Monday, September 3, 2012

እኛ የምናውቀውና የሱዛን ራይስ መለስ ዜናዊ(በዳዊት ከበደ)
ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል፡፡ የጠቅላዩን ህልፈት ተከትሎ አህአዴግ ውስጥ በአንጋፋዎቹ የህወሀት አመራሮችና በተቀሩት የኢህአዴግ አባል ድርጅት መሪዎች መካከል የስልጣን ሽኩቻው ቀጥሏል፡፡ በረከት ስምኦን፣ ኩማ ደመቅሳ፣ አባዱላ ገመዳ፣ ሬድዋን ሁሴን እንዲሁም በመስከረም 2003ቱ የአዳማው ድርጅታዊ ጉባኤ በይፋ የተሰናበቱት አዲሱ ለገሰን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የብአዴን-ኦህዴድ አመራሮች ከበረከት ጎን ተሰልፈዋል፡፡ (Read the amharic version in PDF)
 ከመጋረጃው በስተጀርባ ህወሓት ድርጅታዊ ጥንካሬውንና ርዕዮተአለማዊ አጀንዳውን ይዞ እንዲቀጥል ስውር መንፈሳዊና ሞራላዊ ሚና በመጫወት የሚታወቁት ስብሐት ነጋ፤ የመለስን ዜና እረፍት ተከትሎ ከሌሎች የህወሃት አንጋፋ አመራሮች አባይ ጸሐዬ፣ አለቃ ጸጋይ በርሄ፣ ቴዎድሮስ ሐጎስ ጋር አሁን ካለው ማዕድ ብቻ ሳይሆን ከቴሌቭዥን ስክሪንም ጭምር ገለል እንዲሉ ተደርገዋል፡፡ የመለስን የቀብር ስነስርአት በቀጥታ የቴሌቭዝን ስርጭት የተከታተለ ማንም ሰው የዚህን እውነትነት ለመመስከር አይቸገርም፡፡ ከመለስ ቀብር በኋላ የትዕይንቱ አዲስ ምዕራፍ በይፋ ስለሚቀጥል ያኔ የምንለውን እንላለን፡፡
መለስን በቅርብ ርቀት:
አቶ መለስን ለመጀመሪያ ጊዜ በቅርብ ርቀት ያየኋቸው በሚያዝያ ወር 2002 ዓ.ም ጽህፈት ቤታቸው በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው፡፡ በአራት ኪሎው ቤተመንግስት በር ላይ ጥቂት ታጣቂዎችና ስቪል የለበሱ የግቢው የደህንነት ሹሞች ወደ ውስጥ የሚዘልቁ ጋዜጠኞችን ማንነት በጥንቃቄ ይመረምራሉ፤ የቀበሌ መታወቂያ፣ ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ከሰጠው ጊዜያዊ መግቢያ ካርድና በእጃቸው ከያዙት ወረቀት ጋር በማመሳከር ካረጋገጡና አስፈላጊውን ሁሉ ፍተሻ ካደረጉ በኋላ ከሌሎች እኔን መሰል ጋዜጠኞች ጋር ወደ ውስጥ እንድንዘልቅ ፈቀዱልን፡፡ ጭር ያለውን የቤተመንግስት ግቢ ተረማምደን ወደ ውስጥ እንደገባን እዛም ሌላ ዙር ፍተሻ ጠበቀን ለዚያውም በማሽን የታገዘ፡፡ በእጄ የነበሩ የምስልና የድምጽ መቅረጫ ቁሳቁሶችና ሌሎች በኪሴ የያዝኳቸውን ኮተቶች ሁሉ አስቀምጬ በማሽኑ ተረማምጄ አለፍኩ፡፡ በቦታው ሆኖ ፍተሻውን የሚያስፈጸመው የደህንነት ሹም በትግርኛ ቋንቋ ተንኮስ የሚያደርግ ንግግር ጣል አደረገ፡፡ ወደ አማርኛ ሲተረጎም ‹‹አእምሮህንም በዚህ ማሽን ብታስፈትሸው መልካም ነበር›› እንደ ማለት ነው፡፡ ነገሩ ቢያበሳጨኝም የእኔ ምላሽ ግን ደብዘዝ ያለ ፈገግታ ነበር፡፡ ለነገሩ ምንስ ምርጫ አለኝ?
መለስን በቴሌቭዥን ስክሪን ብቻ የሚያውቃቸው ሰው በአካል ሲመለከታቸው በስክሪን የተመለከተውን ያህል ግዙፍ ተክለ ሰውነት ላያገኝ ይችላል፡፡ መለስ ፊታቸው አይፈታም፡፡ በእርግጥ ከጋዜጠኞቹ የሚሰነዘሩ ጥያቄዎችም በፊት ገጽታቸው ላይ የራሳቸው የሆነ ተጽእኖ አላቸው፡፡ እንደሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ባህሪይ አንዳንዴ ረጋ ብለው፤ አልፎ አልፎ እጃቸውን እያወናጨፉ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጠያቂውን በትኩረት እየተመለከቱ ይመልሳሉ፡፡
በወቅቱ ምርጫ 2002 እየተቃረበ ነበርና ምርጫ ቦርድ ለተለያዩ አካላት የስነ ምግባር ደንብ በማውጣት ተጠምዶ ነበር፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ስነ ምግባር ደምብ፣ የመገናኛ ብዙሐን የምርጫ አዘጋገብ ደምብ፤ የታዛቢዎች ደምብ…ብቻ ብዙ ግራ የሚያጋቡ ደምቦች ወጥተው ነበር፡፡ የእኔ የጥያቄም ያተኮረው እዚህ ላይ ነበር፡፡ ‹‹ጋዜጠኝነት የራሱ የሆነ ሙያዊ ስነምግባር አለው፤ አንድ ጋዜጠኛ እንዴት መዘገብ እንዳለበት የስነምግባር ሀሁ የሚያስተምር ደምብ ማውጣት ለምን አስፈለገ? ለምሳሌ ዛሬ ለጋዜጣዊ መግለጫ እዚህ እርስዎ ጋ መጥተናል፤ እርስዎ ዛሬ የሰጡንን መግለጫ እንዴት አድርገን በየሚዲያዎቻችን ላይ ማስተናገድ እንዳለብን የሚያስተምር የስነ ምግባር ደምብ መውጣት አለበት ማለት ነው? ምርጫም እኮ ልክ እንደ አሁኑ መግለጫ ክስተት ነው፤ ሌላም ክስተት ሊያጋጥም ይችላል ለያንዳንዱ ክስተት ደምብ ማውጣት ተገቢ ነው ይላሉ?›› የሚል ነበር ጥያቄዬ፡፡
የአቶ መለስ ምላሽ ትንሽ ሸንቆጥ የሚያደርግ ነበር፡፡ ደምብ ማውጣት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አጠር ያለ ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ…‹‹ሚዲያ የራሱ የሆነ ስነ ምግባር አለው፡፡ ያንን ስነ ምግባር የሚያከብር ጋዜጠኛ እንዳለ ሁሉ ምርጫ በመጣ ቁጥር ከስነ ምግባር የወጣ ነገር በመስራት የሚታሰርና ይቅርታ ጠይቆ የሚወጣ ጋዜጠኛም አለ፡፡ ለዚህ ነው ደምቡ አስፈላጊ የሚሆነው›› አሉ፡፡ እንግዲህ በመግለጫው ላይ ተሳታፊ ከነበሩ ጋዜጠኞች መካከል በ1997ቱ ምርጫ ታስሬ በይቅርታ የወጣሁት እኔ ብቻ ነኝ….
ጋዜጠኛ አኒታ ፓወል ሰሞኑን ስለ መለስ በሰጠችው አስተያየት ‹‹መለስ ፈታኝ ጥያቄዎች በቀረቡላቸው ቁጥር ምላሻቸው በፈገግታ የታጀበ ነው›› ብላ ነበር፡፡ አኒታ ፓወል የገለጸቻቸው መለስ ሌላ መለስ መሆን አለባቸው፡፡ እኛ የምናውቃቸው መለስ እንኳን ፈታኝ ጥያቄ ቀርቦላቸው ይቅርና የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ጋዜጠኞች ሲጠይቋቸውም ፈገግ አይሉም፡፡ እርግጥ ነው ከኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞች ይልቅ የውጭ ጋዜጠኞችን ያከብራሉ፡፡ ከፕሬስ ኮንፈረንስ ውጪ አንድ ለአንድ የሚባል አይነት ቃለምልልስ ለኢትዮጵያ የግል ጋዜጦች ሰጥተው አያውቁም፡፡ ደስ የማያሰኛቸው አይነት ጥያቄ ከቀረበ ፊታቸውን ጭፍግግ የሚያደርጉ መለስን ነው እኔ የማውቀው፡፡
አንድ ምሳሌ ላቅርብ፡- ግንቦት 17 ቀን 2002 ዓ.ም የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ የሆኑት ቲዝ በርማን የ2002ቱ ምርጫ አለም አቀፍ ስታንዳርዱን እንዳልጠበቀ ይፋ አደረጉ፡፡ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከልም በበርማን መግለጫ እጅግ በመበሳጨት ‹‹በርማን የአና ጎሜዝ አይነት ጸረ ሰላም አጀንዳ አንግቧል›› ሲል ጻፈ፡፡ በዕለቱ (ከሰዓት በኋላ) በተጠራ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ‹ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል የኢህአዴግ የሚዲያ ተቋም ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በቲዝ በርማን ላይ የተሰነዘረው ትችት (ዋልታ የጻፈውን በማስታወስ) የመንግስትዎ አቋም ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቀረብኩላቸው፡፡ የአቶ መለስ ፊት ወዲያውኑ ተለዋወጠ፡፡ ጥያቄዬ እንዳልገባቸው በመግለጽ አስተካክዬ በድጋቢ እንዳቀርበው አሳሰቡኝ፡፡ ደገምኩት፡፡ ‹‹ቅድም እኮ ተናግሬአለሁ…የቲዝ በርማን ሪፖርት በርካታ ጥሬ ሐቆችን ይዟል፡፡ ያ ማለት ግን በሪፖርቱ ድምዳሜ ላይ እንድንስማማ አያደርገንም፡፡ በድምዳሜው አለመስማማት አንድ ነገር ሆኖ ቲዝ በርማንን ከጠቀስካት ሴትዮ ጋር ማመሳሰል ተገቢ አይደለም፡፡ እሷ እኮ ውጭ አገር በየሰላማዊ ሰልፉ ወያኔ ካልወረደ ….የሚል ዘመቻ ነው የከፈተችው››… አሉ፡፡ መለስ ምላሹን የሰጡት ከግልምጫም ጭምር ነው፡፡ ግልምጫ ብቻም አይደለም፡፡ ከዛ በኋላ ሁለት ጊዜ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ ብሳተፍም የመጠየቅ እድል ግን ጨርሶ ሊሰጠኝ አልቻለም፡፡ ስለዚህ ምቾት የማይሰጥ ጥያቄ ሲቀርብላቸው መለስ ይበሳጫሉ፡፡
ድህረ መለስ ኢትዮጵያ:
የመለስ ሞት ኢህአዴግን ከመጉዳት በቀር አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ለተቃዋሚዎች የሚሰጠው ጥቅም ብዙም አይታየኝም፡፡ ምናልባት ‹‹በመለስ አለመኖር ምክንያት የሚዳከመውና የሚከፋፈለውን ኢህአዴግ ለሚፋለሙ ኃይሎች ቀላል ይሆናል›› ካልተባለ በስተቀር የመለስ ሞት ብቻውን ትልቅ ድል ነው ብለው ‹‹ጉሮ ወሸባዬ››ን ከሚዘምሩ ወገኖች ጋር አልስማማም፡፡ እነሆ ምክንያቴ፡
በመጀመሪያ ደረጃ የመለስ ሞት እንደ ድል ሊቆጠር አይገባም የምለው የሞቱት በተቃዋሚው ትግል ሳይሆን በተፈጥሮ ምክንያት ስለሆነ ነው የሚል መከራከሪያ በማቅረብ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በበቂ ሁኔታ የተዘረጋ ተስፋ ሰጪ የተቃዋሚዎች ኔትወርክ ቢኖርና መለስ በተፈጥሮ (በህመም) ቢሞቱ፤ እናም የእርሳቸው ሞት (ተፈጥሮአዊም ይሁን ሰው ሰራሽ) ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚያሸጋግራት ቢሆን ‹‹ጉሮ ወሸባዬ››ን ሊያስጨፍር ይችላል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ኢህአዴግ ‹‹የሳቸው አለመኖር ብዙም ችግር አያመጣም ትግሉ እንደሆነ ተጠናክሮ ይቀጥላል›› በሚልበት ሰዓት ተቃዋሚዎች በበኩላቸው ‹‹ህዝቡን በግድ አታስለቅሱት›› የሚል ጥሪ ከማሰማት የዘለለ ሚና ሲጫወቱ ባለማየታችን ነው፡፡
እንደ እኔ እንደኔ ግን ፖለቲከኞቹ ‹‹ህዝቡ ተገዶ መውጣቱን›› ካረጋገጡ ‹‹ህዝባችን ሆይ መስቀል አደባባይ ተሰባሰብና በግድ እንድትወጣ ያደረገህን ስርዓት እስኪወርድ ድረስ ወደ ቤትህ እንዳትገባ›› የሚል ጥሪ በማቅረብ ስራ መስራት ነበረባቸው፡፡ በእርግጥም ህዝቡ ተገዶ ከወጣ፤ ለተቃዋሚዎቹ ጥሪ አሉታዊ ምላሽ የሚሰጥበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ አሉታዊ ምላሽ ከሰጠ ደግሞ ችግሩ ሌላ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ከዛ በስተጀርባ ያለውን ችግር መርምሮ እልባት መስጠት፡፡ ሌላ የቤት ስራ መስራት፡፡
በሌላ መልኩ ደግሞ ኢህአዴግ (እንደው በመላው አገሪቱ የወጣው ህዝብ ተደማምሮ 100ሺህ ቢሆን) ያን ያህል ህዝብ በግድ ወጥቶ ቲያትር እንዲሰራ ማስገደድ ከቻለ ተቃዋሚውስ ምን አይነት አጸፋዊ ስትራተጂ መከተል አለበት፡፡ ስርአቱ አስገድዶ ያን ያህል ህዝብ ማሰለፍ ከቻለ ተቃዋሚውስ አገሪቱን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማሸጋገር ህዝቡን በውዴታ እንዴት አድርጎ ማሰለፍ አለበት፡፡ አሁን ያለው የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ይህንን ስለማይፈቅድ ነው የሚል ክርክር የሚነሳም ከሆነ ምን መደረግ አለበት፡፡ ከሰሜን ኮሪያ ጋር በማመሳሰል ትንታኔ መስጠት ቀላል ሊሆን ይችላል፡፡ በኑሮ ውድነትና በፍትህ እጦት 365 ቀን በግድ እያለቀሰ ያለ ህዝብ በአንዱ ቀን ተሰባስቦ ቢያለቅስ ምን ይገርማል? የሚበላውን እንዲያጣ ያደረጉትን መሪ ፎቶግራፍ እያየ በብሶት ከሆነስ የሚያለቅሰው? ከመስቀል አደባባይ ወደ ቤቱ ሲመለስም እኮ በችጋር ማልቀሱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ተግባር እንጂ ‹‹በግድ አታስለቅሱት›› የሚል መግለጫ እምባውን አያብስለትም፡፡
የሱዛን ራይስ ምስክርነት ለኛ :
አምባሳደር ሱዛን ራይስ በመስቀል አደባባይ መለስን የአለም አቀፍ አስተሳሰብ ባለቤት አሏቸው፡፡ እኛ ግን የውጭ ዜጎችን ምስክርነት ሳንጠብቅ አቶ መለስን ጠንቅቀን እናውቃቸዋለን፡፡ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አስተሳሰብ ባለቤት ሆኑም አልሆኑም ‹‹አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ›› የፕሬስ ነጻነት አስፍነው አላሳዩንም፡፡ እኛ የምናውቃቸው መለስ ስለ ፖለቲካዊ መቻቻልም ሆነ ዴሞክራሲያዊ አገር ስለመገንባት ሳይሆን በ21ኛው ክ/ዘመን አውራ ፓርቲን ስለ መመስረት ነበር የሚጨነቁት፡፡ እንደ ሰው ማዘንና ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን መመኘት አንድ ነገር ነው፡፡ መለስ ሱዛን ራይስ እንዳሏቸው አይነት ሰው ቢሆኑ ኖሮ የሱዛን ራይስን ንግግር በአስር ሺህ ማይልስ ርቄ (በራሳቸው በሱዛን ራይስ አገር ተጠግቼ) ሳይሆን መስቀል አደባባይ ተገኝቼ ነበር የማዳምጠው፡፡ ግን አልሆነም፡፡ መለስ እድል ነበራቸው፡፡ ዕድሉን ቢጠቀሙ ኖሮ እኔም፣ እስክንድርም፣ ውብሸትም የአበባ ጉንጉን ይዘንና አልቅሰን በቅድስት ስላሴ ካቴድራል እንሸኛቸው ነበር፡፡
የሱዛን ራይስን ንግግር በተመስጦ ከሰማሁ በኋላ የሂላሪ ክሊንተን ግብጽ ጉብኝት አስታወሰኝ ሂላሪ ክሊንተን በመጀመሪያ ታህሪር አደባባይ የወጡት ሰላማዊ ሰልፈኞችን እንዳላጣጣሉ የኋላ ኋላ ከሙባረክ ስንብት በኋላ ወደ ካይሮ በማቅናት በታህሪር አደባባይ እየተራመዱ የተናገሩትን አስታወስኩ፡፡ to see where this revolution happened and all that it has meant to the world, is extraordinary for me ነበር ያሉት ሂላሪ፡፡ ታዲያ በዚህ ድርጊታቸው የተገረመው የኒውዮርክ ታይምሱ ስቴቨን ሊ ሜየርስም በማርች 16,2011 የጋዜጣው እትም እንዲህ አለ Clinton, in Cairo’s Tahrir square, embraces a revolt she once discouraged. በቀጣይነት የሂላሪን ስልጣን ይረከባሉ ተብሎ ተስፋ የተጣለባቸው ሱዛን ራይስም ዛሬ በመስቀል አደባባይ ያደረጉት ንግግር ዘልአለማዊ ንግግር አይደለም፡፡
/ዳዊት ከበደ፣ የአውራምባ ታይምስ ድረገጽ ኤዲተር ነው/

No comments:

Post a Comment