Sunday, April 8, 2012

በኢንቨስት መንት ሥም ዜጎችን ከይዞታቸው የማፈናቀሉ ዘመቻ ቀጥሎአል። ከመሬታችን አንፈናቀልም ያለው የአፋር ህዝብ ከወያኔ መከላከያ ሰራዊት ጋር ተፋጧል


ለዜጎች ህይወትና ደህንነት ደንታ የሌለው የዘረኛው መለስ ዜናዊ አገዛዝ የአዋሽ ወንዝ ተፋሰስን የኑሮው መሰረት አድርጎ የኖረውን የአፋር ህዝብ ከቦታው በማፈናቀል የሸንኮራ ተክል ልማት ለማስፋፋት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ እንደገጠመው ለዝግጅት ክፍላችን የደረሰን መረጃ አመለከተ።
ካለፈው ሁለት ሳምንት ወዲህ እጅግ እየተጠናከረ በመጣው ህዝባዊ ተቃውሞ የተደናገጠው የወያኔ አገዛዝ ተቃውሞውን በሚያሰማ የአካባቢው ህዝብ ላይ ሰራዊት በማዝመት የሃይል እርምጃ እንደወሰደና በዚህም ምክንያት እርጉዝ ሴቶች፤ ወጣቶችና አዛውንቶች ሳይቀሩ የጥቃቱ ሰለባ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሎአል።
ተቀማጭነቱ ቤልጂዬም ብራስልስ የሆነው የአፋር ሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት ሃላፊ የሆኑት አቶ ገአስ አህመድ ኑር በክልሉ ህዝብ ላይ እየደረሰ ስላለው መብት ረገጣና መፈናቀል ለዝግጅት ክፋለችን ሲያስረዱ፤ ከህዝቡ ፈቃድና ፍላጎት ውጪ ህዝቡን ለኑሮውና ህይወቱ መሰረት ከሆነው የአዋሽ ወንዝ ተፋሰስ ክልል ለማፈናቀል በመወሰድ ላይ ያለውን እርምጃ የተቃወሙ ሁለት ነፍሰ ጡሮችን ጨምሮ 8 ሴቶችና ቁጥራቸው የበዛ ወንዶች ታስረዋል። በእስር ላይ እያሉና ወደ እስር ቤት ሲወሰዱ ድብደባ የተፈጸመባቸው ሰዎች ቁጥርም ቀላል እንዳልሆነ የገለጹት አቶ ገአስ የአካባቢው ተወላጆችን መኖሪያ በሃይል ለማፍረስ የተሰማሩ ዶዘሮችን ለማስቆም ሙከራ የሚያደርግ ማንኛውም ሰው ላይ በክልሉ የተሰማራው መከላኪያ ሰራዊት የፈለገውን እርምጃ እንዲወስድ መታዘዙን ከአካባቢው ምንጮቻቸው መረጃ እንደደረሳቸው ገልጸዋል።
በመከላኪያ ሠራዊቱና በህዝቡ መካከል በተፈጠረው ግብግብ ፍርሃትና ስጋት የገባው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በቦታው ያሰማራቸውን ዶዘሮች ለማስጠበቅ ያሰማራቸው ሃይሎች አንድ ኝጹህ ዜጋ ተኩሰው እንዳቆሰሉ ሆኖም ህዝቡ ለህይወቱና ለኑሮው ብቸኛ የሆነውን ይዞታውን አቅሙ እስከፈቀደ ድረስ ለመከላከል በህይወቱ ወስኖ እየተጋፈጠ እንዳለ ለማወቅ ተችሎአል።
ከአካባቢው በደረሰን ተመሳሳይ ዜና በዚህ የወያኔ ዜጎችን ከቦታቸው የማፈናቀል ዘመቻ ቁጥራቸው ከሰባ ሺ በላይ የሆነ የአፋር ህዝብ ይፈናቀላል ተብሎ እንደሚገመትና ይህንን ውሳኔ በተቃወመው የአፋር ህዝብና በአገዛዙ መካከል የተፈጠረው ፍጥጫ ተባብሶ ሌላ ያልተጠበቀ የህዝብ አመጽ ሊቀሰቅስ እንደሚችል ስጋት ፈጥሮአል።
የሙቀት ደረጃው ሃይለኛ በሆነው የአዋሽ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚኖረው የአፋር ህዝብ ለራሱና ለሚያረባቸው ከብቶች ህልውና ከአዋሽ ወንዝ ርቆ መኖር እንደማይችል ለዘረኛዉ መለስ ዜናዊና ለክልሉ ባለስልጣኖች ያቀረበው አቤቱታ ሰሚ ከማጣቱም በላይ አባ ጸሃዬ የተባለው የመለስ ዜናዊ ተቀጢያ “መንግሥት ከፈለገ የአዋሽን ወንዝ ሞጆ ላይ በመገደብ አካባቢውን ወደ ምድረ በዳነት የመለወጥ አቅም እንዳለው በመናገር ህዝቡን ለማስፈራራት መሞከሩን የአካባቢው ሽማግሌዎች ይናገራሉ።
በሽንኮራ ልማት ሥም ለዘመናት ተከብሮ የኖረውን የዋልድባ ገዳምን ይዞታ ወያኔ ለመውሰድ እያደረገ ያለው ጥረት ተመሳሳይ ተቃውሞ ማስነሳቱን መዘገባችን ይታወሳል። ለመለስ ዜናዊ አገዛዝ ባላቸው ቀረቤታና ታማኝነት ለኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓቲሪያርክነት የበቁት አባ ፓውሎስ የሚመሩት ሲኖዶስ በዋልድባ ገዳም የተፈጠረውን ጥቃት እንደማውገዝ ፋንታ አገር ያወቀውንና ጸሃይ የሞቀውን ሃቅ በመሸፋፈን “መንግሥት የዋልድባን ይዞታ እንደማይነካ አረጋግጦልናል” የሚል የተሳሳተ መግለጫ ባለፈው ሳምንት ማሰራጨታቸው ህዝበ ክርስቲያንን እያነጋገረ ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ የሚታየው የህዝብ መፈናቀል በመላ አገሪቱ ቁጣን እየቀሰቀሰ ነው። በደቡብ ኦሞ ከ200 ሺ በላይ ህዝብ መፈናቀሉን ተከትሎ ከፍተኛ የጸጥታ መደፍረስ እየታየ ነው። በጋምቤላም እንዲሁ በክልሉ ለሚታየው ተደጋጋሚ የጸጥታ ችግር ዋናው መንስኤ የህዝብ መፈናቀል ነው።
ዜጎችን ከድንግል መሬታቸውና ታሪካዊ ቦታዎቻቸው እያፈናቀሉ በህንድ በቻይናና በአረብ ከበርቴዎች የማስያዙን ጥረት ህዝባችን በሙሉ በአንድነት ሆ ብሎ ካላስቆመ በስተቀር የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ዘመኑን ጨርሶ ከስልጣን ሲወገድ አገራችን የምትከፍለው ዋጋ ቀላል እንደማይሆን ግንቦት 7 ሁሌም እያስጠነቀቀ መሆኑ ይታወቃል።
source ;http://www.ginbot7.org/2012/04/05/በኢንቨስት-መንት-ሥም-ዜጎችን-ከይዞታቸው/

No comments:

Post a Comment