Saturday, August 4, 2012

የመኢአድ ም/ፕሬዚዳንት፣ ዶ/ር ታዲዮስ ቦጋለ ከእስር ተለቀቁ


አውራምባ ታይምስ(አዲስ አበባ) – ከኢ/ር ኃይሉ ሻውል ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ድርጅቱ እንዳይጠቀምበት በተከለከለ ክብ ማህተም ተጠቅመዋል በሚል አንድ ዓመት ከስምንት ወራት ጽኑ እስራት ተፈርዶባቸው በእስር ላይ የቆዩት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ምክትል ፕሬዚዳት ዶ/ር ታዴዎስ ቦጋለ ከእስር ተለቀቁ፡፡
ዶ/ር ታዴዎስ ቦጋለ (ፎቶ አውራምባ ታይምስ)
ዶ/ር ታዴዎስ የመኢአድ ገንዘብ ያዥና የመዝገብ ቤት ኃላፊ ከነበሩት አቶ ግርማ ነጋ ጋር በመሆን በህገወጥ ማህተም መጠቀማቸው ወንጀል መሆኑን በመግለጽ በ2003 ዓ.ም መጀመሪያ ኢ/ር ኃይሉ ለዓቃቤ ሕግ አቤቱታ ያቀርባሉ፡፡ ዓቃቤ ሕግ ማመልከቻውን በማየት እነ ዶ/ር ታዴዎስ የወንጀል ሕግ ተላልፈዋል በማለት በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት  ክስ ይመሠርታል፡፡ ፍርድ ቤቱም ክሱን በመመልከት ተከሳሾቹ ‹‹ጥፋተኛ ናቸው›› በማለት ዶ/ር ታዴዎስን በሁለት ዓመት ከአራት ወር፣ አቶ ግርማን ደግሞ በአንድ ዓመት ከስምንት ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ይወስናል፡፡
ዶ/ር ታዴዎስና አቶ ግርማ የሥር ፍርድ ቤት የቅጣት ውሳኔን በመቃወም ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ ቢሉም፣ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ ያሉበትን የግራና ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ የሥር ፍርድ ቤት ‹‹ጥፋተኛ ናቸው›› ያለውን በማፅናትና ቅጣቱን በማሻሻል፣ ዶ/ር ታዴዎስን አንድ ዓመት ከስምንት ወራት ጽኑ እስራት፣ አቶ ግርማን ደግሞ በአንድ ዓመት ከሁለት ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ሰጠ፡፡ በዚህ መሰረት አቶ ግርማ የ14 ወራት እስራታቸውን ጨርሰው ከሦስት ወር በፊት ሲለቀቁ ዶ/ርታዲዮስ ደግሞ ከ17 ወራት እስር በኋላ ሐምሌ 5 ቀን 2004 ዓ.ም. ከእስር ቤት ተለቀዋል፡፡
ዶ/ር ታዲዮስ ምርጫ 97 ትን ተከትሎ በተፈጠረው አለመግባባት ከሌሎች የቅንጅት አመራሮች ጋር ህገ መንግስቱንና ህገመንግስታዊውን ስርአት በሀይል ለመናድ ሞክረዋል በሚል ታስረው በይቅርታ መፈታታቸው ይታወሳል፡፡ ‹‹ሊቀመንበሩ  ፓርቲያቸው ውስጥ የተፈጠረውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ መፍታት ሲችሉ የትግል አጋራቸውን ለአህአዴግ አሳልፈው መስጠታቸው ክህደት ነው›› በማለት በርካታ ተቃዋሚዎች በወቅቱ ኢንጅነሩን ማውገዛቸው ይታወሳል፡፡

No comments:

Post a Comment