Friday, July 27, 2012

በተቃዋሚው ጎራ ያሉት ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞችና ምሁራን ልሂቃን ልብ ሊሉት የሚገባ አበይት ታሪካዊና ተጨባጭ ጉዳዮች፡፡


በተቃዋሚው ጎራ ያሉት ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞችና ምሁራን ልሂቃን ልብ ሊሉት የሚገባ አበይት ታሪካዊና ተጨባጭ ጉዳዮች፡፡በተቃዋሚው ጎራ ያሉት ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞችና ምሁራን ልሂቃን የፈፀሙትና እየፈፀሙት ያሉ ታሪካዊና ተጨባጭ ነባራዊ ስህተቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡
1ኛ)የደርግን ስርዓት ያለአካሄዱ በማውገዝ የባእዳን ሃይሎችን ኒዎ-ኮሎኒያሊዝም ፕሮጀክት ለማስፈፀም በቅጥረኝነት ለተሰለፉት መለስ/ወያኔ እና ኢሳያስ/ሻእብያ በግዴለሽነትና ባለማስተዋል አሳልፎ መስጠት፡፡ከደርግ ጋር አብሮ መለስ/ወያኔ እና ኢሳያስ/ሻእብያን በሚቻለው ሁሉ ታግሎ ቢቻል ሙሉ በሙሉ አሸንፎ ባይቻል ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ አቅም አሳጥቶና አዳክሞና በአንድ ቦታ ገድቦና ይህ አይነት ስልጣን ላይ እንዳይወጡ በማድረግ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ደህንነትና ህልውና ካስጠበቁ በኋላ በደርግ ላይ ሪፎርም እንዲመጣ መዝመት ይቻል ነበር፡፡ይህ ቢሆን ኖሮ ከባለንጣዎቻችን መለስ/ወያኔ እና ኢሳያስ/ሻእብያ ጋር ደረትን ነፍቶ በእኩልነት የመደራደር ነገር ስለሚኖር ኢትዮጵያም የባህር በር የማግኘት ፍትሃዊና ተፈጥሯዊ መብቷን በሚያሳዝን ሁኔታ በሻጥር በመለስና ኢሳያስ አማካኝነት ባልተነፈገች ነበር፡፡ደርግን በሰይጣን የመመሰልና መለስ/ወያኔን በቅዱስ ዲሞክራት የመመሰል ቅዠትና አርቆ አለማሰብ ይኸው ዛሬ ይህንን ሁሉ ቀውስ አስከተለ፡፡
2ኛ)መለስ/ወያኔ የባእዳን ሃይሎችን ኒዎ-ኮሎኒያሊዝም ፕሮጀክት በረቀቀና በተቀነባበረ መንገድ ለማስፈፀም በቅጥረኝነት ከደደቢት በረሃ የተነሱ ሃይሎች መሆናቸው ተዘንግቶ ከእነዚህ ሃይሎች ዲሞክራሲና እድገት መጠበቅ፡፡ላለፉት 21 ዓመታት በውሸት ምርጫ ተቃዋሚውንና ምሁሩን ሁሉ የsuspense(ልብ አንጠልጣይ) ፊልም እየሰሩ እነደ ጡጦ እንደሚጠባ ህፃን ልጅ ቀለዱበት፡፡የሚገርመው ዛሬም ድረስ ስለ ምርጫ የሚያወራ ልብ ያልገዛ ልበ-ቢስ ተቃዋሚ መኖሩ ነው፡፡እውነቴን ነው ይህ አጠቃላይ ያለፉት 21 ዓመታት ክስተት እጅግ አሳፋሪና አሳዛኝ ነው፡፡
3ኛ)የተቃዋሚው ጎራና ፖለቲከኛና ምሁር ኤሊት የኢኮኖሚውን ጉዳይ ፈፅሞ ችላ ብሎት የውሸት የምርጫ ዲሞክራሲ ላይ መረባረብ ስራ ብሎ ተያያዘው፡፡በዚህ ምክንያትም መለስ/ወያኔ ከፊት ለፊት ዲሞክራሲ እያለ ከበስተጀርባ ግን በረቀቀና በተቀነባበረ መንገድ ከውጪ በእርዳታና ብብድር ከሚገኝ ዶላርና በማፍያ ስታይል የቢዝነስ ስራና ዝርፊያ እንደ ኢፈርት አይነቱን በቢሊዮኖች ደላር የሚቆጠር የኢኮኖሚ ኢምፓየር ለመመስረት ቻለ፡፡ከዚህ ስንነሳ የተቃዋሚው ጎራ ፖለቲከኛና ምሁር ኢኮኖሚውን ፈፅሞ ችላ ብሎት የኢትዮጵያ ህዝብ ምድራዊ ዳቦ ሳይሆን ሰማያዊ ህብስተ መና እየበላ የሚኖርና ዳቦ ያማያስፈልገው በውሸት የምርጫ ዲሞክራሲ በምርጫ ካርድ ብቻ የሚኖር አድርገው አሰቡት፡፡
4ኛ) ህብረ ብሄራዊ ስሜትን ከማዳበር ይልቅ ለወያኔ እና የእሱ አለቃ ለሆኑት ባእዳን ሃይሎች የዘር የሃይማኖት ወዘተ የከፋፍለህ ግዛው ስልት ዋና አስተባባሪና ተባባሪ ሆኖ መገኘት፡፡ወያኔም ሆነ ሌሎች ባእዳን ሃሎች ተራውን ህዝብ በዘር በሃይማኖት ለመከፋፈልና እረስ በርስ ለማናከስ ቅድሚያ መነሻ መንደርደሪያ የሚያደርጉት የተማረውን ኤሊት በጥቅማጥቅምና በስልጣን በመያዝና በመሸበብ ነው፡፡
5ኛ)የመለስ/ወያኔን እውነተኛና ተግባራዊ እየሆነ ያለ ድብቅ አይዲሎጂ አለመረዳት፡፡መለስ ወያኔ በዋናነት በእስትራቴጂ ደረጃ የባእዳን ሃይሎችን ግሎባል-ካፒታሊዝም ኒዎ-ሊበራል ፖሊሲ እና ኒዎ-ኮሎኒያሊዝም ፕሮጀክት ለማስፈፀም በቅጥረኝነት የተሰለፈ ሃይል ነው፡፡ሌሎች እንደ ማሌሊት፣አብዮታዊ ዲሞክራሲ፣ ኢህአዲግ(ኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር)፣ልማታዊ መንግስት፣እድገትና ትራንስፎርሜሽን ወዘተ ሁሉ በራሳቸው በጊዚያዊነት እንደ እስስት ስም እየቀያየረ የሚጠቀምባቸው ስልታዊ አካሄዶች ሁሉ ታክቲካዊ እንጂ እስትራቴጂካዊ ግቦች አይደሉም፡፡መለስ/ወያኔ ለባእዳን ቅጥረኝነት እንዲሰለፍ ያደረጉት ውስጣዊ ድብቅ ምክንያቶች ደግሞ ከዘመነ ጣሊያን ወረራ፣ ከአድዋ ድል ጋርና ከዘመነ አፄ ምኒልክና በተከታይ ከነበሩት የአማራ ነገስታት አገዛዝ ጋር የተያያዘና ይህንንም አንድ ወቅት እንደ ተስፋ ኪዳን ደስታ አይነት ወያኔዎች “የትግራይ ህዝብ ታሪክና የትምክህተኞች ሴራ” በሚል መፅሀፍ ውስጥ ቁልኝ ተብሎ ተፅፏል፡፡በእርግጥ ደርግ እራሱ ይከተለው የነበረው የሶሻሊስት አይዲኦሎጂ በምእራባውያን ዘንድ ከቀዝቃዛው ጦርነት ጋር በተያያዘ እንዲወገድ ስለሚፈለግ ምእራባውያን መንግስታት መለስ/ወያኔ እና ኢሳያስ/ሻእብያን በመርዳት በደርግ ላይ የትጥቅ ትግል አድርገው እንዲዘምቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ስለዚህም መለስ/ወያኔ እና ኢሳያስ/ሻእብያ በነፃነት ትግል ሽፋን ወደ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ በዚህ አይነት ሁኔታ መከሰት በአንድ በኩል የጥንቱ ኮሎኒያሊዝም አሻራ ያለበት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በአይዲኦሎጂ ደረጃ የግሎባል ካፒታሊዝም ኒዎ-ሊበራል ፖሊሲና ይህንንም ለማስፈፀም በተያያዥነት ያለው የኒዎ-ኮሎኒያሊዝም ተፅእኖ ያለበት ነው፡፡የተቃዋሚው ጎራም ዲሞክራሲ የሚባለውን ነገር እነ መለስ/ወያኔ ሆነኝ ብለው ለማሳሳትና ለማዘናጋት አስበው ስላወሩት ብቻ እውነተኛ ድብቅ ማንነታቸውን በቅጡ ሳይረዳ ይህንን እንደ ሞኝ ሆ ብሎ ተከትሎ ከእነሱ ጋር አብሮ በዚህ ስሜት ማጫፈሩና የዲሞክራሲ ፌሽታ ሊያደርግ ማሰቡና መድከሙ ትልቅ ልበ-ቢስነትና አርቆ አስተዋይነትን ማጣት ነበር፡፡
6ኛ) እነሆ ዛሬ 21 ዓመታትን አሳልፈን የመለስ/ወያኔም ስርዓት እየበሰበሰ መጥቶ ሊወድቅ እየተንገዳገደ ያለበት ደረጃ ላይ ደርሶ እነሆ ዛሬ እዚህ ቀውጢ ሰዓት ላይ ደረስን፡፡የመለስ/ወያኔም ስርዓት በህገ-አራዊት የሚመራ አረመኔ ይለሰለጠነ ስብስብ ነው፡፡የመለስ/ወያኔ ስብስብ ስልጣንን በሕይወት ውስጥ ያለ የመጨረሻ ደረጃ የሞት የሽረት ትግል አድርጎ የተያያዘው እብድ ስርዓት ነው፡፡ነገር ግን ቀላል የማይባሉ የተቃዋሚው ጎራ ሃይሎች ይህንን ስርዓት በሰላማዊ ትግል ብቻ እንደሚገረሰስ አድርገው በማየት ነገሮችን ለራሳቸው በሚመቻቸው መንገድ አቅለው ለማየት የሚፈልጉ አሉ፡፡እንደዚሁም ሌሎች ነገሩን አክብደውት በተቃራኒው የለም በትጥቅ ትግል ነው ይህ ስርዓት ሊወገድ የሚችለው ይላሉ፡፡ጥቂቶች እንደ ግንቦት ሰባት አይነቶች ደግሞ ማንኛውንም አማራጭ በመጠቀም ነው ይላሉ፡፡ሙሉ በሙሉ የግንቦት ሰባት ደጋፊ ወይንም ተቃዋሚ ባልሆንም ቅሉ ግን እንደ ትክክለኛና ተገቢ ጤናማ አማራጭ ግን ይህ አስተዋይነት ያለው እንደሆነ ይሰማኛል፡፡በመሳሪያ የተደገፈና የታጠቀ አንድ የተወሰነ ደረጃ ያለው የተዘጋጀ ወታደራዊ ሃይል መመስረት ግን ግድ የሚለው የግድ ለመገዳደልና ለመጠፋፋት ብቻ አይደለም፡፡ሀገርንና ህዝብን በዚህ አይነት ቀውጢ ወቅት እንደ አማራጭ ሆኖ ለማረጋጋትና ሰላም ለማስከበርም ጭምር እጅግ ወሳኝነት አለው፡፡እንደሚታወቀው መለስ/ወያኔ የሀገሪቱን አጠቃላይ ወሳኝ የሆኑትን የደህንነት፣የስለላ፣የሚሊታሪ፣የኢኮኖሚ፣የፖለቲካ፣የቢሮክራሲ ቴክኖክራት፣ ወዘተ ሁሉ በአብዛኛው ከአንድ ዘር በተውጣጣ የትግሪኛ ተናጋሪ ማህበረሰብ ስብስብ በሞኖፖል ነው የተቆጣጠሩት፡፡ይህ አይነት ስርዓትና ሁኔታ በሰፈነበት ሀገር ውስጥ ይህ ግባ የሚባል ተጨባጭ ተፅእኖ ለመፍጠር የማይችል ሰላማዊ ትግል ለማካሄድ ማሰብ እንዲያው በተጨባጩ አለም ውስጥ ሳይሆን ፍፁም ሰላማዊ የሆነ ገዳም ውስጥ እንደምንኖር ነው የሚያስመስለው፡፡ስለዚህም ነገሮችን ጫፍና ጫፍ በረገጠ በነጭና በጥቁር ማየት መቆም አለበት፡፡ማለትም በአንድ ጫፍ የለየለት ንፁህ ሰላማዊ ትግል ወይንም በተቃራኒው የለየለት ንፁህ የትጥቅ ትግል በሚል ጫፍና ጫፍ የረገጠ በነጭና በጥቁር ማሰብ ተገቢ አይደለም እንደዚሁም ለነባረዊው ተጨባጭ ሁኔታ አይስማማም፡፡አንዳንዶች ይህ የመለስ/ወያኔ ስርዓት እጅግ አጥብቆ የሚፈራው ንፁህ ሰላማዊ ትግል ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ በተቃራኒው የለም የመለስ/ወያኔ ስርዓት እጅግ አጥብቆ የሚፈራው ንፁህ ሰላማዊ ትግል ነው ይላሉ፡፡ሁለቱም የኢትዮጵያን ያለፈ ታሪክና አሁን ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘበ እይታ ነው፡፡ለምሳሌ ንጉሱ ሃይለስላሴ በሚሊታሪው የደርግ ስብስብ ሃይል ከስልጣን ሲወገዱ ምንም አይነት የትጥቅ ትግልና ደም አፋሳሽ ጦርነት አልተካሄደም ነበር፡፡የተካሄደው በአንድ በኩል መፈንቅለ መንግስት ነበር፡፡ንጉሱም የእኔ ስልጣን መልቀቅ ለኢትዮጵያ ይበጃል ካላችሁና የሚበጅም ከሆነ ስልጣኔን እለቃለሁ ነበር ያሉት፡፡ስለዚህም ደርግ ሚሊታሪውን መቆጣጠር ስለቻለ የስርዓት ለውጥ ማምጣት ችሎ ነበር፡፡ስለዚህም አንድን ስርዓት ከስልጣን ለማስወገድ(ማስወገዱ ተገቢ ነው አይደለም የሚለው እንዳለ ሆኖ) የግድ አዲስ የሚሊታሪ ሃይል ለመመስረት ግድ የማይልበት ሁኔታ አለ ማት ነው፡፡በደርግ እና በወያኔ ያለው ትግል ጋር ስንመጣ ግን ለስርዓት ለውጥ በሁለቱም ወገን የተካሄደውን እጅግ መራር የ17 ዓመታት የትጥቅ ትግልና ይህንንም ተከትሎ የተከፈለውንና የጠፋውን የሰው ህይወትና የንብረት ጉዳይ ሁላችንም የምናውቀው ነገር ነው፡፡ስለዚህም የጦርነትን አስከፊነት ሁላችንም እንረዳዋለን፡፡ስለዚህም ያ አይነት ቅስም ሰባሪና አውዳሚ ጦርነት ዳግም እንዲመጣ ማንም ጤነኛ አእምሮ ያለው ሰው አይፈልግም፡፡ነገር ግን መለስ/ወያኔ ይህንን ጤናማ ማህበረሰባዊ አስተሳሰብ በራሱ መንገድ እየጠመዘዘ ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትልውድ ወዘተ እያለ ለራሱ የፖለቲካና የስነ-ልቦና ጥቅም እየተጠቀመበት ነው፡፡ማለትም ከዚህ በኋላ እኔን ማንም በሚሊታሪ ሃይል የሚገዳደረኝ ሃይል አይኖርምና ስለዚህም የኢትዮጵያን ህዝብ ለዘላለም እንደፈለግሁኝ እረግጬ እየዘረፍኩኝ ዲሞክራሲ ወዘተ እያልኩኝ እያምታታሁኝ ለመኖር እችላለሁ ወደሚል እብሪት እብደትና ቅዠት ውስጥ በመግባት ማለት ነው፡፡እነ ስዬም አንድ ወቅት ጦርነትን መዋጋት ብቻ ሳይሆን መፍጠርም ጭምር እንችላለን እስከማለት ደረሱ፡፡የመለስ/ወያኔ አጠቃላይ ይህ አይነት በህዝብ ላይ የሚታይ ስር የሰደደና የተስፋፋ እብሪትና ንቀትም አንዱ ከዚህ የሚሊታሪ ታሪካዊና ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በእጅጉ የተያያዘ ነው፡፡የመለስ/ወያኔ ጠባብ ስብስብ በወንድማማች ህዝቦች መካከል የነበረን የእርስ በርስ የትጥቅ ትግል ልክ የውጪ ባእዳዊ ፍልሚያ እስኪመስል ድረስ እየለጠጠ ይህ ስብስብ እራሱን እንደተለየ ጀግና በመቁጥር በአርዓያ ስላሴ የተፈጠሩ ሰዎችን “ሽንታም አህያ ገና ትረገጣለህ ገና ትገዛለህ” እስከማለት በደረስ ስብእናን እጅግ የሚያዋርድ ክብረ ነክ ንግግር እስከመናገር የደረሰ እብሪተኛና ያልሰለጠነ በህገ-አራዊት የሚመራና እራሱ ጭምር የወጣበትን ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ ጭምር የዘነጋ ግብዝ ሃይል እየሆነ መጣ፡፡ይህ አይነት ክብረ-ነክ ንግግርም በቀጥም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚያሳየው ነገር መለስ/ወያኔ ኢትዮጵያውያንን ሆነኝ ብሎ ለማሸማቀቅ ለማዋረድ አንገት ለማስደፋት የኢትዮጵያውያንን በራስ ማንነት መተማመን የማይፈልጉ የባእድ ሃይሎች ቅጥረኛ ሃይል መሆኑን ነው፡፡ይህንን ሁሉ ያልኩት የመለስ/ወያኔ ስርዓት የደርግን ስርዓት ሲያስወግድ ወታደሩን በጥቅላላ በመበተን ወሳኝ በሆነ ሁኔታ የሚሊታሪውንና የደህንነቱን ስርዓት በራሱ የብሄር ስብስብ በሞኖፖል ነው የተቆጣጠረው፡፡ስለዚህም ይህ አይነት አሻፈረኝ ያለ እብሪተኛ ሃይል በባዶ እጅ በጩኸት ብቻ የሚበረግግና ለድርድርም በጠረጴዛ ዙሪያ በቀላሉ የሚቀመጥ ይሆናል ብሎ ለመተማመን እጅጉን አስቸጋሪ ነው፡፡ይህ ሃይል ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን እንደ ጦር ምርኮኛና ግዞተኛ የሚያይ እብሪተኛ ሃይል ነው፡፡የሰለማዊ ትግል ብቻ ነው ተገቢው አማራጭ የሚሉት ሃይሎች የሀገራችንንም ሆነ የአጠቃላዩን አለም ታሪካዊና ተጨባጭ ነባራዊ እውነታውን ለመጋፈጥ የማይፈልጉ ናቸው፡፡ቢያንስ እንደ ተመጣጣኝ ሃይል በሰለጠነ መንገድ ለመደራደር ከባዶ ቃላት በዘለለ የተወሰነ ተፅእኖ ለመፍጠር የሚችል ሃይል(እውነት እውቀት ሚሊታሪ ገንዘብ የሰው ሃይል ወዘተ የተለያየ አይነት) ያስፈልጋል፡፡የተቃዋሚው ጎራ መለስ/ወያኔን አስገድዶ ለተገቢ ድርድር የሚያመጣ ምን አይነት ተጨባጭ ሃይል ነው?መለስ/ወያኔን የሚደግፉት ምእራባውያን መንግስታት በራሳቸው ለተቃዋሚው ጎራ ያላቸው ግምት ከእነዚህ ነገሮች ጋር ጭምር የተያያዘ ነው፡፡ስለዚህም እረጅም ጦር ባይወጉበት ያስፈራሩበት አይነት ነውና የተቃዋሚው ጎራ እራሱንና የተቀረውንም የኢትዮጵያንም ህዝብ ለማስከበርና ለመታደግ እንደዚሁም ሰላምና መረጋጋትን በአማራጭነት እንደ አስፈላጊነቱ ለማስፈን እንደ አቅሙ የግድ አንድ የተወሰነ የሚሊታሪ ሃይል ያስፈልገዋል፡፡ይህ ሲሆን ነው ከመለስ/ወያኔ ስብስብ ጋር ማንኛውንም ገንቢ ድርድር ለማድረግ የሚቻለው፡፡እንደ ግንቦት ሰባት አይነቶች በመርህ ደረጃ ማንኛውንም አይነት አማራጭ ያሉትን ትክክለኛና ተገቢ አካሄድና እይታ አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ሲታይ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
አለው፡፡እንደሚታወቀው መለስ/ወያኔ የሀገሪቱን አጠቃላይ ወሳኝ የሆኑትን የደህንነት፣የስለላ፣የሚሊታሪ፣የኢኮኖሚ፣የፖለቲካ፣የቢሮክራሲ ቴክኖክራት፣ ወዘተ ሁሉ በአብዛኛው ከአንድ ዘር በተውጣጣ የትግሪኛ ተናጋሪ ማህበረሰብ ስብስብ በሞኖፖል ነው የተቆጣጠሩት፡፡ስለዚህም ከዚህ አይነት ሃይል ጋር ስርዓት ለመቀየር የሚደረግ ትግል እልህ አስጨራሽና ፈታኝ ነው የሚሆነው፡፡ይህ ሆኖ እያለ የተቃዋሚው ጎራ የመለስ/ወያኔን ስርዓት ሃጢያት ከመናዘዝ ባለፈ ይህ ነው የሚባል ትርጉምና ፋይዳ ያለው የራሱን ውስጣዊ ጥንካሬና ሃይል በተገቢው መንገድ አልገነባም፡፡አንድ ወቅት ኤድሞንድ ብሩክ “All that is necessary for the triumph of evil is that good men do nothing.” እንዳለው የመለስ/ወያኔ አገዛዝ አስከፊነት በአንድ በኩል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከመለስ/ወያኔ ስብስብ ውጪ ያለው ሃይል ደካማነት መገለጫ ነው፡፡አንድ እኩይና መጥፎ ስብስብ ሃይል ኖሮት በሌላው ስብስብ ላይ በበላይነት ሃይል ኖሮት ለመሰልጠንና ለመጨቆን ለማሰቃየት ለመበደል የሚችለው ይህንን ተዋግቶና ሃይ ብሎ ለመታገልና ለማሸነፍ የሚችል የመልካምና የቅዱስ ሃይል ስብስብ ሲጠፋ ወይንም ሲደክም ነው፡፡በተቃዋሚው ጎራ ያሉት ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞችና ምሁራን ልሂቃን ታሪካዊ ስህተት መለስ/ወያኔ እንደዚሁም ኢሳያስ/ሻእብያ እባብ ሆነው ሳለ እርግብ እንደሆኑ አድርጎ ማሰቡና መጠበቁ ነው፡፡መለስ/ወያኔ ዲሞክራሲን አላሰፈኑም ነፃነታችንን ነፈጉን አሰሩን ገደሉን ጨቆኑን አሰደደዱን ዳቦ ከለከሉን ወዘተ ወዘተ አይነት የተለመደ የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ አይነት አካሄድ ከእባብ ዘንድ የእርግብ እንቁላል ወይንም ከዝንብ የንብ ማር የመጠበቅ ያህል ነው፡፡ስለዚህም ይህ እራስንና ሌላውን ህዝብ የመዋሸት አካሄድ መቆምና ወደ ነባራዊው እውነታ መምጣት ተገቢ ነው፡፡መለስ/ወያኔ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ስለ እውነተኛው ድብቅ ማንነታቸው እየነገሩን ነው፡፡እኛ ግን እንዲገባን የምንፈልግ አይነት አልሆነም እንጂ፡፡በቅርቡ በረከት ስምኦን የመለስን የጤንነት ሁኔታ በሚመለከት ለምን ለህዝብ ይፋ አይሆንም ሲባሉ ይህ የህውሃት የበረሃ ትግል ህይወት ልምድ አካል ነው ነበር ያሉት፡፡ከዚህ አባባል የምንረዳው እነዚህ ሰዎች አንድ ትልቅ ሀገርና ህዝብ ፍቅር አክብሮት ታማኝነት ግልፅነትና ሃላፊነት እንደሚሰማው ሃይል ሆነው እየመሩ አለመሆኑንንና ይህንንም ለማድረግ ብቃትና ፍላጎት እንደዚሁም የመንግስትነት ባህሪና ይዘት እንደሌላቸው መሆኑን ነው፡፡በመለስ/ወያኔ አስተሳሰብ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ድል የተደረጉ የጦር ምርከኛና ግዞተኛ እንደዚሁም የተዘዋዋሪ ዘመናዊ ቅኝ ግዛት ናቸው ያልኩትም ለዚህ ነው፡፡ስለዚህም ከዚህ በኋላ የተቃዋሚው ጎራ ማንኛውንም ልዩነቱን ወደ ጎን ትቶ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ከመበታተን ለመታደግ በቁርጠኝነት መነሳትና ይህንንም ለማሳካት አንድ የተወሰነ ቢያንስ ሰላም ለማስከበር የሚችል የታጠቀ ወታደራዊ ሃይል ሊኖረው ግድ የሚልበት ወሳኝ ወቅት ነው፡፡ይህ ካልሆነ ግን ሌላ እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ ታሪካዊ ስህተት ነው የሚሆነው፡፡መለስ/ወያኔ እንደ ባእዳን ቅጥረኝነታቸው በእኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አይነት እኩይ አስተሳሰብ ይህችን ሀገርና ህዝቦቿን የማያባራ ያለመረጋጋትና ቀውስ ውስጥ ከተው ለመፈትለክ አስበውስ ከሆነ እንዴት ነው ይህ እንዳይሆን ለመከላከል የሚቻለው?ሃይል እውነት ነው ሲባልም ተገቢና ሞራላዊ ሃይልን በተገቢው ሞራላዊ መንገድ መጠቀም ግድ የሚልበት ሁኔታ አለ ለማለት ጭምር ነው፡፡ከዚህ ውጪ ግን የራስን የቤት ስራ በቅጡ መስራትን ችላ ብሎ መለስ ኮማ ውስጥ ነው መለስ ሞቷል መለስ ከዚህ በኋላ ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ አመራር መስጠት አይችልም ወዘተ አይነት በመለስ/ወያኔ ስብስብ ላይ ስላለ ሁኔታ ብቻ ማተኮር ለዘለቄታው ብዙም የሚጠቅመው ነገር የለም፡፡የተቃዋሚው ጎራ ሃይል የሀገርና የህዝብ አለኝታነት የሚለካው የመለስ/ወያኔን ስርዓት ማንነትና ሃጢያት በማውራት ላይ ባተኮረ አካሄድ አይደለም፡፡የመለስ/ወያኔን ስርዓት ማንነትና ሃጢያት ከሆነማ የኢትዮጵያ ህዝብ ላለፉት 21 ዓመታትና አሁንም ጭምር በተግባር በእለት ተእለት ሕይወቱ እያየውና እየኖረበት ያለ የገፈቱ ቀማሽ ነው፡፡አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የተቃዋሚው ጎራ ሃይል የሀገርና የህዝብ አለኝታነት የሚለካውም ማናቸውንም ልዩነቶችን ለጊዜው አክብሮና ወደ ጎን አስቀምጦ አንድ ጊዚያዊ አንድነት(Grand National Coalition) ድርጅት ፈጥሮና በዚህም ድርጅት አማካኝነት አንድ የተወሰነ ጊዚያዊ ሰላም አረጋጊ የሚሊታሪ ሃይል አደራጅቶ ኢትዮጵያን ከመበታተን አደጋ ለመታደግ ሲችል ነው፡፡ይህንን ማድረግ እስካልተቻለ ድረስና ይህ ባለመሆኑም የመለስ/ወያኔ የበሰበሰ ስርዓትን የማይቀር ውድቀት ተከትሎ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ የሆነ አደገኛ አለመረጋጋትና ቀውስ ከተፈጠረ ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞችና ምሁራን ታራካዊ ግዴታቸውን እንዳልተወጡና በዚህም የተነሳ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ተገቢውን የቅቡልነትና የክብር ቦታ እንደማያገኙ ነውና ከዚህ በኋላ በራሳቸው Theoretical የቅዠት አለም ውስጥ ሆነው ዲሞክራሲ ገለመሌ እያሉ ሀገር ለመምራት ባይሞክሩ መልካም ነው፡፡የፓርቲ ፖለቲካና የምርጫ ዲሞክራሲም ጨዋታ ሊቀጥል የሚችለው መጀመሪያ ሀገርና ህዝብ ሉአላዊነቱ ተረጋግጦና ተከብሮ ብሄራዊ ህልውና ደህንነትና ሰላም መስፈን ሲችል ብቻ ነው፡፡ስለዚህም ሀገርና ህዝብ ለማረጋጋትና ሰላም ለማስፈን እንዲቻል በተቻለው ፍጥነት ሁሉ አንድ አማራጭ ወታደራዊ ሃይል ማደራጀት ግድ ይላል፡፡ከዚህ ውጪ ግን ምን ሊያደርግ እንደሚችል በቅጡ ያልታወቀ የመለስ/ወያኔን ከአንድ በሄር የተውጣጣ ዘረኛና አረመኔ አግአዚ ወታደር አምኖ ሰላማዊ ትግልም ሆነ ሀገርና ህዝብን በተረጋጋ ሁኔታ ሰላምና ደህንነቱን አስጠብቆ ለማስቀጠል ከፍተኛ አደጋ አለው፡፡በዚህ አማራጭ ጊዚያዊ ወታደራዊ ሃይል መጥፋት የተነሳ በዚህች ሀገር ላይ ከፍተኛ አለመረጋጋትና ቀውስ ከተፈጠረ ደግሞ የተቃዋሚው ጎራ የሚፈፅመው 6ኛው ታሪካዊ ስህተት ይሆናል ማለት ነው፡፡ይህ ታሪካዊ ስህተት እንደማይፈፀም ግን ተስፋ አደርጋለሁኝ፡፡አበበ ገላው መለስን በድንገተኛ የተቃውሞ ንግግሩ ቀልባቸውን ገፎ ማስደንገጡ በራሱ አንድ ጥቅምና ትርጉም ያለው ትልቅ ጀግነነት ቢሆንም ቅሉ ግን የተቀረው የወያኔ ስብስብ ግን በአበበ ገላው አይነት አካሄድ ወይንም በሌሎች ምሁር በሆኑ በዶክተሮች ወይንም በፕሮፌሰሮች አንደበተ ርቱእ ንግግር ብቻ በቀላሉ በርግጎና ተሸንፎ የሚሸሽ ወይንም ለተገቢ ገንቢ ድርድር በቀላሉ የሚሸነፍ ስብስብና ሃይል አይደለም፡፡ስለዚህም ከሰላማዊ ትግሉ በተጓዳኝ እረጅም ጦር ባይወጉበት ያስፈራሩበት አይነት ነውና እራስን ለማስከበርና ለመፈራት የተቃዋሚው ሃይል ቢያንስ ቆመህ ጠብቀኝ ያለው የተወሰነ የተደራጀ ወታደራዊ ሃይል እንዲኖረው ግድ ይላል፡፡ይህ ካልሆነ ግን ወያኔ በእኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አይነት ቀቢፀ ተስፋ አካሄድ ተመርቶ ያለማንም ተቀናቃኝና ሃይ ባይ ሀገሪቱን እንደፈለገው የአለመረጋጋትና ቀውስ አውድማና መፈንጫ ሊያደርጋት ይችላል፡፡
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!!!

Source; comment from   http://www.abugidainfo.com/index.php/20537/

No comments:

Post a Comment