊ ጥያቄ አለኝ፤-
በአቶ መለስ፣ በሕወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣናትና በእርሳቸው እውቅና (ወ/ሮ አዜብ መስፍን) የወልቃይ ጠገዴ እና ጠለምት ጀግና ሕዝብን የእኩይ ተግባራቸው ተባባሪ ባለመሆኑ ወንዶች እየተመረጡ፣ የአልጋ ቁራኛ (በሽተኛ) ሳይቀር የወያኔ ስቆቃ መፈፀሚያ ባዶ-6 በተባለ እስር ቤት በማጎር በተፈፀመባቸው ስቃይ ብዛት ሰውነታቸው እስኪተላ ተገርፈው ዘር ማጥፋት በሚባል መልኩ የተጨፈጨፉ፣ በ21 ዓመታት ብልሹ አስተዳደር ሳቢያ በወለጋ፣ በአርሲ፣ በጋምቤላ፣ በሶማሊያ፣ በቤንሻንጉል፣ በሐረር፣ በሞያሌ፣ ወዘተ... በብሔርና ጎሳ ግጭት ምክንያት በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የአንድ ቤተሰብ አባላት የተጨፈጨፉ፣ ዋጋቢስ ለሆነ ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በአገር ሉዓላዊነት ስም ተግዘው ደመ- ከልብ የሆኑ፣ በቀናነት አገራቸውንና ወገናቸውን ሲያገለግሉ በአቶ መለስ ዜናዊ ፀጥታ አስከባሪ ተብየዎች በጠራራ ፀሐይ በጥይት የተገደሉት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አመራር የነበሩት የአቶ አሰፋ ማሩ፣ በወያኔ እሥር ቤት ማቀውና በሽተኛ ተደርገው የሞቱት የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን አለኝታ የነበሩት የፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስና የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት አባላትን በማናለብኝና እብሪት የተገረፉ፣ የተሳደዱ፣ በአደባባይ ላይ የተረሸኑና እስካሁንም ያሉበት ያልታወቁ፣ እንደነ ሸብሬ ደሳለኝ ዓይነት ለጋ ወጣቶች፣ ሕፃናት ልጆች፣ ሽማግሌዎችና አሮጊቶች፣ በአቶ መለስ ዜናዊ ቀጥተኛ ትዕዛዝ ርህራሄና ስብዕና እንደሌለው በሚነገርለት በአረመኔ አጋዚ የትግርኛ ተናጋሪ ቅልብ ወታደር በጎዳና፣ በበር፣ በመጫዎቻ ሜዳ ላይ ጭንቅላት ጭንቅላታቸው እየተመታ የተገደሉ፣ አካላቸው የጎደለ፣ የተገረፉ፣ የተሰደዱና የአዕምሮ በሽተኞች የሆኑበት የ1997 ብሔራዊ ምርጫ ተጎጂዎች፣ በሚደርሰው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ሳቢያ ወደ አረብ አገራት በመሰደድ የሚሰቃዩ፣ ህይወታቸውን የሚያጠፉና በአሠሪዎቻቸው የሚገደሉ ለጋ ሴት እህቶቻችን፣ በአቶ መለስ ዜናዊ አምባገነን አስተዳደር ስቃይ፣ ግርፋት፣ እስርና ግድያ ሲሸሹ ውሀ ያስቀራቸውና በሰውነት የውስጥ አካል ነጋዴዎች እየተገደሉ በሰሃራ በረሃ ያለ ቀባሪ አሸዋ ውስጥ ተቀብረው የቀሩ፣ የወያኔው ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለቅፅበት እንኳን ያላያቸው እንዲሁም የትኛውም የዜና አውታር ያልዳሰሳቸው ነገር ግን ቤት የሚቆጥራቸው፣ በተረሪስት ስም በውሸት ድራማ ተቀናብሮ በቃሊቲ፣ ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ በሚገኘው ቀሌንጦና የተለያዩ እስር ቤቶች ታስረው የሚማቅቁና በእስር ቤቶች በስቃይ ብዛት ህይወታቸው ያለፈ፣ ወዘተ...... ቤተሰቦች፣ አፍቃሪዎች፣ ወላጆች፣ ዘመዶች፣
ጓደኞችና ወዳጆችስ ስቃይ፣ መሪር ሀዘን፣ እሮሮ፣ ደም እንባ ማንባት፣ የመሳሰሉት ለአንዲት ሰኮንድ ትዝ ብሏችሁ ያውቅ ነበርን???
እንግዲያውስ እንደናንተው ወይም ከእናንተ እጅግ በላቀ መጠን ተንሰቅስቀዋል፣ ሀዘናቸውን በቀል ለሚመልስ አምላክ ተንበርክከው በዓይናቸው ያሳያቸው ዘንድ አንብተዋል፣ እስካሁንም እያነቡ ይገኛሉ። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱትን ተጎጂ ቤተሰቦች ሐዘን ከአቶ መለስ ቤተሰብ የከፋ የሚያደርገው ወ/ሮ አዜብ መስፍን ሙሾ እንዳወረዱት ዓይነት ብቻ ሳይሆን ልጆች ያለ አሳዳጊ መቅረት፣ የእለት ጉርሳቸውን በማጣት ወንዶች ልጆች የጎዳና ተዳዳሪ መሆንና ሴቶች ልጆቻቸው በመንገድ ዳር በመቆም ክብረ-ሥጋቸውን ለመሸጥ መገደዱ፣ በድህነት ተቆራምደው ያሳደጓቸው ልጆቻቸው በመገደላቸውና ከአረመኔው ሥርዓት ሲሸሹ ከታሰበበት ቦታ ሳይደርሱ በመንገድ ላይ የቀሩ የስደተኛ እናቶች ጧሪ አልባ መሆን ወዘተ፣ ወዘተ፣ ወዘተ፣....ነው።
ስለዚህ እናንተ የዚህ ሀዘን ተጠቂዎች የሆናችሁና በዚህ ሥርዓት ስም ሕዝብን ያሳዘናችሁና የበደላችሁ ሆይ የኑሮ አጋር ያደረጉት፣ ያፈቀሩት፣ የወደዱት፣ የወለዱትና ያሳደጉት ሲገደል ወይም ሲሞት እንደዚህ ከማሳዘን፣ መሪር እንባ ከማስነባቱም በላይ ብቸኝነትን፣ ጎደሎነትን፣ ረዳት አልባነትን፣ አለመረጋጋትን፣ በሽተኝነትንና እብደትንም ስለሚያስከትል ነገም በእኔ በማለት ካለፈው ስህተት ተምራችሁ በመተሳሰብና በመተዛዘን ለመኖር ፍርድን የማያጓድል እግዚያብሔር ማስተዋልን ይሰጣችሁ ዘንድ ምኞቴ ነው።
ኢትዮጵያንና ሕዝቧን እግዚያብሔር ይባርክ!!!!August 26, 2012,
ፀሐፊውን በ belete_z@yahoo.co.uk ሊደርሱት ይችላሉ፤፤ 

No comments:

Post a Comment