Friday, July 20, 2012

የጠ/ሚ መለስ ህመም ማነጋገሩን ቀጥሏል። ሪፖርታዥ (ደረጀ ሀብተወልድ፦ኢሳት)


ላለፉት 21 ዓመታት በስልጣን የቆዩት መለስ ዜናዊ፤ የዛሬ ሁለት ወር የቡድን ሀያ አገሮች በዋሽንግተን ዲሲ የሬጋን ህንፃ ውስጥ ባደረጉት ስብሰባ ላይ ተገኝተው ገለፃ ሲያደርጉ ከጋዜጠኛPM Meles Zenawiአበበ ገላው ተቃውሞ ባጋጠማቸው ማግስት ያደረባቸውን ህመም ተከትሎ፤ ከሥራ ገበታቸው ላይ ከጠፉ በትንሹ ጥቂት የማይባሉ ጊዜያት አልፈዋል።
የአቶ መለስን መታመም ከሁሉ ቀድሞ ከሳምንታት በፊት የዘገበው ኢሳት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጠና ታመው በቤልጂየም-ብራሰልስ ሴንት ሉክ ሆስፒታል ውስጥ ህክምና እየተከታተሉ መሆናቸውን ይፋ አደረገ።
በማግስቱ በዋልድባ ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክትና በአዲሱ ቴሌኮም ህግ ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የኮሙኒኬሽን ም-ሚኒስትሩ አቶ ሽመልስ ከማል፤ ከጋዜጠኞች ፦”መለስ ታመዋል ይባላል” በማለት ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሙሉ ጤንነት እንደወትሮው ሥራቸውን እያከናወኑ እንደሚገኙ በመግለጽ፤ “ታመዋል የሚለው የኢሳት ወሬ ነው” አሉ።
ኢሳትም፦ በአቶ መለስ የተያዙ በርካታ ፕሮግራሞች እየተሰረዙ መሆናቸውን መረጃዎችን በመፈልፈል ይፋ ማድረጉን ቀጠለ።
አቶ ሽመልስን ጨምሮ ሌሎች ባለስልጣኖች ደግሞ ፦”አቶ መለስ አልታመሙም፤ጤነኛ ናቸው” በማለት መከላከላቸውን ቀጠሉ።
በተለይ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ አንድ ዲፕሎማት ለፎርቹን ጋዜጣ፤መለስ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ እና በሚዲያ ከስተው የታዩትም ፤መክሳቱን ፈልገው “ዳይት” ላይ ስለሆኑ ነው” ማለታቸው፤ ብዙዎችን ፈገግ አሰኘ።
እንዲህ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት የአቶ መለስን መታመም በምስጢር በያዙበት ሁኔታ ነው 19ኛ የ አፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ በአዲስ አበባ የተጀመረው።
እናም…ስብሰባውን በንግግር ይከፍታሉ ተብለው የተጠበቁት አቶ መለስ የውሀ ሽታ ሆነው በመቅረታቸው፤ በምትካቸው የሴኔጋሉ ፕሬዚዳንት በንግግር ሊከፍቱ ወደ መድረክ ወጡ።
ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል ለተናጋሪዎች ወደተዘጋጀው ስፍራ ብቻቸውን ካመሩ በሁዋላ ፦” ይህን ስብሰባ በንግግር መክፈት የነበረባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ነበሩ፡፤ በህመም ምክኒያት ሊገኙ ስላልቻሉ እኔ ለመክፈት ተገድጃለሁ። መለስ በቶሎ ተሽሏቸው ያገግሙ ዘንድ እመኛለሁ” በማለት የጓዳውን በሰገነት አወጁት።
የአቶ መለስ መታመም ምስጢርነት እዚህ ላይ አከተመ።በኢህአዴግ ሳይሆን በሴኔጋል ፕሬዚዳንት ግልጽነት።
ይህ እውነታ አደባባይ በዋለ በማግስቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ፦”መለስ፤ማናቸውም ሰው እንደሚታመም ትንሽ አሟቸው እየታከሙ ነው። በቅርቡ ህክምናቸውን ጨርሰው ይመለሳሉ” በማለት ለመጀመሪያ ጊዜ የአቶ መለስን መታመም ለመናገር ተገደዱ።
ከዚያም አንዳንድ የአውሮፓ ብዙሀን መገናኛዎች ምንጮቻቸውን በመጥቀስ የመለስ ጤንነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሆነ መዘገብ ጀመሩ።
በማስከተልም የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ በረከት ስምዖን ለውጪ ሚዲያዎች ፦”መለስ ሆስፒታል ተኝተው ህክምና እየተከታተሉ እንደሚገኙ፤ሆኖም ህይወታቸው አስጊ ደረጃ ላይ ይገኛል የተባለው ስህተት መሆኑንና በደህና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ “ገለጹ።
የአገር ውስጥ ጋዜጠኞች ፦’መለስ ታመዋል የሚባለው እውነት ነወይ?” ብለው ከቀናት በፊት ሲጠይቋቸው፤” ይህ ኢሳት ያናፈሰው የውሸት ወሬ ነው” በማለት ምላሽ የሰጡት የኮሙኒኬሽን ፅህፈት ቤት ሚኒስትሮች፤ ለነ ቢቢሲና ለነ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ፦”መለስ ታመው ሆስፒታል ናቸው”እያሉ መግለጫ ሰጡ።
የአገር ውስጥ ሚዲያዎችም በራሳቸው ጉዳይ የውጪ ሚዲያዎችን እየጠቀሱ መዘገቡን ቀጠሉ።
የኢህአዴግ ልሳን የሆነውና ከሁለት ወራት በፊት፦”ኢሳያስ አፈወርቄ እጅግ በጠና ታመዋል”( Isayas Afeworki is terminally ill) የሚል ሰበር ዜና ያቀረበው አይጋ ፎረምም፤ዛሬ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ፦”መለስ ሆስፒታል ውስጥ ናቸው፣ መለስ በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ” በማለት ዘገበ።
“መለስ አሣሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛሉ” የሚለውን የውጪ ሚዲያዎች ዘገባ ፤ በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፈጠረው ውጥረት በተጨማሪ፤ በተቃዋሚዎች ዘንድ ከመለስ በሁዋላ ስለምትኖረው ኢትዮጵያ ሀሳቦች መንሸራሸር ቀጠሉ።
ውጥረቱም ሆነ የሀሳብ ፍጭቱ ያየለው፤ ብዙዎች በምንም ምክንያት ይሁን በምን መለስ ከሥልጣን ቦታቸው ከተገለሉ በኢትዮጵያ ፖለቲካ አሰላለፍም ሆነ በሥርዓቱ ላይ የጎላ ለውጥ ይታያል የሚል እምነት ስላላቸው ነው።
ነገሩ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ ነው የህወሀት መስራች የሆኑትና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአቶ መለስ መገለል እንደረሰባቸው ሲነገርባቸው የነበሩት አቶ ስብሀት ነጋ ትናንት ምሽት ለአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ የአማርኛው ክፍል፦”መለስ ታመው ሆስፒታል እየታከሙ እንደሆነና በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራቸው እንደሚመለሱ፤ሆኖም መለስ ኖሩም አልኖሩም፤ሥርዓቱ ያለምንም ለውጥ እንደሚቀጥል የተናገሩት። “መለስ ኖረ አልኖረ፣ በቀለ ኖረ አልኖረ፣ ዘርይሁን ኖረ አልኖረ፣ ፋጢማ ኖረች አልኖረች ለውጥ የለውም። ኢህአዴግ
የገነባው ሥርዓት እያለ ለምን ወደ መለስ እንሄዳለን?” ነው ያሉት አቦይ ስብሀት።
በመለስ መምጣትና መሄድ፤ በድርጅቱ ውስጥ የሚኖር የስልጣን ሽኩቻ እንደማይኖርም አቦይ ስብሀት ተናግረዋል። አቦይ ስብሀት ይህን ይበሉ እንጂ፤ በኢህአዴግ ውስጥ የእርስበርስ የሥልጣን ሽኩቻ የተጀመረው ገና መለስ በታመሙ ማግስት እንደሆነ የውስጥ ምንጮች ይፋ አድርገዋል። ራሳቸው አቶ ስብሀት በዚሁ ቃለምልልሳቸው ስለ አቶ መለስ ጤንነት መሻሻል የገለጹት በቀጥታ የሚያውቁትን ሳይሆን በተዘዋዋሪ ከሌሎች ሰምተው እንደሆነ መናገራቸው፤በህወሀት-ኢህአዴግ መካከል ጫፍ ላይ ለደረሰው መቃቃር- እንደ አንድ ምልክት ነው ሲሉ ፤ቃለ-ምልልሱን ያዳመጡ ወገኖች አስተያት ሰጥተዋል። አይጋ ፎረም በበኩሉ ዛሬ አቦይ ስብሀት ከቪኦኤ ጋር ያደረጉትን ቃለ-ምልልስ ከለጠፈበት ራስጌ ፦”ዓለም በመለስ ጤና ዙሪያ የተፈጠረበትን ብዥታ ለማጥራት የመንግስት ቃል አቀባይን መረጃ እየጠበቀ ባለበት ጊዜ፤ልምድ እና ብቃት ያላቸው የህወሀት/ኢህአዴግ መስራቹና መሪው አቦይ ስብሀት በቪኦኤ በመቅረብ፤ ነገሩን ግልጽ አድርገውታል” በማለት እነ በረከትን በመንቀራፈፍ የሚተች እና አቦይ ስብሀትን የሚያሞግስ ፅሁፍ አትሟል። ከዚህ ሁሉ በሁዋላ ፤ ዛሬ ከቀትር በሁዋላ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት አቶ በረከት ስምዖንና ምክትላቸው አቶ ሽመልስ ከማል፤ በመለስ ጤና ዙሪያ ትናንት ለውጪ ሚዲያዎች የገለፁትን ዛሬ ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች ጭምር ነግረዋቸዋል። መለስ ጥቂት ህመም እንዳጋጠማቸው እና ያም የሆነው በስራ መደራረብና ጫና እንደሆነ ሀኪሞቹ መገንዘባቸውን የጠቀሱት አቶ በረከት፤ ለጥቂት ጊዜ ከሥራቸው ተገልለው ዕረፍት እንዲያደርጉ መመከራቸውን ተናግረዋል። የሐኪም ፈቃዳቸውን ከጨረሱ በሁዋላ በቅርቡ ወደ ሥራቸው እንደሚመለሱም አቶ በረከት አክለዋል። አቶ በረከት ይህን ቢሉም፤በብራሰልስ-ሴንት ሉክ ሆስፒታል የሚገኙ ምንጮች ፤የአቶ መለስ ህመም ከባድ መሆኑን እና የኬሞ ቴራፒ ህክምና ሲከታተሉ መቆየታቸውን ነው ቀደም ሲል ያረጋገጡት። ጉዳዩን በቅርበት እየተታተሉ ያሉ ወገኖች በሰጡት አስተያዬት፤ ከብዙሀን መገናኛዎች፣ከተለያዩ ምንጮችና ከዲፕሎማቶች የተገኙ መረጃዎችም ሆኑ የነ አቦይ ስብሀት መግለጫዎች የሚያመለክቱት ፤ከእንግዲህ መለስ ኖሩም አልኖሩም፤ በቀድሞ ቦታቸውና ጉልበታቸው የሚቀጥሉበት ዕድል ማክተሙን ነው ብለዋል። በኢትዮጵያ ፖለቲካ የአቶ መለስ ፈላጭ ቆራጭነት ማክተሙ ለተሻለ ለውጥ ዕድል ይፈጥር ይሆን? ወይስ የባሰ ነገር ያመጣል? የሚለው ብዙዎችን ማነጋገሩን እንደቀጠለ ነው።

No comments:

Post a Comment