Tuesday, October 2, 2012

ጥሪ ለኦሕዴድ አባላት!!!


ተዋርዶ ከማዋረድ መላቀቂያችሁ አሁን ነው!!!
የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ታላቁን የኦሮሞ ሕዝብ እወክላለሁ ይላል። ኦሮሞ ደግሞ የኢትዮጵያ ምሰሶ ነው። ከዚህ ታላቅ ሕዝብ ወጣሁ የሚለው ኦሕዴድ ግን እወክለዋለሁ የሚለውን ሕዝብ ጥቅም ሊጠብቅና ሊያስጠብቅ ቀርቶ ለራሱ እንኳን መሆን ያልቻለ፤ የተናቀና የተዋረደ የወያኔ ሎሌ ሆኖ ድፍን 21 አመት አስቆጠሮአል። ወያኔ ደግሞ ስሙ እንደሚያለክተው ከውልደቱ ጀምሮ የትግራይ ነፃ አውጭ ድርጅት ነው።
ወያኔ ትግራይን “ነፃ” ካወጣ በኋላ ለመቋቋሚያ የሚሆነው ግዛት አስፈለገው። ወያኔ ኦሮሚያን መግዛትና መበዝበዝ ለሕልውናው አስፈላጊ እንደሆነ ተገነዘበ፤ ለዚህም ተንቀሳቀሰ። በኦሕዴድ ሎሌነት የኦሮሚያን ሕዝብና መሬት በቁጥጥሩ ሥር አደረገ። “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” እንዲሉ በዘር ፊደራሊዝም ስም የኦሕዴድ ካድሬዎች ኦሮሚያን ለወያኔ ዘረኞች አሳልፈው ሰጧት። ኦሕዴድ ባይኖር ኖሮ ኦሮሚያ የወያኔ መፈንጫ ባልሆነችም ነበር። የኦሕዴድ ክህደት ግን በዚህ አላበቃም። የወያኔ ሹማምንት በኦሮሞ ለም መሬት፣ ደን፣ ማዕድንና ውሃ ሲከብሩ የኦሕዴድ ሎሌዎች ለፍርፋሪ ሲሉ ብዘበዛውን ማሳለጥ ጀመሩ። የኦሕዴድ ካድሬዎች የገዛ ወገናቸውን አሳረዱ፤ ያደጉበትን መንደር፤ የሮጡበትን ሜዳ አዘረፉ።
በኦሕዴድ ሎሌነት ሳቢያ ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ እስር  ቤቶች በኦሮሞዎች ተሞልተዋል። የኦሮሞ ለም መሬቶች ለወያኔና የወያኔ ወዳጆች ለሆኑ ባዕዳን በብላሽ ታድሏል። የኦሮሞ ደኖች ተመንጥረዋል። የኦሮሞ ማዕድናት ወያኔ እንዳሻው የሚያፍሰው ባላቤት ያጣ ንብረት ሆኗል። በኦሕዴድ ሎሌነት ሳቢያ ዛሬ የኦሮሞ ገበሬ ብቻ ሳይሆን የዱር አራዊቱም ተሰደዋል። ይህ ሁሉ የሆነው የኦሮሞ ልጆች ነን በሚሉ የኦሕዴድ ካድሬዎች ሎሌነት መሆኑ እጅግ የሚያስቆጭና የሚያንገበግብ ነገር ነው።
አሁን ደግሞ የባሰ አሳፋሪ ነገር እየታዘብን ነው።
ዘረኛውና አምባገነኑ መለስ ዜናዊ በመሞቱ በረከት ስምኦንና ግንባር ቀደም ወያኔ ደቀመዛሙርቱ የወታደሩንም የሲቪሉንም ሥልጣን እየተቀራመቱ ነው። እስቲ እንጠይቅ።
  • ከዚህ ቅርምት ለኦሕዴድ ምን ደረሰው? ምንም።
  • የጄኔራልነት ማዕረግ ለሕወሓት ሰዎች ሲታደል ኦሕዴድ ምን አደረገ? ምንም።
  • የአገሪቱ  የደህንነት መዋቅር ሙሉ በሙሉ በወያኔ ሲያዝ ኦሕዴድ ምን አለ? ምንም።
  • የአገሪቷ ንብረት በሙሉ ወያኔ በፈለፈላቸው ድርጅቶች ሲያዝ ኦሕዴድ ምን አለ? ምንም።
  • ሟቹን መለስ ዜናዊን ለመተካት በነበረው ሽኩታ የኦሕዴድ ሚና ምን ነበር? ምንም።
ይህ ከምር ያሳፍራል።
አሳፋሪነቱ ደግሞ  ለኦሕዴድ አባላት ብቻ ሳይሆን  ለመላው የኦሮሞ ሕዝብ ከዚያም አልፎ  ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተርፎአል ። የኦሮሞ ሕዝብ ኦሕዴድን የመሰለ አሳፋሪና ከሃዲ  ድርጅት በታሪኩ ገጥሞት አያውቅም።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ኦሕዴድን ከአባላቱ ለይቶ ማየት ይሻል። ከዚህም በተጨማሪ የኦሕዴድን ከፍተኛ አመራር አባላትን ከበታቾቹ ለይቶ ይመለከታል። ሥጋቸውን ብቻ ሳይሆን ነፍሳቸውንም ሳይቀር ለወያኔ አሳልፈው የሰጡ ሰዎች ኦሕዴድ ውስጥ መኖራቸው ምንም ጥርጥር የለውም። በአንፃሩ ደግሞ  ራሳቸውን ከወያኔ ባርነት ነፃ አውጥተው የበደሉትን ሕዝብ በመካስ ላይ ያሉ ጀግኖች መኖራቸው ግልጽ ነው። ግንቦት 7፡ ከውስጥ ሆነው ወያኔን እየታገሉ ላሉም ሆነ ድርጅቱን ጥለው የነጻነት ትግሉን ለተቀላቀሉ  ለእነዚህ ቆራጥ የቀድሞ  የኦሕዴድ አባላት፤ የዛሬ አርበኞች ትልቅ አክብሮት አለው። በሚያደርጉት ትግልም ከጎናቸው ቆሟል፤ ወደፊትም ይቆማል።
ግንቦት 7፣ ብዙሃኑ የኦሕዴድ አባላት ራሳቸውን ከወያኔ ዘረኛ አምባገነን አገዛዝ ነፃ የማውጣት የግል፣ የወገንና የአገር ግዴታ  አለባቸው ብሎ ያምናል።
ስለሆነም ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ለብዙሃኑ ኦህዴድ አባላት የሚከተለው ጥሪ ያደርጋል።
የኦሕዴድ አባላት ሆይ!
ከወያኔ ዘረኛ አምባገነን አገዛዝ ሎሌነት ነፃ ለመውጣት መንገድ መሻት የራሳችሁ ኃላፊነት ነው። የገዛ ራሳችሁን፣ ቤተሰቦቻችሁን፣ የኦሮሞን ሕዝብ እና  ኢትዮጵያን እያዋረደ፤ ሃብቷን እያዘረፈ ካለው ወያኔያዊ ኦሕዴድ ተላቀቁ። አሊያም እውስጡ ሆናችሁ ድርጅቱን ግደሉት። የኦሕዴድ መኖር ለወያኔ ካልሆነ በስተቀር ለእናንተ፣ ለቤሰቦቻችሁ፣ ለክልላችሁ ለኦሮሚያና ፣ ለኢትዮጵያ አይበጅም። በአሁኑ ሰዓት የወያኔን እድሜ እያራዘማችሁ ያላችሁ እናንተ ናችሁ። በፓርላማው ሳይቀር ለወያኔ የማሳሳቻ ጭንብል የሆናችሁለት እናንተ ናችሁ። ተዋርዳችሁ ሕዝባችሁን አታዋርዱ። ይልቁንስ ታሪክ ሥሩ። ዛሬውኑ የነፃነት ትግሉን ተቀላቀሉ።
አለበለዚያ ወያኔ ያለበሳችሁን የውርደት ካባ ለማውለቅ እንኳን ጊዜ አይኖራችሁም።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

    No comments:

    Post a Comment