Sunday, September 23, 2012

ትንሽ ድጋፍ ለአቶ ሀይለማርያም – ደረጀ ሀብተወልድ-ሆላንድ


ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ከአቶ መለስ የተረከቧት ኢትዮጵያ፤ እርሳቸው  ቃለ-ምሕላ ከፈጸሙ በሁዋላ እንዳሉት ወደ ተስፋ ምድርነት ለመቀየር ሩብ ጉዳይ የቀራት ኢትዮጵያ ሳትሆን፤ በውድቀት አፋፍ እያጣጣረች የምትገኝ ኢትዮጵያ ናት።
በፖለቲካው መስክ በወንድማማቾቹ ኢትዮጵያውያን መካከል የቆመው የልዩነት አጥር እንደ ሰናዖር ግንብ ቋንቋችንን ደበላልቆት መደማመጥ ባልቻልንበት ሁኔታ ነው አቶ መለስ ያለፉት።
በኢኮኖሚው መስክ ጥቂት ሰማይ የነኩ ከበርቴዎች በተፈጠሩበትና ብዙ ድሆች እንደ አሸን በፈሉበት ጊዜ ነው አቶ መለስ የሞቱት።
በማህበራዊው ዘርፍ የፍትሕ ሥርዓቱ የአንድ ፓርቲ መሳሪያ ሆኖ ተቃዋሚዎችን ማጥቂያ በሆነበትና ከኢትዮጵያ ምድር ጨርሶ ፍትሕ በጠፋበት፤ በትምህርቱ መስክ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሩቃን ሥራ አጥተው ድንጋይ በማንጠፍ ሥራ በተሰማሩበት ወቅት ነው አቶ መለስ እስከወዲያኛው ያሸለቡት። በሌሎችም ዘርፎች አቶ ሀይለማርያም የተረከቧት ኢትዮጵያ የተዘፈቀችበት ችግር፤ ከዚህ ቢብስ እንጂ የሚሻል አይደለም።
ይህ ማለት አቶ ሀይለማርያም በብዙ ዘርፎች ብዙ ፈተናዎች ተጋርጠውባቸዋል ማለት ነው።አዎ! በእውነት እንናገር ካልን፤በአቶ ሀይለማርያም ፊት፦ እንደ ጎልያድ የገዘፉ በርካታ ችግሮች ቆመውባቸዋል።
ይሁንና የድሉን ምስጢር አውቀው በትክክለኛው መስመር ከሄዱ፤ እነዚህን <ጎልያዶች>(ችግሮች) ሊያሰኝፉዋቸው ይችላሉ።
ጎልያድን የማሸነፊያው ዋነኛ የድል ምሥጢር ደግሞ፤ ራስን ሆኖ ወደ ፍልሚያው መግባት ነው። መጽሐፉን ያስታውሱ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር!
! ዳዊት ጎልያድን እንዲገጥም ሲላክ የንጉሥ ሳዖልን ካባና ሰይፍ ነበር ያለበሱት። ሆኖም ልኩ አልሆነም።ካባውም ሰፋው፣ሰይፉም መሬት ለመሬት ተጎተተ። በዚያ መልኩ ወደ ጎልያድ ቢሄድ ኖሮ የሚጠብቀው ዕድል ሽንፈት ነበር።ዳዊት ግን -የንጉሥ ካባና ሰይፍ ስለሆነ ብቻ ፤ልኩ ያልሆነን ትጥቅ ታጥቆ ወደ ፍልሚያው መግባት አልፈለገም።ለዚህም ነው የሳዖልን ካባና ሰይፍ አውልቆ በመጣል ፦”ወንጭፌን አምጡልኝ!”ያለው።እናም ወንጭፉን አነገተ፤ጠጠር በኮሮጆው ጨመረ። በግ ጠባቂው ዳዊት ራሱን ሆነ። የሚያውቀውንና የተለማመደውን ወንጭፍና ኮሮጆ አንግቶ ጎልያድን ገጠመ።አሸነፈም።
ይህን ነገር ያነሳሁት አቶ ሀይለማርያም  ከሹመታቸው በሁዋላ ባደረጉት ንግግር፤ በአቶ መለስ መስመር ከመሄድ ውጪ ሌላ መንገድ እንደሌለ በተደጋጋሚ በአጽንኦት ሲገልጹ በመስማቴ ነው።የአቶ መለስ መስመር ባለፉት 21 ዓመታት የ ኢትዮጵያን ችግሮች(ጎልያዶች) አላሸነፈም። እንዲያውም ይበልጥ አግዝፏቸዋል። በዚህ ተሸናፊ መስመር ለመቀጠል መወሰን፤ በሳዖል ካባና ሰይፍ ጎልያድን ለመግጠም እንደመዘጋጀት ነው። የዚህ ውጤት ደግሞ ያለ ጥርጥር ሽንፈት እንደሚሆን ለመተንበይ ነቢይነት ቅባት አይጠይቅም።

ስለዚህ አቶ ሀይለማርያም ሆይ! በአቶ መለስ ካፖርት ውስጥ ለመግባት አይሞክሩ። የራስዎን ጫማ ይጫሙ። ምንም <ኢህአዴግ> የሚባል የጋራ ማዕቀፍ ቢኖራችሁም፤እርስዎ ሀይለማርያም እንጂ መለስን አይደሉም።በዚህ ምድር ላይ እርስዎን የመሰለ ሰው ከዚህ በፊት አልተፈጠረም፤ከዚህ በሁዋላም አይኖርም! ይህም የአምላክ ልዩ ሥራ ነው። አምላክ የሰጠዎትን ይህን ውብ የራስን ማንነት፤ሌላን ለመምሰል በመታተር አያጥፉት።

No comments:

Post a Comment