Monday, August 6, 2012

የኢትዮጵያ ሰራዊት ንቅናቄ” የህቡህ እንቅስቃሴ መጀመሩን ፣ የንቅናቄው ተግባር መግለጫ


ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ መስዋዕትነት ታፍራና ተከብራ የኖረች የጥቁር
ህዝቦች የነጻነት ተምሳሌት ነች። የሃገሪቱ የመከላከያ ሃይል በዘመናዊ መልኩ ከተደራጀ በኋላም በተለያዩ የሃገሪቱ መንግስታዊ ሥርዓቶች መመሪያና ትእዛዝ መሰረት የቀደምቶቹን አርአያነት በመከተል ለሃገሪቱ ዳር ድንበርና ነጻነት መከበር የራሱን አኩሪ መስዋእትነት ከፍሏል። ይህ የመከላከያ ሃይል ዳር ድንበር ከማስከበር አልፎም የህዝብ መብት ተገፏል ብሎ ባማነባቸው ወቅቶች ከህዝብ ጎን በመቆም የፖለቲካ የኢኮኖሚ የማህበራዊ ለውጦች በሃገሪቱ ላይ እንዲመጣ የድርሻውን ተወጥቷል።
ይሁንና ተከታታይ መንግስታዊ ሥርአቶች የህዝብንና የመከላካያ ሰራዊቱን መስዋእትነት መና በማስቀረታቸው የሃገራችን ህዝብ በነጻነት ፈንታ ባርነትን፣ በእኩልነት ፈንታ ዘረኝነት፣ በዴሞክራሲ ፋንታ አፈና ነግሶ ህዝባችን በአስከፊ እና በመራራ የህይወት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቋል። ባለንበትም ዘመን ከኢትዮጲያ ህዝብ አብራክ የወጣው የመከላከያ ሠራዊት ይህ ሁኔታ መለወጥ እንዳለበት በማመን ለዓመታት በህቡዑ ሲደራጅ ቆይቷል።
የኢትዮጲያ የመከላከያ፣ የፖሊስ፣ የደህንነት ሀይል በጥቂት የወያኔ ከፍተኛ መኮንኖች እግር ተወርች ተይዞ የወያኔ የማፈኛና የመጨቆኛ መሳሪያ መሆን እንደሌለበት በማመን በቆራጥነት እና በኢትዮጲያዊነት ወኔ ከኢትዮጲያ ህዝብ ጎን ለማሰለፍ ዝግጁቱን ማጠናቀቁን ለወገኖቻችን ስንገልጽ በታለቅ ደስታ ነው።የኢትዮጲያ ህዝብ ሆይ በአንተ ላይ እየደረሰ ያለ መከራ በእኛ በሠራዊቱ ውስጥ በክፉ መልኩ ያለ መሆኑን የምታውቀው ነውና ከጎንህ ለመቆም መወሰናችን እንግዳ ዜና እንደማይሆንብህ እናውቃለን።።
የመከላከያ ሰራዊት ለሃገር ብሄራዊ ጥቅምና ደህንነት ሳይሆን፣ ጥቂት መሪዎች በስልጣን ለመሰንበት ሲሉ በሚፈጥሩት የፖለቲካ መጠቀሚያ ሁኖ፣ ወደ ጎረቤት ሶማሊያ እየተላከ በከንቱ ደሙ እንዲፈስ፣ አስከሬኑ በየመንገዱ እንዲጎተት፣ በየጎዳናውወድቆ መሳቂያና መሳለቂያ እንዲሆንና ቤተሰቦቹ እርማቸውን እንዳያወጡ መሞቱ እንኳን የማይነገርለት አሳዛኝ ሰራዊት ሆኗል። ዘረኛነት ከተጠናወታቸው አምባገነኖች ጋር የተቆራኙ፣ በጥቅምና በክፋት የተሳሰሩ ጥቂቶች እያስገደዱት፣ ከወታደርነት ውጭ ያለው
አማራጭ ጦም-አዳሪነት ብቻ እንደሆነ እያመላከቱት፣ በሃገሪቱ ያሰፈኑትን ድህነትና ስራ አጥነት በማስፈራሪያነት እየተጠቀሙ በማይፈልገውና ትክክል ናቸው ብሎ በማያምንባቸው ግዳጆች ላይ እየተሰማራ በመሰቃየት ላይ ይገኛል።
የወታደሩ ኑሮ እያሽቆለቆለ፤ ቤተሰቡና ራሱን መደገፍ ልጆቹን ማሳደግ የማይችልበት ሁኔታ ላይ ሲደርስ፣ በሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ በላይቤሪያ፣ በሱዳንያ ዘምቶ ከሌሎች አፍሪካ አገሮች ከመጡት ሰራዊት ያነሰ እያገኘ፣ ለሱ የመጣውን ጥቂቶች መሪዎች እየወሰዱበት፣ እሱ በችግር ሲቆራመትና ሲዋረድ፣ መሪዎች ግን በአዲስ አበባና በዋና ዋና ከተማዎች ህንጻዎች እየሰሩ፣ ወድ መኪናዎች እንደሸሚዝ እየለወጡ፣ ልጆቻቸውን በግል ትምህርት ቤቶች በአገርና በውጭ አገር እየላኩ በማስተማር፣ የተንደላቀቀ ኑሮ ሲመሩ በተለያዮ ግንባሮች ሲዋጉ አካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰራዊት አባሎች ግን እንደ
ዕቃ በየትም ተጥለው በሞትና በኑሮ መሃል በበሽታና በችግር ሲሰቃዩ ሁሉም የሚመለከተው ነው። ሰራዊቱ ይህንን ሁሉ መስዋዕትነት ከፍሎም አገሪቱ ብታድግ ኖሮ
እጅግም ባልቆጨው ነበር:: ነገር ግን ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ በታሪክችን ታይቶ በማይታውቅ ሁኔታ በዘር ተከፋፍሎ፣ አንድነቱ ተናግቶ ከዛሬ ከነገ ምን ይመጣ ይሆን
እያለ በስጋት የሚኖርበት ጊዜ ሆኗል::
አስከፊውን የከተማና የገጠር ህዝብ የቀን ተቀን ህይወት በመሸፈን በመጋረጃነት ከተገነቡ የከፍተኛ ሙስናና ዘረፋ ምንጭ ከሆኑ የተወሰኑ መንገዶችና ህንጻዎች በስተቀር ኢትዮጵያ በዓለም ውስጥ የመጨረሻ ድሃ ከሚባሉት ሃገሮች አንዷ ከመሆን አልተለወጠችም። ይህንን ሃቅ ከሕዝብ ደብቆ ለማቆየት ባለመቻሉ የሕዝቡና የአገሪቱ ድህነት፣ የሕዝቡ እርዛትና ጉስቁልና በገሃድ ወጥቷል። ምንም ዓይነት ፕሮፓጋንዳ
የሕዝቡን ምሬትና ብሶት ሊቀንሰው አልቻለም:: በከተማ የምናያቸው ህንጻዎች ከሕዝብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገዶች በተዘረፈ ሃብት የተሰሩ፣ መንገዶቹ ደግሞ ከውጭ ዓለም በብድርና በስጦታ በተገኘ ገንዘብ የተሰሩ ሲሆኑ፣ ግማሹ ገንዘብ የተወሰኑ የመንግሰት ባለሰልጣኖችና የግል ኩባንያዎች ኪስ ውስጥ የገባ ገንዘብ ነው። ይህም ከህዝብ ተዘርፎ የተሸሸገው ሀብት መረጃ በእጃችን ይገኛል።
ገበሬው የበሬ ግምባር በምታክል መሬት አያረሰ፣ ራሱንም ቤተሰቡን መቀለብ
ባልቻለበት ጊዜ፣ ኢትዮጵያም ተደጋጋሚ "ድርቅ" ደርሶባት፤ ሕዝብ በችጋር በሚያልቅበት ጊዜ፣ ኢትዮጵያችን የዘውትር የምግብ ለማኝ ሆና በምትታወቅበት በአሁኑ ጊዜ፤ የኢትዮጵያ ለም መሬቶች በነጻ ከማደል ልዩነት በሌለውና አለምን ባስደመመ ርካሽ ክፍያ ለአረብ፣ ለህንድና ለቻይና ከበርቴዎች እየተቸበቸቡ ናቸው። መሬት
ለባእዳን በርካሽ መቸብቸቡ ሳይበቃ፣ ባእዳኑ የሚያመርቱት የግብርና ምርት በሙሉ ወደውጭ የሚላክ እንጂ ለአገራችን ሕዝብ እንዳይተርፍ የሃገራችን ሳይሆን፣ የባእዳን ጉዳይ አስፈጻሚ የሆኑት የሃገሪቱ ባለስልጣናት ከባእዳኑ ጋር ውለታ የተፈራረሙበት
ጉዳይ ነው::
በዚህ አሳሳቢና ወሳኝ ወቅት የአገሪቱን ህልውና አስከብሮ፣ ህዝቡን ከእርስ በእርስ እልቂት ለማዳንና ኢትዮጵያ ወደ ዲሞክራሲያዊ ባህልና ዘመን እንድትሸጋገር ለማድረግ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአገርና በውጭ አገር በመደራጀት እየታገለ መሆኑን በመገንዘብ ሰራዊቱ የዚሁ ትግል አባል ለመሆን ወስኖአል።


የኢትዮጵያ መለዮ ለባሾች ለፍትህ፣ ለነጻነት፣ ለአንድነትና ለዲሞክራሲ የቆሙ ሃይሎችን አይወጉም። የኢትዮጵያ የጦር ሃይሎች አባላት የእዚህ ዘረኛ አስከፊ ከፋፋይና በዝባዥ መንግስት መሳሪያ አይሆንም። በዚሁም ውሳኔያቸው ከአንድነት፣ ከዴሞክራሲና ከሰላም ሃይሎች ጋር ተሰልፈዋል። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ሃገሪቱ እንደምትፈልጋቸውም ተገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ መለዮ ለባሾች ትግሉን የሚያራምዱበት ዝርዝር እንቅስቃሴዎች በንቅናቄው
ማዕከላዊ ኮሚቴ እየተነደፈ ለአፈጻጸም ለአባላት ይደርሳሉ። የኢትዮጵያ መለዮ ለባሾች ድምጻቸውን የሚያሰሙበትን እና ለነጻነት ለአንድነትና ለፍትህ የሚታገሉበት አዲስ መድረክ በመፈጠሩ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ከፍተኛ እመርታ ማድረጉንና አዲስ ምእራፍ ውስጥ መሸጋገሩን ያሳያል። ኢትዮጵያም እንደሌላው የአለም ሕዝቦች ትግልና መስዋዕትነት፤ አምባገነንነትን አሽቀንጥራ ለነጻነት፣ ለፍትህ እና ለእኩልነት በምታደርገው ትግል የኢትዮጲያ ሠራዊት ወሳኝ እና ግንባር ቀደም ሚና ለመጫወት መወሰኑን የጦር ሀይሎች አባላት በታላቅ ኩራት ዜናውን ለሕዝቡ ያበስራሉ።
የኢትዮጵያ መለዮ ለባሽ፣ የህዝብ አገልጋይ የሕዝብ ጥቅም ጠባቂ እንጂ የአምባገነኖች ሃብት ማካበቺያና የስልጣን ጥቅም ማርኪያ መሳሪያ አይሆንም። ይህ እምነቱ በወታደርነት ሲመለመል ለኢትዮጵያ ሕዝብ የገባው ቃል ኪዳን ነው። ይህ የዛሬው
ውሳኔ የቃል ኪዳኑ ተሃድሶ ነው። ሌላው በተግባር ይታያል:: 

የነኢሠን ማዕከላዊ ኮሚቴ::
ሐምሌ 2004

To read the  PDF format of the above text. follow the link ;
http://www.abetokichaw.com/wp-content/uploads/2012/08/ነኢስን-ሐምሌ28Final.pdf

No comments:

Post a Comment