የሞዛምቢኩ መሪ የነበሩት ጀነራል ሳሞራ ማሼል በአውሮፕላን አደጋ በ1986 (እ.ኤ.አ) በሞቱ ጊዜ ወዳጃቸው ኮ/ል መንግስቱ
በአደባባይ ወጥተው፤ "ሳሞራ አልሞተም! ሳሞራ በመካከላችን አለ!" ብለው ሲናገሩ ትዝ ይለኛል። አለም አቀፍ ሜዲያው የሚለው
ሌላ - እሳቸው የሚነግሩን ሌላ። ነገሩ በለጋነት አስተሳሰብ ግራ ያጋባል። ኮሎኔሉ የሚናገሩት እንዳሁኑ ጥሬ ውሸት ሳይሆን፤
የሳሞራን በመንፈስ አለመለየት መሆኑ ቆይቶ ነበር የገባኝ።
እነ በረከት ስምኦን መለስ ይመጣል ነው የሚሉን። በመንፈስ ሳይሆን በአካል። ልክ እንደ አስፈሪ (ሆረር) ፊልም ላይ የምናየው
ጣዕረ-ሞት አይነት። ብዙዎች ይህንን የበረከት የፖለቲካ ቅኔ "ከጥቂት የእረፍት ጊዜ በኋላ የመለስ ስርዓት ተመልሶ ይመጣል። "
በሚለው መተርጎማቸው ታዲያ አያስደንቅም።
ከሶስት ወር በፊት - በያዝነው አመት - ደግሞ ዶክተሮችና አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የማላዊው ፕሬዚዳንት ቢንጉዋ ሙታሪካን
መሞት እየተናገሩ፤ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ግን በመንግስት ሜድያ ብቅ ብለው “ቢንጉዋ አልሞተም ደቡብ አፍሪካ ህክምና ላይ
ነው።” ይሉ ነበር።
የሙታሪካ ወራሾች የመሪያቸው ሞት በእጅጉ ረብሿቸው ኖሮ፤ በመጀመርያ መሪያቸው በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳለ ሲናገሩ ሰነበቱ፣
ቀተል አድርገው ትንሽ እንደነታመ፣ ከዚያ እያገገመ ነው፣ እያሉ ... ትንሽም ቢሆን ግዜ ከገዙ በኋላ ምእራቡ አለም ሊያጋልጣቸው
ሆነና እውነቱን መናገሩን ነበር የመረጡት። እዚህ ላይ የአንባገነኖችን የባህሪ ተመሳሳይነት እናያለን።
የፕሬዚዳንት ሙታሪካ ሞት በእጅጉ ያሳሰበው ሃገሬውን ሳይሆን የአሜሪካ መንገስትን እንደነበር ዘ-ኒው-ዮርክ-ታይምስ አስነብቧል።
ፕሬዚዳንት ቢንጉዋ ሙታሪካ እንደ መለስ እጅግ ክብርን በሚነካ ሁኔታ ባይሆንም የምእራቡ አለም ጉዳይ አስፈጻሚ ተላላኪ
ነበሩ። (የኋላ ኋላ ዊኪ ሊክ ይፋ ያደረገውን መረጃ አቅብለዋል ያሏቸውን የእንግሊዝን አምባሳደር ከማላዊ ሲያባርሩ ከምእራቡ
አለም መቃቃራቸው አልቀረም) የአቶ መለስ ማምለጥም ከነበረከት በበለጠ ምእራቡን ያስጨነቀ ለመሆኑ ከሚደረገው ድብብቆሽ
መረዳትይቻላል።
በአቶ መለስ ስርዓት መፍረስ ሊከሰት የሚችለው የሃይል አሰላለፍ እና ሊመጣ የሚችለው አዲስ የፖለቲካ አቅጣጫ
ምእራብያውያኑንም ማስጋቱ አልቀረም። በተለይ ስር ነቀል ለውጥ ቢመጣና ብሄራዊ ስሜት ያለው መንግስት ቢመሰረት ኢትዮጵያ
የአሜሪካ አጀንዳ አራማጅ ልትሆን እንደምትችል ምእራባውያኑ ይሰጋሉ። መለስም ቢሆኑ ለውጩ አለም በአለም አቀፉ መድረክም
ብቻቸውን ጎልተው ወጥተው ከስዎቻቸውም መሃል አንድ እንኳ በላምባዲና ተፈልጎ እንዳይገኝ ማድረጋቸው ለዚህ ስጋት
አስተዋጽኦ አድርጓል።
ዊኪ ሊክስ እንዳስነበበው አቶ መለስ የምእራቡ አለም ፍጹም ታዛዥ እና ጥሩ አሽከር ሆነው አገልግለዋል። በተለይ አስቸጋሪውን
የሶማሊያ (አል-ሻባብ) እና የአሜሪካ ጦርነት አቶ መለስ ተዋግተውላቸዋል። በኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ውድ ህይወታቸውን
እየከፈሉበት ያለው ይህ ጦርነት ሙሉ በሙሉ የሚታዘዘው ከአቶ መለስ እንደሆነ ራሳቸው ፓርላማቸው መስክረዋል። በጦርነቱ
ስንት ወታደር እንዳለቀ ፓርላማው የማወቅ መብት እንደሌለው በድፍረትና በንቀት ሲናገሩ አቶ መለስን የተቃወማቸው እንኳን
አልነበረም።
ይህንን በእንዲሁ እንተወውና ወደ እነ በረከት ህዝብን በመዋሸት የማታለሉ ዘዴ እንሂድ።
እ.ኤ.አ. በ1913 ዓ.ም. ዳግማዊ አጼ ሚኒሊክ ከዚህ አለም ከሞት ሲለዩ፤ ልጅ እያሱ የንጉሰ ነገስቱን ቦታ መያዛቸው ይፋ
አልተደረገም ነበር። በወቅቱ የካቢኔው ሚኒስትር የአጼውን መሞት ለሶስት አመታት ያህል ሆን ብሎ ደብቆት እንደነበር የታሪክ
መዛግብት ይነግሩናል። የአጼ ምኒሊክ ካቢኔ ሚኒስትሮች ይህንን ያደረጉበት ምክንያት የንጉሱ ሞት ዜና ከተሰማ በሃገሪቱ የርስበርስ
ብጥብጥ እና አለመረጋጋትን ሊያመጣ ይችላል የሚል ስጋት ስላደረባቸው ይሁን እንጂ ውስጥ ውስጡን የልጅ እያሱ አልጋ
ወራሽነትን በሙሉ ድምጽ ተቀብለውት እንደነበር በታሪክ ተመዝግቧል።
ወራሾቻቸው ለመደበቅ ይጣሩ እንጂ፣ አጼ መለስ ዜናዊ ከዚህ አለም በሞት እንደተለዩ የሚያረጋግጡ መረጃዎች አሁን ይፋ
ሆነዋል። የሚገርመው አቶ መለስ የሚቃወሟቸው ወገኖች ላይ ከህግ ውጭ ግድያ አልፈው የሞት ቅጣት ሲያስወስኑ ሰንብተው
እሳቸው ሞት ከተፈረደባቸው ወገኖች መቅደማቸው ነው።
ይህንንም ክስተት ተከትሎ የመጣው የአገዛዙ ሃይሎች የስልጣን ሽኩቻ እና የሃገሪቱ የሃይል ሚዛን አስላለፍ -በተለይ የህወሃት
ቁንጮዎች የሚኒሊክ ዘመኑን ታክቲክ ለመጠቀም ደፋ ቀና ሲሉ የወቅቱ ሁኔታ ከአጼ ሚኒሊክ ዘመን ፈጽሞ የተለየ መሆኑን
ያገናዘቡት አይመስልም። በመጀመርያ ያለንበት ሃያ አንደኛው ክፍለዘመን የመረጃ ዘመን በመሆኑ ያውም ፍጹም ከቁጥጥር ውጪ
የሆነው የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ሁሉንም ነገር እንደ አጉሊ መነጽር እያሳዩ ባሉበት ባሁኑ ወቅት ለረጅም ጊዜ ህዝብን እየዋሹ
መቆየት እንደማይቻልም አልተረዱትም።
በሁለተኛ ደረጃ የአጼ ሚኒሊክ ካቢኔ ቢያንስ ልጅ እያሱ ዙፋኑን እንዲረከብ በሙሉ ድምጽ ተስማምቶ ወስኖ ነበር። ካቢኔው
በወቅቱ ይሰጋ የነበረው በውስጥ የሚነሳ የስልጣን ሽኩቻ ላይ ሳይሆን ይልቁንም ከውጭ ሊመጣ በሚችል ሃይል ሳቢያ ሃገሪቱ
አለመረጋጋት ውስጥ እንዳትገባ በማሰብ ለመሆኑ ከተግባሩ በግልጽ እናያለን።
የነስብሃት እና በረከት ግን ግልጽ የሆነ የርስበርስ ግጭት እና የስልጣን ሽሚያ ለመሆኑ ከአነጋገረቸው ብቻ ይታያልእናያለን።
ስብሃት ነጋ ከምኑም ስለተገለሉ መረጃውም ያላቸው እናያለን።
“የአቶ መለስ ዜናዊ እረፍት በህወሃት ፖለቲካ ላይ ለውጥ አያመጣም!” ብለው ሊነግሩንም ሞክረዋል። ይህንን የሚያምኑ ካሉ
የዋሆች ናቸው። ላለፉት 20 አመታት ኢትዮጵያ በአንድ ግለሰብ አገዛዝ ስር ለመውደቋ ምንም መረጃ መጥቀስ አያስፈልግም።
መለስ ሀገሪቷን በህግ ሳይሆን ይልቁንም በአዋጅ ነበር ሲያስተዳደር የነበረው።
ለነጻ ፕሬስ አዋጅ፣ ለቤትና ንብረት አዋጅ፣ ለ "ሙስና" አዋጅ፣ ለ "ሽብር" አዋጅ፣ ለእርዳታ ድርጅቶች አዋጅ፣....ወዘተ። ይህ ደግሞ
ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውንና ለዘመናት ይሰራ የነበረውን የወንጀልም ሆን የፍታብሄር ህግ እንዲሁም የራሱ ፓርላማ ያጸደቀውን
ህገ-መንግስት ለመጣስ ምቹ ዘዴ ሆኖ አገልግሏል። ሃገሪቱ በህግ ሳይሆን በአዋጅ መተዳደር ስትጅምር ነው ፍትህ የሞተው።
በአንባገነን ስርዓት ውስጥ የግለሰብ ሚና ወሳኝ ብቻ አይደለም። በእንደዚህ አይነቱ ስርዓት መሪውንና ድርጅቱን መለየት
አይቻልም። ግለሰቡ ሲሞት ድርጅ ወዲያው ሲከስም እናያለን። የጀርመኑ አዶልፍ ሂትለር ትልቁ ምሳሌያችን ነው። ሂትለር በሰዎች
ውስጥ የፈጠረው የናዚ መርዝ ስር የሰደደ ቢሆንም በህልውናው ማብቂያ ናዚ የሚለው ስርዓት አበቃ። የሮማኒያው ኒኮላይ
ቻውቼስኮ፣ የካምቦዲያው ካሜሩዥ መሪ ፖል ፖት... ሲወድቁ የበሰበሰው ፓርቲያቸው ሲጠፋ አይተናል። ላለፉት 26 አመታት
በጦር ሄሊኮፕተር ጭምር ሲታገል የነበረው ታሚል ታይገር አማጺ ሃይል - ከሲሪላንካ ምድር የጠፋው በ2009 (እ.ኤ.አ) መሪው
ቬሉ ፒላይ ሲገደል ነበር። ከቬሉ ፒላይ ሞት በኋላ ታሚል ታይገር ዛሬ ዜና ሳይሆን ታሪክ ሆኖ ቀረ።
አንባገነኖች የመንግስት ስልጣን ብቻ ሳይሆን ቴክኖክራቱም ቢሮክራሲውንም በአንድ ሰው ትእዛዝ ነው የሚንቀሳቀሱት። ይህ
ባይሆን ስርዓቱ እንደ ስርዓት ይቀጥል ነበር። ቤልጂየም በፓርቲዎች አለመስማማት ጥምር ካቢኔው ወድቆ ከ 400 ቀናት በላይ
ያለመንግስት እየተዳደረች ነው። ሆላንድም በተመሳሳይ ምክንያት ካቢኔው ለሶስተኛ ጊዜ ፈርሷል። እነዚህ ሀገሮች በግለሰብ ሳይሆን
በስርዓት ስለሚመሩ አንድ ሰው ሞቶ አይደለም መላው ካቢኔ ፈርሶ ያለአንዳች ግርግር ይተዳደራሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ ይህ የአቶ መለስ ዜና እረፍት ፓርቲውን ይሰነጣጥቀዋል ብለው የሚያምኑ የህወሃት ባለስልጣናት ህዝቡን
ለማደናገርና በውስጣቸው ምንም ችግር እንደሌለ ለማስመሰል ሲናገሩ ይሰማሉ።
አቶ መለስ ሲመሩት የነበረው ስርዓት ከበሰበሰ ስንብቷል። ይህንን ከባድሜ ጦርነት ባኋላ የህወሃት አመራር ለሁለት ሲከፈል እና
የነአቶ መለስ ጎራ አሸናፊ ሆኖ በወጣበት ማግስት ከራሳቸው ከአቶ መለስ አንደበት የሰማነው ነው። "ህወሃት በስብሷል!" ነበር
ያሉት አቶ መለስ ዜናዊ። ይህንን የበሰበሰ ፓርቲ እየመሩ ያለፉ አስር አመታትን ሊዘልቁ እንደማይችሉም ግልጽ ነው። እነ ስዬ
አብርሃን ገፖለቲካው ምእዋር ካስወገዱ በኋላ ካቢኔያቸውን መበወዝ ነበረባቸው። የተቃቃሩ የህወሃት ቡድኖችን በባትሪ እየፈለጉ፣
አንዱ ሌላዉን እንዲጠራጠር፣ እርስ በርስ መተማመን እንዲጠፋ፣ በተጠና መልኩ በየምኒስትሩ ቢሮ ሾሟቸው። በአለም አቀፉም
መድረክ ከራሳቸው ውጭ አንድ የህወሃት ሰው እንዲመጣም እንዲታይም አላደረጉም።
የአቶ መለስ ወራሾች በየመገናኛ ብዙሃኑ እየወጡ የሚቃረኑ አስተያየቶች መስጠጣቸው ራሱ በውስጣቸው ያለውን ችግር አጉልቶ
ያሳያል። የስልጣን ትግሉ ጀምሯል። ይህ ሊያሳስበን አይገባም።
ከሁሉም በላይ ሊያሳስበን የሚገባው ሃገሪቱ በችግር ላይ መሆንዋ ነው። ለአስርተ አመታት የታፈንና እንደ እሳተ ገሞራ ሊፈነዳ
የታመቀ እሳት እንዳለ ይታያል። በሙስሊም ወገኖቻችን የተጀመረው አመጽ የዚህ ሱናሚ ነጸብራቅ ይመስላል። በመኖር እና
ባለመኖር መሃከል ያለው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በአመጽ ቋፍ ላይ ይገኛል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ፈተና ነው። የፖለቲካ
ፓርቲዎች እውነት ለሃገርና ለህዝብ ደህንነት መቆማቸውን የሚያሳዩበት ፈታኝ ወቅት ነው።
ይህ ችግር በፖለቲካ ፓርቲዎች ጫንቃ ላይ ብቻ መተውም ተገቢ አይደለም። የዲሞክራሲ ሃይሎች፣ ተቃዋሚና የሲቭክ ድርጅቶች
ተሰባስበው ሁሉንም አንድ በሚያደርግ የጋራ ጉዳይ ላይ ተወያይተው ስምምነት ላይ መድረስ ያላባቸው ወቅት አሁን ነው።
አገርን የማዳን ስምምነት።
አሁን ስለ ስልጣን፣ ስለፓርቲ ፕሮግራም ስለ ዲሞክራሲ ወዘተ የምናወራበት ወቅት አይደለም። የመለስ መንፈስ እነ በረከትን አንድ
ቢያደርጋቸው ባያደርጋቸውም ለላው ወገን ግን ስለ ህብረት እና አንድነት ለጋራ አላማ መነጋገር አስፈላጊነት ያለበት ወቅት ላይ ነው
ያለነው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ያገባናል የሚሉ ሃይሎች ይህንን ካላደረጉ መጭው ዘመን ካለፈው የከፋ ሊሆን እንደሚችል
ለአያዳግትም።
ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com
July 23, 2012
No comments:
Post a Comment