Sunday, April 8, 2012

በኢትዮጵያ ውስጥ እየደረሰ ያለው የመብት ጥሰትና የህጋዊ ስርዓት መናጋት በእጅጉ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የኢትዮጵያ ፌደራላዊት መድረክ አስታወቀ


ድርጅቱ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ ወያኔ ስልጣን ከተቆናጠጠበት ጊዜ አንስቶ የዜጎች መብት ጥሰት እየባሰበት መጥቷል፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ የህግ የበላይነት አለ ማለት አይቻልም፤ለመብት ጥሰት ሳይጋለጡ ለመኖር የወያኔ ድርጅት አባል መሆን የግድ ሆኗል ብሏል።
እንደ መግለጫው በዘረኛው መንግስት ካድሬዎች ከህግ አግባብ ውጪ ዜጎች ይታሰራሉ፤ ከስራ ይፈናቀላሉ፤ንብረታቸው ይዘረፋል፤ በአጠቃላይ ግፍና በደል ይፈጸምባቸዋል።በመሆኑም መድረክ ህግ የት አለ? በወረቀት ላይ መኖሩ ፋይዳው ምንድነው? እንዲል ተገዷል።
የመድረክ መግለጫ በዘረኛው የወያኔ መንግስትና ሆድ አደር ካድሬዎቹ ተፈጸሙ ያላቸውን በርካታ በደልና ግፎች የዘረዘረ ሲሆን በተለይም የኦሮሞ ፌደራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅንቄ /ኦፌዴን/ በሚንቀሳቀስበት የኦሮሚያ አካባቢ እየተፈጸመ ያለውን ግፍ እጅግ ዘግናኝ ብሎታል።
በኦሮሚያ በቄለም ወለጋ ዞን፣በሀዋ ገላንና በሀዋ ወለል ወረዳዎች ውስጥ ሰላማዊ ዜጎችን ሌቦች በማለት የስርዓቱ ሚሊሻዎችና ፖሊሶች ከባድ ድብደባ እንደፈጸሙባቸው የሚያብራራው መግለጫው በተለይም ሰንበቶ ወዬሳ፣ይልቅ እስራኤል፣ደገፉ ሲርጋና ወሰኑ ዲሳሳ በተባሉ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ሰቆቃ ለአብነት ያነሳል።
እነዚህ ዜጎች በቅድሚያ ታስረው በፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል።በመቀጠልም ሰብዓዊ ክብራቸውን በማዋረድ በገበያ ውስጥ እየዞሩ እንዲገረፉ ተደርጓል።ይህም ይላል መግለጫው በ21ኛው ምዕት ዓመት ወያኔ ይህቺን ሀገር ወደ ጥንታዊው ኋላ ቀር ስርዓት እየወሰዳት መሆኑን አመላካች ነው።
በተመሳሳይም በሁዋ ወለል ወረዳ የጉራቴ ወለል ቀበሌ ነዋሪ የሆነው ረጋሳ ቲቾ በቶጂ ወረዳ ፖሊስ በደረሰበት ድብደባ ህይወቱ ማለፉንና በባለቤቷ ሞት የተበሳጨችው ወይዘሮ ተመስጌ ሊሙም በዕለቱ ራሷን ሰቅላ መሞቷ በመግለጫው ተብራርቷል።
መግለጫው በማያያዝም በቤንች ማጂ ዞን ምስኪን አርሶ አደሮችን በገፍና በግፍ ከመኖሪያ ቀዬአቸው በማፈናቀል የማባረሩ ርምጃ በአሁኒቷ ኢትዮጵያ የህግ የበላይነት ከስሞ ስርአት አልበኝነት የበላይነት ለመያዙ ዓይነተኛ ማስረጃ መሆኑን ጠቅሶ መድረክ ይህ ሁኔታ ሀገሪቱን ወደ አጠቃላይ ቀውስ ሊከታት ይችላል ብሎ እንደሚሰጋ ገልጿል።
በመጨረሻም መድረክ በመግለጫው የተቃውሞ ፖለቲካን ለማጥፋት የዜጎችን የግለሰብና የቡድን መብት እየረገጠ ያለውን የወያኔ ስርዓት በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ አግባብ ለመቀየር የሚያደርገውን ትግል በመደገፍ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገባ ለመላው ህዝብ ጥሪ አስተላልፏል።
በጉዳዩ ላይ አንድ የወያኔ ተቃዋሚ ድርጅት አባል በሰጡት አስተያየት ይህ ዘረኛና ግፈኛ የወያኔ መንግስት በቂም በቀል በመነሳት ህዝቡን በረሃብና በችግር ከመጥበሱ ባሻገር ሞራሉን በመስበር የመንፈስ ድቀት እንዲደርስበትና አንገቱን ደፍቶ እንዲገዛ ለማድረግ ተግቶ እየሰራ ነው።የግፍና የመከራ ብዛቱ ደግሞ ስርአቱ የፍጻሜው መጨረሻ ላይ መድረሱን አመላካች ነው።እናም ሁሉም ዴሞክራሲያዊ ሃይሎችና መላው ህዝብ ይህን ዘረኛና ግፈኛ የወያኔ ስርአት ለማስወገድ በጋራ መረባረብ ያለባቸው ወቅት ነው ዛሬ።ይህ ወቅት ካለፈ ግን የስቃይ መጠኑ እንደሚጨምርና ዘመኑም እንደሚረዝም ልብ ሊባል ይገባል ብለዋል።
source;http://www.ginbot7.org/2012/04/05/በኢትዮጵያ-ውስጥ-እየደረሰ-ያለው-የመብት/

No comments:

Post a Comment