Saturday, September 1, 2012

የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ህትመት ተቋረጠ  • የጋዜጠኞቹ የአቶ መለስን ቀብር እንዳይዘግቡ ተከልክለዋል
  •  ጋዜጣዋ ለአንባቢያን የምትደርስባቸው መንገዶች እየተፈለጉ ነው
በአንድነት ለዲሞክራሲ ለፍትህ ፓርቲ /አንድነት/ ኢዲቶሪያል ቦርድ ሥር የምትታተመው ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ በብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት እንቢተኝነት ህትመቷ ተቋረጠ፡፡
ጋዜጣው ስለ አቶ መለስ የዘገበውን በማተማችን በርካታ ተቃውሞ ገጥሞናል በማለት የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ማናጅሜንት ጋዜጣውን ላለማተም መወሰኑን የማተሚያ ቤቱ ማርክቲንግ ማናጀር አቶ መኮንን አበራ ለፍኖት ነፃነት ጋዜጣ ገልፀዋል፡፡
አቶ መኮንን ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት “በዚህ ወቅት እንዲህ ዓይነት ጋዜጣ ታትሞ በመሰራጨቱ ከፍተኛ ወቀሳን አስከትሏል፡፡ በዚሁ መሠረት የድርጅቱ ማናጅሜንት ተሰብስቦ ከእንግዲህ ጋዜጣውን ላለማተም ወስኖአል” ብለዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ነሐሴ 25 ቀን 2004 ዓ.ም ሊታተም የነበረው የጋዜጣው ልዩ እትም ሳይታተም ቀርቷል፡፡ ዝግጅት ክፍሉ አስፈላጊውን ዝግጅቱን አጠናቆ 18,640 ጋዜጣ ለማሳተም ማተሚያ ቤቱ ዋጋ እንዲያወጣለት ቢጠይቅም ማተሚያ ቤቱ እንቢተኛ በመሆኑ ጋዜጣው ሳይታተም ተርቷል፡፡
ጋዜጣው ስለመቋረጡና ወደ ፊት ምን እንደታሰበ የጋዜጣውን ኤዲቶሪያል ቦርድ ሰብሳቢ አቶ በላይ ፍቃዱ በሰጡት መልስ “የብርሃንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት በነበረን ስምምነት ጋዜጣውን ሲያትምልን ቆይቷል፡፡ ከዚህ በፊት ላለማተም አንገራግሮ የነበረ ቢሆንም ተነጋግረን ህትመቱ መቀጠሉ ይታወቃል፡፡ አሁን ደግሞ ከአቶ መለስ ሞት ጋር በተያያዘ በዚህ ወቅት እንዲህ ዓይነት ጋዜጣ በመታተሙ ተወቅሰንበታል በማለት እንቢ ብሏል፡፡ ማተሚያ ቤቱ በማይመለከተው ሥራ ውስጥ እየገባ የጋዜጦችን ህትመት ማስተጓጐሉ አሳዝኖናል፡፡ ጋዜጣችን እንደ አንድ ነፃ ጋዜጣ የሚያገለግል ቢሆንም የፓርቲ ልሣን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ መሞታቸውን ተከትሎ ገዢው ፓርቲ የሚፈፅመውን ተገቢ ያልሆነ ፕሮፓጋንዳ መመከትና ትክክለኛውን መንገድ እንዲከተል መተቸት ነበረብን፡፡ ትክክል ነን ብለን የምናምንበትን አማራጭ ለገዢው ፓርቲም ይሁን ለህዝብ ማሳወቅ ስለነበረብን አሳይተናል፡፡ ይህ በክፋት መታሰብ የለበትም” ሲሉ መልሰዋል፡፡
በመቀጠልም አቶ በላይ ሲናገሩ “ብርሃንና ሠላም አንድ የመንግስት ማተሚያ ቤት ነው፡፡ ከፖለቲካ ወገንተኝነት በፀዳ አመለካከት ሥራውን በገለልተኝነት መሥራት አለበት፡፡ ሲፈልግ አትማለሁ ሲፈልግ ደግሞ የገዢውን ፓርቲ ህፀፅ ከተቻችሁ አላትምም እያለ የፓርቲውን ትግል ለማደናቀፍ መሞከሩ ተገቢ አይደለም፡፡ ይህ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ህገመንግስታዊ መብትን መጣስ ነው፡፡ ስለዚህ የብርሃንና ሠላም ማተሚያ ቤት ማናጅሜንት ኃላፊነቱንና ተግባሩን በአግባቡ ተረድቶ ውሳኔውን እንደገና ሊያጤነው ይገባል የሚል ጥሪዬን ማቅረብ እወዳለሁ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሌላ ምን አማራጭ አላችሁ ብለን የጠየቅናቸው የኢዲቶሪያል ቦርድ ሰብሳቢው አቶ በላይ ሲመልሱ “የመጀመሪያው ምርጫችን ማተሚያ ቤቱ ጋዜጣችንን እንዲያትም እስከህግ አግባብ የሚዘልቅ ጥረት እናደርገደለን” ካሉ በኋላ “ዘላቂው ግባችን ግን ፓርቲው የራሱ ማተሚያ እንዲኖረው ማድረግ ነው፡፡ ትግሉን ገፍቶ እንዲሄድና አሁን በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የአፈና ስርዓት በአቅም ለመታገል ከተፈለገ የራሳችን ማተሚያ ማሽን መግዛት ብቸኛ አማራጭ ነው፡፡ ስለዚህ በአገር ቤትም ይሁን በውጭ አገር የሚኖሩ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ድጋፍ አድርገው ፓርቲው የራሱ ማተሚያ እንዲኖረው የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ አሁን ለጊዜው ግን ዝግጅታችን እንዳይቋረጥ ጋዜጣችንን ለአንባቢያን የምናቀርብበትን አማራጭ እያጠናን ነው” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል፡፡ በየሳምንቱ ማክሰኞ በመደበኛ ለአንባቢያን የምትቀርበው ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ሰሞኑን በልዩ እትም ጭምር በተከታታይ በቀድሞ የኢፌዲሪ ጠ/ሚኒስትር መለስ ሞትና በቀጣዩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አቅጣጫ ዙሪያ ያተኮሩ እትሞችን ለገበያ በማዋል፣ በመንግስት መገናኛ ብዙሀን ከሚቀርበው ፕሮፓጋንዳ የተለየ መረጃ ለአንባብያን በማድረሷ ከፍተኛ አንባቢ አግኝታ ነበር፡፡ ሆኖም ማንነታቸው የማይታወቅ ግለሰቦች የፍኖተ ነፃነት አዘጋጆችን በማስፈራራት ጋዜጣው ስለ አቶ መለስ ከአሁን በኋላ እንዳይዘግቡ ማስፈራሪያና ማስጠንቀቂያ እየደረሰባቸው ሲሆን የተወሰኑት ላይም በአካል ወከባና ማስፈራሪያ እየደረሳቸው ነው፡፡
በተመሳሳይ ዜና የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዘጋቢዎች የአቶ መለስ ዜናዊን የቀብር ሥነ ሥርዓት እንዳይዘግቡ ተከለከሉ፡፡ ሥነ ስርዓቱን ለመዘገብ ለእያንዳንዱ ጋዜጠኛ የመንቀሳቀሻ ባጅ የተሰጠ ቢሆንም የጋዜጣው ዘጋቢዎች ባጁ እንዲሰጣቸው የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤትን ቢጠይቁም መስሪያ ቤቱ ፍቃደኛ ሊሆን አልቻለም፡፡
በስልክም በአካል በመሄድ በዘጋቢዎቹ ጥያቄ የቀረበላቸው የመንግስት ኮሚኒኬሽን ሚዲያ ግንኙነት ክፍል ሃላፊዎች “ባጅ አልቋል” በሚል ምክንያት እንቢታን መርጠዋል፡፡ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ለዝግጅት ክፍሉ የሚዲያ ጥቆማ የማይልክ በመሆኑ የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል የመንግስትን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ለመዘገብ መቸገሩን ዝግጅት ክፍሉ ለመንግስት ኮሚኒኬሽን አቤቱታ ቢያቀርብ እስከ አሁን መፍትሄ ማግኘት አልቻለም፡፡

No comments:

Post a Comment