Wednesday, September 19, 2012

መለስ አዝማሪ አይደለም


በተስፋዬ ገብረአብ
በመለስ የሃዘን መድረክ ላይ አንዲት የህወሃት ደጋፊ የሆነች ሴት ያደረገችውን ንግግር ተከታትዬው ነበር። ለጆሮ በሚጥመው፣ “ለለ” በበዛበት ውብ የእንደርታ ትግርኛ እንዲህ አለች፣
“ቀዳሚዎቹ መሪዎች ለአባይ ምን አደረጉ? ከሃምሳ አመታት በላይ በማሲንቆ ዘፈን ሲዘፍኑለት ነበር። አዝማሪ አቁመው፣ ‘አባይ! አባይ!’ ሲሉ ሙሾ ሲያወርዱ ነው የኖሩት። መለስ ግን አዝማሪ አለመሆኑን ሊያውቁት ይገባል። (መለስ ዋጣ አይኮነን)፣ አዎ! መለስ ጀግና እንጂ አዝማሪ አይደለም። አባይ እንዴት እንደሚደፈር አሳይቶአቸዋል…”
ወይዘሮዋ እዚህ ላይ መናገር አቃታትና ስቅስቅ ብላ አለቀሰች። መለስ አርባው ሳይወጣ ስሙን በአሉታዊ ማንሳት የሚመች አልነበረም። ስርአቱ ግን የመለስን መሞት ለፖለቲካ ፍጆታ እያዋለው ስለሆነ የግድ ስሙን ለማንሳት እንገደዳለን።መለስ አዝማሪ አይደለም
ከመነሻው፣ “አባይን መድፈር” ምን ማለት ነው?
አባይን ለመገደብ ሃይለስላሴም ደርግም ጥናት አድርገው ነበር። የአለማቀፉን ማህበረሰብ ድጋፍና የብድር ገንዘብ ስላላገኙ ሊጀምሩት ሳይችሉ ቀርተዋል። የመድፈር ያለ መድፈር ጉዳይ አልነበረም። በጀብደኛነት ኮሎኔል መንግስቱን ማን ይስተካከለዋል? ኤርትራን ጠምዝዘው በእጃቸው ያስገቡት አክሊሉ ሀብተወልድ አይደሉም እንዴ? ጃንሆይ ወሰን በማስፋት እንጂ፣ ወሰን በማጥበብ አይታወቁም። ሁለቱም መንግስታት ቢቻላቸው ኖሮ አባይን ከመገደብ ወደሁዋላ ባላሉ ነበር። የመድፈር ወኔ አጥተው ሳይሆን፣ ተጨባጩ አቅማቸው ስላልፈቀደ ይመስለኛል የአባይን ግድብ ያልገነቡት።
መለስ በወኔ ዘሎ ገባበት።
ግድቡን ለመገንባት የሚበቃ ገንዘብ ማግኘት አለማግኘቱን አላጠናም። ታሞ ስለነበር ሳይጨርሰው እንደሚያልፍ መቼም ተረድቶት ይሆናል። ተከታዮቹ (እነ በረከት፣ እነ ሃይለማርያም) የግድቡን ግንባታ ሊጨርሱት እንደሚችሉ ምን ዋስትና ነበረው? ከቦንድ ሽያጭ የተሰበሰበችው 5 ቢሊዮን ለሲሚንቶም አትበቃ። ሌላ ምን ትቶላቸው ሄደ? ድፍረት እና ወኔ?
የሆነው ሆኖ፣ “መለስ አዝማሪ አይደለም” ወይም፣ “አባይን ደፈረ” ለማለት ቢያንስ ግድቡ ተገንብቶ እስኪያልቅ መጠበቅ ይገባል። የፋይናንስ ባለሙያ ቡልቻ ደመቅሳ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ አባይን ለመገንባት የሚበቃ አቅም አንደሌለው ጠቁመው ነበር። ብርሃኑ ነጋም፣ የአባይ ግድብ ግንባታ ወሬ ለፖለቲካ ፍጆታ የመጣ መሆኑን አስረግጦ ተናግሮ ነበር። ቡልቻ የተናገሩትን በቅርቡ አይ፣ ኤም ኤፍ ደግሞታል። ግብፅ ግድቡ ከተገነባ በጦር ጄት እንደምትመታው መግለፅዋን ዊኪሊክስ ጠቁሞ ነበር። በርግጥ ግብፅ ይህን አስተባብላለች። ግብፅ አስተባብላለች ብሎ ማመን ግን አይቻልም። ግድቡ በግብፅ ጦር ከተደበደበ የኢትዮጵያ ምላሽ ምን ይሆናል? በአፀፋው አስዋን ግድብን በጦር ጄት መምታት ወይስ የሱዳንን መሬት በመጣስ ታንከኛ ጦር ወደ ግብፅ መላክ? የመቀሌው የኢትዮጵያ አየር ሃይል ግብፅን ለመደብደብ ብቃት አለው? ዝግጅት ተድርጎአል? መለስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ አልሰጠም። “ግብፅ አትደፍረንም፣ ማን እንደሆንን ታውቀናለች” አይነት የጎረምሳ ንግግር ነበር ያደረገው።
የአባይ ግድብ ዜና የኢትዮጵያን ህዝብ ስሜት በከፍተኛ ሁኔታ እንዳነቃቃ እሙን ነው። በመለስ ዜናዊ እረፍት ያዘኑ ወጣቶች ሲናገሩ የተሰሙትም፣ “መለስ የአባይ ወንዝ ተገንብቶ ሳያይ በመሞቱ…” የሚለውን ነበር። የአባይ ግድብ ግንባታ በአንድ ምክንያት ቢቋረጥ፣ “መለስ ባይሞት አይቋረጥም ነበር። ሞት ቀደመው እንጂ…” የሚል አባባል እንደሚመጣ ግልፅ ነው። አንድ የቆየ ቀልድ ታወሰኝ።
“…ዳቦ የለም እንጂ፣ ስኳር ቢኖር ኖር፣ ሻይ አፍልተን ቁርስ እንበላ ነበር።”

No comments:

Post a Comment