Sunday, September 23, 2012

ወያኔን የማስገደድ አሊያም የማስወገድ ትግላችን ተጠናክሮ ይቀጥላል!


በረከት ስምዖን በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብሎ ኃይለማርያም ደሣለኝና ደመቀ መኮንን የኢሕአዴግ ዋናና ምክትል ሊቀመናብርት ሆነው መመረጣቸውን ተናግሯል። ኃይለማርያም ደሣለኝ ደግሞ የተደረገው “ምደባ” መሆኑን በአጽንዖት ደጋግሞ ሲናገር ተደምጧል። “በምርጫ” እና “በምደባ” መካከል ስላለው ውስጠ ወይራ ለጊዜው እንተወው እና በሚከተሉት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እናትኩር።
ኃይለማርያም ደሣለኝና ደመቀ መኮንን የህወሓት አባላት አይደሉም፤ የታላቋ ትግራይ ሪፑብሊክ እቅድ ሲነደፍም በቦታው አልነበሩም። የእነዚህ ሁለት ሰዎች የኢሕአዴግ ዋናና ምክትል ሊቀመናብርት ሆኖ መመረጥ እና በቅርቡም ጠቅላይ ሚኒስትርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሊሰየሙ የሚችሉ መሆኑ በኢትዮጵያ ፓለቲካ ውስጥ የሚኖረው አንድምታ ምንድነው? የእነዚህ ሰዎች ወደ ፊት መምጣት በገዢዎች ቡድን ውስጥ የአስተሳሰብ ለውጥ መምጣቱን የሚያመለክት ነውን?  እነዚህና እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎች ከየአቅጣጫው እየቀረቡ ነው።
በመለስ ዜናዊ የተመራው የትግራይ ገዢ ቡድን ሥልጣን እንደያዘ አንድ ማኅበረሰብ የሚገነባባቸው ሶስቱንም አውታሮች በመቆጠጣር በዘመናችን ተወዳዳሪ የሌለው ዘረኛ አምባገነናዊ አገዛዝ ኢትዮጵያ ውስጥ አሰፈነ። እነዚህ ሶስቱ አውታሮች ፓለቲካ፣ ኢኮኖሚና ሲቪል ማኅበረሰቡ ናቸው።
በፓለቲካው ረገድ ቡድኑ ራሱ ህግ አውጭ፣ ህግ ተርጓሚ እና ህግ አስፈፃሚ በመሆን ሁሉንም መንግሥታዊ ሥልጣኖችን ተቆጣጠረ። በተለይም የመንግሥት የአስተዳደር መዋቅርን፣ መከላከያ፣ ደህንነትን እና የፍትህ ሥርዓቱን በቁጥጥሩ ሥር አደረገ። በኢኮኖሚው ረገድ ኢፈርትንና መሰል ኩባንያዎችን አደራጅቶ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረ። ሲቪሉ ማኅበረሰብን ለማስገበር ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስና የኢትዮጵያ እስልምና ምክር ቤት (መጅሊስ) ከመቆጣጠር ጀምሮ እስከ ገጠር መንደር ድረስ የወረደ የመቆጣጠሪያ መረብ ዘረጋ። “የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ” ማለት ይኸ ሁሉ ነው። ስለትግራይ ገዢ ጉጅሌ (ቡድን) ስንናገር የምናስበው ይህንን ሰፊ የአፈናና የብዝበዛ  መረብ ነው።
አሁን መለስ ዜናዊ እንደ ግለሰብ ሞቷል፤ የገነባው ዘረኛ የአገዛዝ ሥርዓት ግን አለ። የመለስ ዜናዊ መሞት አገዛዙን የነቀነቀው ቢመስልም ሥርዓቱ የተገነቡበት ምሰሶዎች፣ ግድግዳና ጣሪያዎች ግን በቦታቸው እንዳሉ ናቸው። ለማስረጃም ያህል ዛሬም መከላከያና ደህንነት በወያኔ እንደተያዘ ነው። እንዲያውም በቅርቡ በተደረገው ሹመት ጦሩ ከቀድሞው የባሰ ወያኔያዊ እንዲሆን ተደርጓል። ከብርጋዴር ጀኔራልነት ወደ ሜጀር ጄኔራልነት እንዲያድጉ የተደረጉት ሶስቱም ከፍተኛ መኮንኖች የትግራይ ተወላጆች መሆናቸው የሚያመለክተው ይህንኑ ነው። ከኮለኔልነት ወደ ብርጋዴር ጄኔራልነት ማዕረግ ካደጉት 34 ወታደራዊ መኮንኖች 22ቱ የትግራይ ተወላጆች መሆናቸው የሚያረጋግጠው ና ይህንኑ ነው። ሁሉም ተሿሚዎች የወያኔ አባላት ወይም ታማኝ ደጋፊዎች መሆናቸው ግልጽ ነው።  በኢኮኖሚው ረገድ የታዩ መሻሻሎች የሉም፤ ዘረፋው እንደቀጠለ ነው። በቤተክህነትና በመጅሊስም ወያኔ የራሱን ሰዎች እንደገና ለማንገስ እየጣረ ነው። እስከ ገጠር መንደር የወረደው የወያኔ መረብ እንዳለ ነው። በዚህም በተጨማሪ አዲሶቹ ተሿሚዎች እየማሉና እየተገዘቱ ያሉት የመለስ ዜናዊ “ራዕይ”  ስለማሳካት መሆኑ አጽንዖት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም ደረጃዎች ላይ ያለ የመንግሥት ሥልጣን መያዝ ያለበት በነፃ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒን የሕዝብ ምርጫ ብቻ መሆን አለበት ብሎ በጽኑ ያምናል፤ ለዚህም ይታገላል። ባለጉዳዩ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሩ ተዘግቶበት በሚደረግ ምርጫም ሆነ ምደባ የሚመጣ ሹመት ተቀባይነት የለውም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለውጥን የሚለካው ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፈን ባለው አስተዋጽዖ ነው።
ብአዴኖች፣ ኦህዴዶችና ደህዴዶች ራሳቸውን ከህወሓት ባርነት ነፃ የማውጣት ድፍረት ያላቸው ከሆነ፤ በህወሓት ውስጥም የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ያደረሰው እና ወደፊትም ሊያደርስ የሚችለውን ጥፋት የተገነዘቡ ሰዎች ካሉ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፈን አስተዋጽዖ ያላቸው ተጨባጭ ተግባራዊ እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርባቸዋል። የሚከተሉት ተግባራት ደግሞ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል።
  1. መለስ ዜናዊ የገነባቸው የስለላና የብዝበዛ መዋቅሮችን ማፈራረስ፤
  2. የመከላከያ ሠራዊትና የደህንነት መሥሪያ ቤት ከህወሓት ቁጥጥር ነፃ ማውጣትና ታማኝነቱ ለኢትዮጵያ በሆነ ሠራዊትና የደህንነት ተቋም መተካት፤ እና
  3. በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ኃይሎችን ሁሉ የተሳተፉበት ነፃ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒን ምርጫ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ለሽግግር ሥርዓት ቦታ መልቀቅ።
እስካሁን ከላይ በተዘረዘሩት የተግባር መስኮች ላይ ያየነው ፍንጭ የለም። የመለስ ዜናዊ በሞት መለየት ህወሓትን የጎዳ መሆኑ ግልጽ ነው፤ ተገዶ ወደ ድርድር የሚመጣበት ደረጃ ግን ገና አልደረሰም።  ስለሆነም ትግላችን ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ወያኔን ለማስገደድ ወይም ለማስወገድ ቆርጦ መነሳት ይኖርበታል። ለዚህ ደግሞ “አልገዛም!” ማለት ይኖርበታል።
ብአዴኖች፣ ኦህዴዶችና ደህዴዶች እንዲሁም ህወሓት ውስጥ ለሕዝብና ለአገር ወገናዊነት ያላችሁ ብትኖሩ አሁኑኑ ከሕዝብ ጎን ብትቆሙ ራሳችሁን ታድናላችሁ፤ አገራችሁን ትጠቅማላችሁ። አለበዚያ ግን በተባበረ የሕዝብ አመጽ ወያኔ መወገዳችሁ አይቀርም።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ከሌሎች ድርጅቶ ጋር በመሆን ይህንን ትግል እየመራ ነው። ፍትህ፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ዲሞክራሲ የናፈቀው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከግንቦት 7 ጎን ይሰለፍ!!!  የቆምንለትን ሕዝባዊና አገራዊ ዓላማ እናሳካለን!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

No comments:

Post a Comment