ነፃና ዲሞክራሲያዊ በሆነ ምርጫ የጋና ህዝብ የመረጣቸዉና ባለፈዉ ግንቦት ወር ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የአፍሪካን የምግብ ደህንነት በተመለከተ አሜሪካ ድረስ አስመጥተዉ ካማከሯቸዉ የአፍሪካ መሪዎች አንዱ የነበሩት ፕሬዚዳንት ጆን አታ ሚልስ በድንገተኛ ህመም ባለፈዉ ማክሰኞ ሐምሌ 17 ቀን 2004 ዓም ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።
የጋና ዲሞክራሲ መጎልበት ምልክት አንደሆኑ የሚነገርላቸዉና የአራት አመት የስልጣን ዘመናቸዉን በቅርቡ የሚጨርሱት ፕሬዚዳንት አታ ሚልስ እንደገና ለመመረጥ በዝግጅት ላይ ነበሩ። በካካኦ አምራችነቷ የምትታወቀዉ ጋና ለብዙ አመታት በመንግስት ግልበጣ፤በህዝባዊ አመጽና በፖለቲካ አለመረጋጋት ስትታመስ የከረመች አገር ነበርች። የሚያሳዝነዉ ጋና ከብዙ አመታት መራራ ትግል በኋላ በመረጠችዉ የድሞክራሲ ጎዳና ላይ በመጓዝ የምዕራብ አፍሪካ የዲሞክራሲ፤ የሠላምና የመረጋጋት ምልከት መሆኗ እየተነገራላት ባለበት ግዜ ነዉ የእድገቷና የሠላሟ ተምሳሌት የሆኑትን ታላቅ መሪዋን ያጣቸዉ።
ፕሬዚዳንት አታ ሚልስ ባለፈዉ ግንቦት ወር ዋሺንግተን ዲሲ ዉስጥ በተካሄደዉ የአፍርካ አገሮች የምግብ ደህንነት ስብሰባ ላይ ከዘረኛዉ መለስ ዜናዊ ጋር ጎን ለጎን ተቀምጠዉ መታየታቸዉ የሚዘነጋ አይደለም። ሆኖም ዘረኛዉ መለስ ዜናዊ በመኪና ወደ ስብሰባዉ አዳራሽ ሲሄድም ሆነ ስብሰባዉ አዳራሽ ከገባ በኋላ ታላቅ ህዝባዊ ቁጣና ተቃዉሞ ገጥሞታል፤ ይሄዉ የህዝብ ቁጣና ተቃዉሞ አበሳጭቶት ነዉ በዚያዉ ሰሞን ከG8 ስብሰባ በኋላ ቅዳሜ ማምሻዉን ሰሜን አሜሪካ ዉስጥ የሚገኙ ቡችሎቹ ኤምባሲዉ ዉስጥ እራት ደግሰዉ ይመጣል ብለዉ ሲጠባበቁ መጣሁ ወይም ቀረሁ ሳይላቸዉ በቀጥታ ወደ አዲስ አበባ ያቀናዉ።
የጋና ህዝብ ወድዶና ፈልጎ የመረጣቸዉ ፕሬዚዳንት አታ ሚልስ ግን “ከእንኳን ደህና መጡልን” አቀባበል ዉጭ የገጠማቸዉ ምንም አይነት ህዝባዊ ቁጣም ሆነ ተቃዉሞ አልነበረም።
በመለስ ዜናዊና በፕሬዚዳንት አታ ሚልስ መካከል ያለዉ ልዩነት በሁለቱ አገሮች ማለትም በኢትዮጵያና በጋና መካክል ያለዉ ትልቅ ልዩነት ነፅብራቅ ነዉ። ኢትዮጵያ የፖለቲካና የኤኮኖሚ ነፃነት የሌለባት ዘረኝነት የነገሰባትና የሰዉ ልጆች ሰብዓዊ መብቶች የሚረገጥባት አገር ናት። ኢትዮጵያ ዉስጥ በገዢዉ ፓርቲ በህወሃት፤ በመንግስትና በአገሪቱ የኤኮኖሚ ተቋሞች መካክል ምንም ልዩነት የለም። ገዢዉ ፓርቲዉ መንግስት ነዉ ፤ ፓርቲዉ ነጋዴ ነዉ፤ ፓርቲዉ አገር አስተዳዳሪ ነዉ። በእርግጥ ጋናም የመለስ ዜናዊ አይነቱ የዘረኝነት መቅሰፍት ባይነካካትም በአንድ ወቅት ጭቆናና አለመረጋጋት የሰፈነባት የአምባገነኖች መዲና ነበረች።
ሆኖም አገር ዉስጥና ከአገር ዉጭ የሚኖረዉ የጋና ህዝብ ባደረገዉ ረጂምና መራራ የነፃነትና የዲሞክራሲ ትግል ዛሬ ጋና የአፍሪካ የዲሞክራሲ ተምሳሌት ለመሆን በቅታለች። እንደ አዉሮፓዉያን ዘመን አቆጣጠር በ2008 ዓም በተደረገዉ የፕሬዚዳንትነት ምርጫ ፕሬዚዳንት አታ ሚልስ ያሸነፉት እጅግ በጣም ጠባብ በሆነ ዉጤት ነበር። ሆኖም የጋና ህዝብ ዉጤቱን በሠላም ተቀብሎ ወደፊት መጓዝ በመቻሉ አለም የጋናን ህዝብ በሳልነትና አገሪቱ በአጭር ግዜ ዉስጥ የገነባቻቸዉን የዲሞክራሲ ተቋሞች ብቃት አድንቋል።
በአንፃሩ ለጋና ህዝብ ነፃነት ቁልፍ ሚና የተጫወተችዉ አገራችን ኢትዮጵያ ግን ዛሬ ዘርኝነት የነገሳበት፡ የህዝብ መብት የሚረገጥባትና የአፍሪካ የአፈና፤ የእስር፤የስዴትና የሰቆቃ ቋሚ ምልክት ሆናለች። ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያ በዲሞክራሲ ስም የዲሞክራሲ መብቶች የሚረገጡባትና የሚጨፈለቁባት አገር ናት።በአጠቃላይ ዛሬ የምንኖርበት ግዜ የመረጃ ዘመን ተብሎ በሚጠራበት ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ የገዛ አገሩን ሁኔታና የግል ህይወቱን ጭምር በተለመለከተ ምንም አይነት መረጃ እንዳያገኝ ተደርጎ በጨለማ ዉስጥ የሚኖር ህዝብ ሆኗል።
የጋና ህገ መንግስት ፕሬዚዳንቱ በጤና መታወክ ወይም በሌላ ምክንያት ስራዉን መስራት ካልቻለ ማን ተክቶት እንደሚሰራና አገሪቱን አንደሚመራ በግልጽና በማያሻማ መልኩ ያስቀመጠዉ ስለሆነ ፕሬዚዳንቱ ባለፈዉ ማክሰኞ ከዚህ አለም በሞት ሲለዩ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጆን ማሃማ ቃለ መኃላ ፈጽመዉ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆነዋል። በፕሬዚዳንቱ ድንገተኛ ሞት የጋና ህዝብ ታላቅ ኃዘን የተሰማዉ ቢሆንም – ደሞ “ማን ይመጣብን ይሆን” እያለ ግራ አልተጋባም። ጋና ዉስጥ ህዝብ የመረጃ ባለቤት ስለሆነ ፕሬዚዳንት አታ ሚልስ ታመዉ በቆዩበት የአንድ ቀን ግዜ ዉስጥም ቢሆን የፕሬዚዳንቱ መታመም በሚስጢር አልታየዘም።
አገራችን ኢትዮጵያ ዉስጥ ግን መሪ ነኝ ተብዬዉ መለስ ዜናዊ ታምሞ ዉጭ አገር ሄዶ መታከም ከጀመረ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ነዉ የዚህ ዘረኛ ሰዉ መታመም በይፋ ለህዝብ የተነገረዉ። እዚህ ላይ አንድ የሚያሳዝነንና የሚገርመን ነገር ቢኖር ኢትዮጵያን እመራለሁ የሚለዉን ሰዉ መታመም ኢትዮጵያዉያን ለመጀመሪያ ግዜ በአደባባይ የሰሙት ከሌላ የአፍሪካ አገር መሪ ነዉ። የኢትዮጵያ ህገ መንግስት በግልጽ ያላስቀመጠዉና ዛሬ ህዝቡን በከፍተኛ ደረጃ እያወዛገበ ያለዉ ጉዳይ መለስ ዜናዊ የመጨረሻ ትንፋሹን ቢተነፍስ ማን ይተካዋል የሚለዉ ጥያቄ ነዉ። መለስ ዜናዊ ህግ መንግስቱን ሲጽፍ እራሱን እንደ መጀመሪያና እንደመጨረሻ አድርጎ ስላየ ይህንን አስፈላጊ የሆነ የአገር ጉዳይ ሆን ብሎ ዘልሎታል። እንግዲህ የጋናና ኢትዮዮጵያ ልዩነት ይህንን ያክል የሰፋ ነዉ። አዚህ ላይ አንድ ነገር መልሶ መላልሶ ወለል ብሎ ሊታየን ይገባል። የጋና ህዝብ በአጭር ግዜ ዉስጥ እዚህ የሚያስቀና ደረጃ ላይ ሊደርስ የቻለዉ አምርሮ ጨቋኝ መሪዎቹንና ስርአታቸዉን ስለታገለ ነዉና እኛም እነዚህ ዛሬ ተመቻችተዉ የምናያቸዉ ሁኔታዎች ሳያመልጡን የዘረኞችን ስርአት በአንድነት ተነስተን ነገ ሳይሆን ዛሬ መደምሰስ አለብን።
No comments:
Post a Comment