Police brutally beat up and arrest morethan 60 University students in Debremarkos. Read more
ትላንት ለተቃውሞ በወጡ የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ የመንግስት ታጣቂዎች በጥይትና በዱላ በወሰዱት እርምጃ ከባድ ጉዳት መድረሱን የአውራምባ ታይምስ ምንጮች ገለፁ፡፡ ባለፈው ዕሁድ የተቀሰቀሰው ዓመጽ መንስኤው በምግብ ጥራት መጓደል ቢሆንም ተቃውሞው ከዚህ አልፎ ፖለቲካዊ መልክ እንደያዘ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ዕሁድ ጧት በተቀጣጠለው በዚህ ተቃውሞ አብዛኛው ተማሪ ቁጣውን የዩኒቨርስቲውን መስታወቶች በመሰባበር እንደገለፀ የሚናገሩት ምንጮቻችን ምሽት ላይ በድንገት ወደ ግቢው የገቡት ታጣቂዎች ተማሪዎቹ ላይ ከመጠን ያለፈ ኃይል በመጠቀም ጉዳት እንዳደረሱ ገልፀዋል፡፡ በወቅቱ በታጣቂዎች በተወሰደው እርምጃ ከ60 ያላነሱ ተማሪዎች መታሰራቸውና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች ላይ ድብደባ እንደተፈጸመ ስሙን መግለጽ ያልፈለገ ተማሪ ለአውራምባ ታይምስ ገልጾአል፡፡ ተማሪው በወቅቱ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ከፍተኛ የተኩስ እሩምታ እንደነበረና በዚህ እርምጃም አብዱራህማን መሀመድ የተባለ ተማሪ በጥይት ተመትቶ መውደቁን ለዝግጅት ክፍላችን ገልጾአል፡፡ ተማሪው በደረሰበት ከፍተኛ ጉዳት በደብረ ማርቆስ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ በመከታተል ላይ እንደሚገኝና ሀኪሞች ለሚዲያ ምንም አይነት መረጃ እንዳይሰጡ ጥብቅ መመሪያ ተላልፏል፡፡ባለፈው ሰኞም ከጠዋት ጀምሮ ‹‹የታሰሩ ተማሪዎች ይፈቱ›› የሚል ጥያቄን ይዞ የቀጠለው ተቃውሞ ቀስ በቀስ ከዩኒቨርሲቲው ውጪ መስፋፋቱን ከከተማው ያገኘናቸው መረጃዎች አመላክተዋል፡፡ ተቃውሞው በደብረ ማርቆስ ከተማ ጎዳናዎች ላይ በቀጠለበት ወቅት በርካታ የከተማው ነዋሪዎችም ትዕይንቱን ተቀላቅለው ጥያቄው ወደ ፖለቲካዊ ተቃውሞ መሸጋገሩን የአይን እማኞች ገልጸዋል፡፡ በዚሁ እርምጃ ኦፕራሲዮን የተደረጉ ተማሪዎች እንደሚገኙና ይህንኑ ተከትሎ በደብረማርቆስ ከተማ ከፍተኛ ውጥረት መንገሱን የሚገልጹት እነዚህ የአይን እማኞች መንግስት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ ቢያስተላልፉም አብዛኛው ተማሪ እስካሁን ትምህርት እንዳልጀመረ ለመረዳት ተችሏል፡፡
source : http://www.ethiosun.com/2012/police-brutally-beat-up-and-arrest-university-students/
No comments:
Post a Comment