Wednesday, November 9, 2011

ህዝብን ማሸበር የመጨረሻዉን ቀን ያሳጥረዋል እንጂ አያስረዝመዉም

የኢትዮጵያ ህዝብ ያለፉት ሀያ አመታት ታሪክ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ከወያኔና ወያኔ ተሸክሞ ካመጣቸዉ ኮተቶች ጋር የተያያዘ ነዉ። ይህ ደግሞ ወደንና ፈቅደን ያቀፍነዉ የታሪክ ምዕራፍ ሳይሆን እንደ ቀንበር በግድ የተጫነብን ዕዳ ነዉ። ለዚህም ይመስላል ወያኔ የተባለዉ ቃል በተነሳ ቁጥር የኢትዮጵያ ህዝብ “ተዉ ስማኝ አገሬ ሲከፋኝ ነዉ መኖሬ” እያለ አንጀቱ ዉስጥ የሚነደዉ እሳት የሚቀዘቅዝ እየመሰለዉ በአፉ የሚተነፍሰዉ። ወያኔ ደርግን አሸንፎ የመጣ ኃይለ ቢሆንም መለስ ዜናዊንና ስብሐት ነጋንየመሳሰሉ መሰሪ መሪዎቹ፤ በኢትዮጵያና በህዝቧ ላይ ያላቸዉን ጥላቻ ያሳዩት ገና በጥዋቱ ስለነበረ ህዝቡ “ደሞ ምን ይመጣብኝ ይሆን” እያለ ጭንቀቱን ከመግለጽ ዉጭ ወያኔን ዬኔ ነዉ ብሎ አያዉቅም። ዛሬ ወያኔ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ ሃያ ድፍን አመታት ተቀጥረዋል፤ ሆኖም ወያኔ እራሱ መንገዶችን፤ አደባባዮችንና አንዳንድ ተቋሞችን ወያኔያዊ ስም ያወጣላቸዉ አንደሆነ ነዉ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሆነ ወያኔን በፍጥነት አስወግዶ ክፉ ትዝታዉን የሚያስረሳዉን ነገር እንጂ ወያኔን የሚያስታዉሰዉ ነገር በፍጹም አይፈልግም።
በዚህ በመገባደድ ላይ ባለዉ የፈረንጆቹ አመት በተለይ ከሰሜን አፍሪቃዉ የአረብ አብዮት በኋላ የወያኔ ፀባይ እንደ እርጉዝ ሴት በየቀኑ ሲቀያየር ይታያል። ባለፉት ሃያ አመታት ህዝብ የሚበላዉ አጥቶ ሲቸገር ኤኮኖሚዉ በድርብ አሃዝ አደገ እያሉና ሰላማዊ ህዝብ መኃል ገብተዉ ቦምብ እያፈነዱ በተቃዋሚ ድርጅቶች ላይ እያላከኩ የከረሙት የወያኔ ጉደኞች በዚህ በያዝነዉ አመትማ ጭራሽ ብሶባቸዉ አላፊ አግዳሚዉን “ሽብርተኛ” እያሉ መክሰስ ጀምረዋል። ይሀ የዘንድሮዉ “አላርፍ ያለች ጣት” አይነቱ የወያኔ አጉል .መንቀልቀልና የቀቢፀ ተስፋ እርምጃ የኢትዮጵያን ህዝብ ለመጨረሻዉ ወሳኝ ትግል ከማዘጋጀቱ ባሻገር ህዝቡ “ሽብር”፤ “ሽብርተኛ”ና “አሸባሪ” የሚባሉ ቃላቶችን ከወትሮዉ በተለየ መልኩ እንዲጠቀምባቸዉ እያደረገዉ ነዉ።
መለስ ዜናዊ አዲስ አበባን ከረገጠበት ግዜ ጀምሮ አገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ የአገዛዙ ቅሌቶች ስትታመስ የቆየች ቢሆንም ይህ ከሰሞኑ የምናየዉ ቅሌት ግን ለጽድቅም ለኩነኔም የማይመች ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ነዉ። መለስ ዜናዊ በአለም አቀፍ ደረጃ በሽብርተኝነት ላይ የሚካሄደዉ ጦርነት ያንን እስቀያሚ ገጽታዉን የሚሸፍንበትን የፖለቲካ ሽፋን እንደሰጠዉ በሚገባ ያዉቃል። ለዚህም ይመስላል የሽብርተኛዉ ብዛት ባደገ ቁጥር በአንድ በኩል የስልጣን ዘመኑ የሚራዘምለት እየመሰለዉና በሌላ በኩል ደግሞ የአሜሪካ መንግስት የሚሰጠዉ ድጎማ የሚጨምር እየመሰለዉ የኢትዮጳያን ህዝብ በደፈናዉ ሽብርተኛ ብሎ ለመጥራት የቀረዉ አንድ ሐሙስ ብቻ ይመስላል። የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ጋዜጠኛዉን፤ ደራሲዉን፤ አርቲስቱን፤ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዉን፤ አስተማሪዉንና ተማሪዉን ሽብርተኛ እያለ ማሰር ከጀመረ ሰንበት ብሏል። የሚገርመዉ ይህ አላፊ አግዳሚዉን ሽብርተኛ እያሉ ማሰር መለስ ዜናዊ አስካመነበት ድረስ ማንንም ሰዉ ያጠቃልላል። ለምሳሌ እስከዛሬ በአለም ላይ በሽብርተኝነት ቀርቶ በተራ ወንጀል እንኳን ስማቸዉ እምብዛም የማይጠራዉን የሲዊዲን ዜጎችም መለስ ዜናዊ ስላመነበት ብቻ ሽብርተኞች ተብለዉ ያልተበደሩትን ዕዳ እየከፈሉ ነዉ።
ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች በዚህም በዚያም ብለዉ አጣብቂኝ የበዛበት መስቀለኛ መንገድ ላይ ደርሰዋል። ከዚህ አጣበቂኝ ዉስጥ ለመዉጣት አማራጩ ከህዝብ ነፃነትና ከነሱ የበላይነት አንዱን መምረጥ አለባቸዉ። ይህ ምርጫ ደግሞ እንዳዉ የዘፈቀደ ምርጫ ሳይሆን ለአገር፤ ለወገንና ለራስ ታማኝ መሆንን የሚጠይቅ ምርጫ ነዉ። መለስ ዜናዊና ጓደኞቹ በተፈጥሯቸዉ እንኳን ለአገርና ለወገን ለራሳቸዉና ለስሜታቸዉም የማይታመኑ ከሃዲዎች ናቸዉ። እንኳን የወደፊቱን የነገዉንም አያምኑምና ዉሳኔያቸዉ የአንድ ቀን፤ ምርጫቸዉ የአንድ ቀን፤ መሃላቸዉም የአንድ ቀን ነዉ። ስለዚህም ነዉ ህዝብን እያስለቀሱና ልጆቹን ከጉያዉ ጎትተዉ እስር ቤት እያጎሩ በዚያ እፍረት የሚባል ነገር በማያዉቀዉ አንደበታቸዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ሽብርተኞችን በማጋለጥ ላደረገልን ትብብር እናመሰግናለን የሚሉት። ነገሩ “ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነዉ” እንዲሉ ሆኖ ነዉ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብማ ማን አሸባሪ ማን ተቀርቋሪ፤ ማን ለአገር አሳቢ ማን አገር ተሳዳቢ መሆኑን ካወቀ ሰንብቷል። ህዝብ የሚቆረቆሩለትን ልጆቹንና የሚዶልቱበትን ጠላቶቹን በዉል ለይቶ ያዉቃል። ይህንን ደግሞ ወያኔ ከሰሞኑ አላፊ አግዳሚዉን እያፈሰና ሽብርተኛ እያለ መዕከላዊ የሚሉት የምድር ላይ ሲዖል ዉስጥ ሲከታቸዉ – ህዝቡ በያለበት እስክንድር ሽብርተኛ ከሆነ እኛም ሽብርተኞች ነን፤ አንዱአለም አሸባሪ ከሆነ እኛም አሸባሪዎች ነን፤ደበበ እሼቱ የአሸባሪዎች ተባባሪ ከሆነ እኛም የአሸባሪዎች ተበባሪ ነን እየለ ተቃዉሞዉን በማሳየት ገልጿል። የሚገርመዉ ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ “ሽብርተኝነት” “ጀግንነት” እያለ የወያኔን የፀረ ሽብር ህግና ወያኔ ሽብርተኞች እያለ የሚወስዳቸዉን እርምጃዎች መሳቂያና መሳለቂያ አድርጎታል። ወያኔም ቢሆን የፀረ ሽበር ህጉን ያወጣዉ የሚቃወሙትን ኃይሎች እያነቀ እስር ቤት ለመወርወር የሚያስችል ህጋዊ ሽፋን ለማግኘት ሲል ነዉ እንጂ እያሰረ የሚያሰቃያቸዉ ኢትዮጵያዉያን ሽብርተኞች አለመሆናቸዉንማ በሚገባ ያዉቃል። እጅግ በጣም ከሚገርሙን ነገሮች አንዱ ዛሬ በአለም አቀፍ ደረጃ አሸባሪ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን ከፈፀሙት የሽብር ተግባር ጋር አያይዞ የሚመዘግበዉ ድርጅት ድህረ ገጽ ላይ ስማቸዉ ከሽብርተኝነት ጋር በቀጥታ ተያይዞ የሚገኘዉ መለስ ዜናዊ የሚመራዉ የህዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ ነዉ አንጂ ዉብሸት፤ አንዱአለም፤ እስክንድር፤ በቀለ፤ ኦላና፤ ወይመ ደበበ እሸቱ አይደሉም።
ኢትዮጵያ ዉስጥ ብቻ ሳይሆን ነፃ የመገናኛ አዉታሮች በሌሉበት በዬትኛዉም አገር ቢሆን የፖለቲካ መሪዎች ያልሰሩትን ሠራን ያልጀመሩትን ጨረስን፤ ያልጋገሩትን አበሰልን ማለት ልማዳቸዉ ነዉ። መለስ ዜናዊ ደግሞ ተሳስቶም ቢሆን እዉነት ከተናገረ ነዉ “ምን ነካዉ” የሚባለዉ እንጂ ዉሸትማ ሲፈጠር ጀምሮ መታወቂያ ካርዱ ነዉ። በዬትኛዉም አገር ዉስጥ መንግስት፤ ሲቪል ማህበራትና ሌሎችም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ግዴታቸዉን በሚገባ መወጣታቸዉን እየተከታተሉ ለህዝብ የማስታወቅ ሐላፊነት ያለባቸዉ የመገናኛ አዉታሮች ናቸዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ ደግሞ ቴሌቪዥን፤ ሬዲዮና አዲስ ዘመንን የመሳሰሉ የዜና ማሰራጫ አዉታሮች የመንግስት ንብረት በመሆናቸዉ ያንኑ መንግስት የዋሸዉን ዉሸት መልሰዉ መላልሰዉ ከማሰተጋባት የዘለለ ተግብር ማከናወን አይችሉም። የግል ጋዜጠኞች ደግሞ በተነፈሱ ቁጥር ዉሎና አዳራቸዉ ማዕከላዊና ቃሊቲ ሆኗል። ለኢትዮጵያ ህዝብ አማራጭ የመረጀ ምንጮች የነበሩት የአሜሪካና የጀርመን ድምፅ ሬዲዮ ጣቢያዎች በወያኔ አፈና የተነሳ አስም እንደያዘዉ ሰዉ መነፋነፍ ከጀመሩ ቆይተዋል። በዉጭ አገር የሚገኙ የኢትዮጵያዉያን ድህረ ገፆች፤ ሬዲዮኖችና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ደግሞ እድሜ ለቻይና አገር ውስጥ እንዳይነበቡ ወይም እንዳይሰሙ ተደርገዋል። በነገራችን ላይ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ የኢትዮጵያ ህዝብ ከአማራጭ ምንጮች መረጃ እንዳያገኝ ለማድረግ ብቻ በዉጭ ምንዛሪ የሚያወጣዉ ወጪ አገሪቱ ዉስጥ የደረሰዉን አስከፊ የረሀብ አደጋ ለመከላከልና ረሀብተኛዉን ለመቀለብ ከሚያወጣዉ ወጪ በአራት እጥፍ ይበልጣል። እንግዲህ ይህ ሁሉ የሚያሳየን የመለስ ዜናዊ የአፈና ኃይል በግሉ ፕሬስ ላይ ያተኮረዉ እንደነ አስክንድር ነጋ፤ ዉብሸት ታዬና ርኢዮት አለሙን የመሳሰሉ የሾለ ብዕር ያላቸዉ ጋዜጠኞች መለስ ዜናዊን አላስዋሽ እያሉ ስላስቸገሩት ብቻ መሆኑን ነዉ።
መለስ ዜናዊና ጓደኞቹ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት አደገ እያሉ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ሲያዉጁ አዉራምባ ታይምስንና ፍትህን የመሳሰሉ የግል ጋዜጦች – የታለ ዳቦዉ ህዝቡኮ እየተራበ ነዉ ይሉታል፤ የወያኔ የፕሮፓጋንዳ አዉታሮች የኢትዮጵያ ህዝብ የኢህአዴግን መመረጥ በመደገፍ ሠላማዊ ሠልፍ ወጣ ብለዉ ነጭ ዉሸት ሲዋሹ በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ ጋዜጠኞች ደግሞ ከየመስሪያ ቤቱ ተገዶ ሠልፍ የወጣዉን ሰዉ በዋቤነት በማቅረብ ዉሸቱን በእዉነት ይቀይሩበታል። እንደዚህ አይነቱ በሞራል ትክክልኛነት ላይ የተመሰረተና ግልፅ የሆነ ጋዜጠኝነት ደግሞ ከደደቢት በረሃ ጀምሮ ነገረ ስራዉ ሁሉ ጨለማ ዉስጥ ብቻ ለሆነዉ ወያኔ በፍፁም የሚዋጥ አልሆነም። ደግሞስ መለስ ዜናዊና ጓደኞቹ ከጫካዉ ወጡ እንጂ ጫካዉ ዛሬም ድረስ ከነመለስ ዜናዊ ዉስጥ አልወጣም፤ የወያኔ ሹሞች የሚኖሩት የጫካ ኑሮ፤የሚሰሩት የጫካ ስራ፤የሚመሩትም በጫካ ዉስጥ ህግ ነዉ፤ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ከፍተኛ ግጭት ዉስጥ የሚገቡትም በነሱ ግራ የተጋባ የጫካ ዉስጥ ህግ ከጫካዉ ዉጭ የሚኖረዉን ሠላማዊ ህዝብ እንዳኝህ ሲሉ ነዉ። እንግዲህ እነ መለስ ዜናዊ በነሱ የጫካ ህግ አልዳኝ ያለዉንና ባጠቃላይ ከነሱ ጋር አልስማማም ያለዉን ሁሉ እጅና እግሩን አስረዉ ማዕከላዊ እየወሰዱ ህይወቱን እስኪስት ድረስ አካሉንና የውስጥ ስሜቱን የሚያቆስሉት። እነመለስ ዜናዊ አለመግባባትን የሚያስወግዱት በአንድ መንገድ ብቻ ነዉ። በጠመንጃ!
ዛሬ እነመለስ ዜናዊ መስከረም ሲጠባ “ሽብር”፤ ህዳር ሲታጠን “ሽብር” ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተናገሩ ቁጥር “ሽብር”፤እያሉ እነሱ ተሸብረዉ ህዝብን የሚያሸብሩት እዉነትም ኢትዮጵያ ዉስጥ ሽብርተኞች ተፈጥረዉ አይደለም። ነገሩ “ጭር ሲል አልወድም” እንዳለቸዉ ወይዘሮ ነዉ። የኢትዮጵያ ህዝብ የወያኔ ቀንበር ከብዶት ለጥቂት ግዜም ቢሆን ዝም ካለ – ይሀ ለወያኔ ሽብር ነዉ፤ ህዝብ ኑሮ ተወደደብኝ ብሎ አቤቱታ ካቀረበ ሽብር ነዉ፤ መብቴንና ነፃነቴን ብሎ ከታገለም ሽብር ነዉ። እንደ መለስ ዜናዊና ጓደኞቹ አባባል የኢትዮጵያ ህዝብ ሽብርተኛ የማይሆነዉ አፉን ዘግቶና አንገቱን ደፍቶ አሜን ብሎ ሲገዛላቸዉ ብቻ ነዉ። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ለመብቱና ለነፃነቱ ለሚታገሉ ልጆቹ ሁሉ የሚዋጥ ሀቅ አይደለም። ስለሆነም ወያኔ ህዝብን አሸባሪ እንዳለ ህዝብም ወያኔን አሸባሪ እንዳለ የኢትዮጵያ ህዝብ መብት፤ ነፃነትና እኩልነት ሙሉ ለሙሉ እስከተከበረ ድረስ ትግሉ ይቀጥላል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ወያኔ በ2002 ዓም ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ብሎ ያረቀቀዉ ህግ ለህዝብ መብት፤ነፃነትና እኩልነት የሚታገሉ የሰላምና የዲሞክራሲ ኃይሎችን አስሮ ለመደብደብ ወይም ለመግደል እንዲያመቸዉና በተለይም በአለም አቀፉ ህብረተሰብ ፊት ህጋዊ ሽፋን እንዲሆንለት የሚጠቀምበት ዘዴ መሆኑን በሚገባ ተረድቷል። ለዚህም ይመስላል ዛሬ ህዝቡ “ሽብርተኝነት” “ጀግንነት” ነዉ እያለ ወያኔ በሽብርተኝነት ስም ያሰራቸዉን እነ አስክንድር ነጋን፤ አንዱአለም አራጌን፤ ርኢዮት አለሙን፤ ኦላና ሌሊሳን፤ በቀለ ገርባን፤ ዉብሸት ታዬንና ሌሎችም ስማቸዉ የማይታወቅ የነፃነት ታጋዮችን “ጀግና” ብሎ መጥራት የጀመረዉ። እንግዲህ ካሁን በኃላ ሌላ ሁሉ ቢቀር ወያኔ የዘራዉ የክፋትና የዘረኝነት ዘር ከኢትዮጳያ ምድር ላይ አስኪነቀል ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ የልጆቹን ስም የሚሰይመው “ጀግናዬ” ለማለት “ሽብሬ” “ጀግናዉ” ለማለት ደግሞ “ሽብሩ” ብሎ ነዉ። በጣሊያን ወረራ ዘመን ለጠላት አንገዛም ብለዉ መሳሪያ አንስተዉ ጠላትን ያንቀጠቀጡ ልጆቹን “ናደዉ” “ድል ነሳ” ና “አሸናፊ” ብሎ እንደሰየማቸዉ ዛሬም የወያኔን ዘረኝነት የሚታገሉ ልጆቹን ሽብሬ፤ ሽብሩ ወይም አሸብር እያለ እንደሚሰይማቸዉ ምንም ጥርጥር የለንም። ባለፉት አስር ወራት በግልፅ እንደተመለከትነዉ መለስ ዜናዊ ከቤን አሊ፤ ከሙባረክና በቅርቡ ደግሞ ጋዳፊን ከገጠማቸው የህዝብ ቁጣ ትምህርት መቅሰም የቻለ አይመስለንም፤ ተራው ደርሶ ላለፉት 20 አመታት ኮትኩቶ ያሳደጋቸው የህዝብ ብሶቶች ገንፍሎ አደባባይ ሲወጣ የሁላችንም ምኞትና ጸሎት የሚሆነው መለስ ዜናዊን አያድርገን ነው። እስከዚያው በወያኔ ፓርላማ ውስጥ ጭምር እያየነው ያለነው የመለስ ዜናዊ ድንፋታ፤ ስድቡና ፉከራ ይቀጥላል:።

ዋና ምንጭ ሚከትለው ድህረገፅ   : http://www.ginbot7.org/amh_wp/?p=2260

No comments:

Post a Comment