Tuesday, September 11, 2012

ኢቲቪ የፈጠረው መለስ ዜናዊብዙ ሰዎች የህወሃት ዋነኛው ማሰቢያ አካል መለስ ዜናዊ ነበር ብለው ያምናሉ። መለስ ዜናዊ የሌለበት ህወሃት ምሶሶ እንደሌለው ጎጆ ነው ብለውም የሚያስቡ ብዙ ናቸው። ከሰሞኑ በአምላኪዎቹ ዘንድ እዚህም እዚያም የሚታየው ሃዘን መሰል ነገር ከዚህ እምነት የመነጨ ነው። አንዳንዶቹ ቀኝ እጃችንን ተቆረጥን ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው አንድ ዓይናችንን አጥተናል ብለዋል። የሞተው መለስ ዜናዊ ባለፉት ሃያ አንድ ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያዊያን ደህና አድርገው የሚያውቁት መለስ ዜናዊ ሳይሆን ሌላ ኢትዮጵያዊያን የማያውቁትደጉና ርህሩሁ” መለስ ዜናዊ ነው። ይህን ኢትዮጵያዊያን የማያውቁትን መለስ ዜናዊን ተማምነው ዜጎች ጎዳና ላይ እስኪወጡ ያደረሰ ደግነቱ የተመሰከረለት ሰው ከየት እንደመጣ ኢቲቭ ብቻ ያውቃል።
ሰሞኑን የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ኢትዮጵያ የማታውቀውን ሌላ “ደግና ሩህሩህ” መለስ ዜናዊን ፈጥረው ህዝቡ ያመልከው ዘንድ ዘመቻ ጀምረዋል።
ኢትዮጵያዊያን የሚያውቁት መለስ ዜናዊ ግን ብዙ ውሸቶችን የፈጠረና ውሸት በዚያች አገር ያባዛ እና ውሸትን የድርጅቱ ባህል ያደረገውን መለስ ዜናዊን ነው። ይህ ግለሰብ ውሸት አገርን የሚያጠፋ ነውር ነገር መሆኑን ሳይረዳ አልፏል።ተከታዮቹም እውነቱን ከውሸት ለመለየት ተክለሰውነታቸው የሚፈቅድላቸው አይደሉም። መለስ ዜናዊ በእንግዶች ፊት “ከሰማይ በታች የማንደራደርበት ነገር የለም የዛሬዋን ብቻ እለፉኝ” ብሎ ተማጽኖ ሲያበቃ ነገ ሌላ አዲስ ሁኖ ብቅ የሚል፤ ትላንት እኮ እንዲህ ብለህ ነበር ሲባል ፈጽሞ ለመካድ ትንሽም ቢሆን የማያንገራግር ግለሰብ ነበር። እኛ የምናውቀው መለስ ዜናዊ እውነትን አዋርዶ የአገሪቷን ወግና ባህል ያጠፋውን እንጂ ኢቲቭ እንደሚለው ለእውነትና ለኢትዮጵያ ቁሟል የሚባለውን አዲሱን መለስ ዜናዊን አይደለም። አምላኪዎቹ እንደሚሉት”ደጉና ሩህሩሁ እንዲሁም ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን ያከበረው” መለስ ዜናዊ አልተፈጠረም።የሌለውን መለስ ዜናዊን ፈጥሮ ቅጥ ያጣ ሃዘን አውጆ አገሪቷን ሃዘንተኛ ማድረግ “ትግራይን ነጻ እናወጣለን“ ብለው የተነሱ ቡድኖች የቆሙለትም የሚሞቱለትም የውሸታቸው አንዱ ገጽታ ነው።
ህወሃት ውስጥ የተሰባሰቡ ግለሰቦች ውሸት ዋነኛ ባህላቸው ነው። ለምሳሌ መለስ ዜናዊ ታሞ ሳለ የለም ደህና ነው ሲሉ ዋሽተው ነበር።ሰውየው ከሞተ ብዙ ቀናት ያለፉት ቢሆንም ከእንቁጣጣሽ በፊት በጣም ፈጥኖ ወደ ሥራው ይመለሳል ብለውም ህዝቡን ዋሽተውት ነበር።የሰውየውን መታመም ለምን እውነቱን አልተናገራችሁም ሲባሉ “ይሄማ ባህላችን” ነው ብሎ በረከት ስምኦን መናገሩን ሰምተናል። ውሸት የድርጅታቸው ባህል እንዲሆን ያደረገው ሟቹ መለስ ዜናዊ ነው። አሁን መለስ ዜናዊ ቢያልፍም ውሸትን ባህላቸው ያደረጉ መለስ ዜናዊ ጠፍጥፎ የሠራቸው ግለሰቦች ዛሬም በአገሪቷ ራስ ላይ ተቀምጠዋል። እነዚህም ቡድኖች ከውሸታቸው ወጥተው እውነት ወዳለበት ወደ ብርሃን ይመጣሉ ብሎ መጠበቅ ለራስ መዋሸት ብቻ ነው። እነዚህ ቡድኖች ከነ ነውራቸው መሞትን የመምረጥ ስብእና ያላቸው በመሆናቸው አገሪቷ እስከምትጠፋ ድረስ ይተጋሉ እንጂ ከእውነት ጋር ታርቀው ከህዝብ ጋር ይኖራሉ ማለት አይቻልም።
ትግራይን ነጻ እናወጣለን ብለው የተነሱ ቡድኖች ነውር ብዙ ነው። ውሸታም ብቻ ሳይሆኑ ዝሪፊያም አንዱ ገጻቸው ነው።ባለፉት ሃያ አንድ ዓመትታ ውስጥ ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከአገሪቷ ወጥቶ በውጭ አገራት ባንኮች ውስጥ መደበቁን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ነግሮናል። በዚህ ዝርፊያ ውስጥ ከሟቹ መለስ ዜናዊ እና ከባለቤቱ አዜብ መስፍን ጀምሮ ወደ ታች ያሉ የህወሃት አባላትና ከድርጅቱ ጋር በተለያየ መንገድ የተሳሰሩ ለአገርና ለወገን ደንታ የሌላቸው ገለሰቦች አሉበት። መለስ ዜናዊ እጁ ባይኖርበት ኑሮ ይሄ ጉዳይ ተጣርቶ እውነቱ ለዚያ ድሃ ህዝብ እንዲገለጥለት ያደርግ ነበር። ግን ምን ያደርጋል አለመታደል ሁኖ ኢትዮጵያን እመራለሁ ብሎ የተቀመጠው ግለሰብ የዚያ ዝሪፊያ መሪ ሁኖ ተገኝቷል። የመለስ ዜናዊ አምላኪዎች ሊጠይቁ የሚገባቸው ሁነኛ ጥያቄ የህዳሴውን ግድብ ያህል ሶስት ሊሰራ የሚችል ገንዘብ ከአገሪቷ ወጥቶ በውጭ አገራት ባንኮች ውስጥ ሲጠራቀም የአገሪቷ መሪ እንደምን ሁኖ ዝም ሊል ቻለ ብለው ነው።መልሱ ግን አገሪቷን እመራለሁ ብሎ በአገሪቷ ራስ ላይ ተቆናጦ የነበረው ግለሰብ ለአገሩና ለሚመራው ወገን ቅንጣት ታክል ፍቅር የሌለው ስለሆነ ይህን የመሰለውን ዝሪፊያ በዝምታ አልፎታል።ለዚህ ጥያቄ ህወሃቶች ምን መልስ እንዳለቸው አናውቅም። እኛ የምናውቀው መለሰ ዜናዊ ግን እንዲህ ያሉ ዝርፊያዎችን ያበረታታና የመራ መሆኑን እንጂ ከሞተ በኋላ በረከት ስምኦን የፈጠረውን ለአገሩና ለህዝቡ “ታማኝ” ሁኖ የኖረውን መለስ ዜናዊን አይደለም።
ትግራይን ነጻ እናወጣለን ብለው የተነሱ ቡድኖች ነውር ውሸት እና ዝርፊያ ብቻ አይደለም። ሌላ የከፋ ነውርም አሏቸው። ጥላቻና ጭካኔ።ይሄ ድርጅት አንድን ህዝብ ጠላት ብሎ የጻፈ ነው። አማራ የትግራይ ህዝብ ቀንደኛ ጠላት ነው ብሎ የጻፈ፤ ያስተማረ እና የሚያምን ድርጅት ነው።ይህ ቡድን ራሱን “ወርቅ” ብሎ የሚጠራ ሌሎችን ግን አህያ ብሎ እስከ መሳደብና ማዋረድ የሚደረስ ቡድን ነው። ይህን በመሰለው ጥላቻ የታወረው ቡድን አማርኛ ቋንቋ የሚናገሩ ንጹሃን ዜጎችን ገድሎ በየገደሉ እንደከተተ የምናውቀው እውነት ነው። የለም እኛ የጎንደር ክፍለ አገር ነዋሪዎች ነን ባሉት ወልቃይቶች ላይ የፈጸሙትን ዘር ማጥፋትም የምንረሳው አይደለም። እነዚህ ጨካኞች የጭካኔያቸው መገለጫ እጅግ በጣም ብዙ ነው።በእነዚህ ቡድኖች ከነ ህይወታቸው የተቀበሩ፤ በእሳት ተቃጥለው የሞቱ፤ ብልቶቻቸው ተቀጥቅጠው ዘር እንዳያፈሩ የተደረጉ ዜጎች በዚያች አገር አሉ።ይሄ ሁሉ በሟቹ መለስ ዜናዊ መሪነት የተካሄደ ነው። ይህን የመሰለ ጭካኔ በዜጎች ላይ እንዲፈጸም ትእዛዝ ሲሰጥ የነበረው መለስ ዜናዊን “ደግና ሩህሩህ”  ነበር ማለት ጅብ የማያውቁት አገር ሂዶ ቁርበት አንጥፉልኝ አለ የተባለውን ተረት ያስታውሰናል።
ለማንኛውም የነጻነት ጎህ ቀዶ እውነት የሚነገርበት ዘመን ሲመጣ የተሰወረው ሁሉ ይገለጣል። ዛሬ በኢቲቪ“ደግና ሩህሩህ” ተብሎ የሚለቀስለት መለስ ዜናዊ  እውነተኛ ማንነቱ ይነገራል። ትውልዱም መለስ ዜናዊ ማን እንደሆነ ያውቃል። አገራችንም በኢቲቭ ብቻ አትቀርም። በቅርብ ግዜ ኢትዮጵያችን ብዙ ቴሌቭዥን ጣቢያዎች ይኖሯታል፤ ብዙ ጋዜጦች፤ ብዙ ሬዲዮኖች፤ ብዙ ስለ እውነት የሚቆሙ መገናኛ ብዙሃን ይኖሯታል። ያን ግዜ የተከደነው ይከፈታል፤ የተሰወረው ይገለጣል። ወደ ፊትም ሳይገለጥ ተከድኖ የሚቀር ነገር አይኖርም። ያን ግዜ ኢትዮጵያችን እውነት ብቻ የሚከብርባት፤ ውሸትና ውሸተኞች ግን ቦታ የሚያጡበት ዘመን ይሆናል።ያ እውነት እንዲሆን ግንቦት ሰባት የፍትህ፤ የነጻነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ የጀመረውን ሁለገብ ትግል አጠናክሮ ይቀጥላል እንጂ አያፈገፍግም።
በመጨረሻም በኢትዮጵያችን ውስጥ ውሸት መንገሱ፤ ዝሪፊያ መስፋፋቱ እና ጨካኞች በትረ ስልጣኑን ይዘው አገራችንን የሚያዋርዷትን ዘረኞች ከምር ለመታገል የምትፈልጉ ወገኖች ትግሉን እንድትቀላቀሉ አሁንም ጥሪያችንን እናቀርባለን። ለራሱ ክብር የሚሰጥ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለፍትህ፤ለእኩልነት እና ለነጻነት ዘብ ይቆማል። ይታገላል። ስለዚህ ወገኖቻችን ኑና  በተጀመረው ትግል ውስጥ ተቀላቀሉ ብለን ደግመን ደጋግመን እንጠራችኋለን።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
source . http://www.ginbot7.org/2012/09/07/ኢቲቪ-የፈጠረው-መለስ-ዜናዊ/

No comments:

Post a Comment