Thursday, August 2, 2012

የድል መዳረሻ ላይ ነን፤ ትግሉን ተቀላቀሉ!!!


    ለፍትህ፣ ለእኩልነት፣ ለነፃነትና ለዲሞክራሲ የምናደርገው ትግል ወደ ድል ተዳርሷል። ትግላችን ከእስልምና ወይም ክርስትና አድማስ ወጥቶ የኢትዮጵያዊያን ሁሉ ትግል እየሆነ ነው። መስጊዶች የትግል ማዕከል እንደሆኑ ሁሉ ቤተክርስያኖችም በተመሳሳይ የትግል ማዕከል ይሆናሉ። በአመቸን ቦታ ሁሉ ተቃውሞዓችን እናሰማለን። የተንገዳገደው የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ ጨርሶ እስኪወድቅ ድረስ በየእለቱ ትግላችንን እያጠነከርን እንሄዳለን። ወደ ድላችን መዳረሻ ላይ እንገኛለን፤ ተቀላቀሉን።
የትግላችን አጨራረስ የግብጽን ይምሰል ወይም የሊቢያ ለጊዜው የለየለት አይመስልም። እኛ ግን ለሁለቱም ተዘጋጅተናል።
ባለፈው ዓርብ የሮመዳን ወር የመጀመሪያው ቀን በአዲስ አበባ አንዋር መስጊድ አካባቢ ተገኝቶ  በሚያስገርም ድርጅታዊ ብቃት ተቃውሞውን በፀጥታ የገለፀው ሰው ብዛት በግብጽ ታህሪር አደባባይ ከነበረው የሚተናነስ አልነበረም። እርግጥ ነው የኢትዮጵያዊያኑ ተቃውሞ  የግብጹን አንድ መቶኛ ያህል እንኳን የሚዲያ ትኩረት አልሳበም። በብዛት አኳያ ሲታይ ግን በሰሜን አፍሪቃና መካከለኛ ምሥራቅ ከታዩት ሕዝባዊ አመጾች ሁለተኛውን ደረጃ ይይዛል።  ይህ እጅግ ተስፋ የሚሰጥ ነገር ነው። በሚቀጥሉት ሣምንታት ይህ ተስፋፍቶ እንደሚቀጥል ይጠበቃል። ክስተቱ በሚዲያ ረገድ ያለብንን ጉድለት አጉልቶ ያሳየ በመሆኑ እያንዳንዱ ታጋይ በራሱ ጋዜጠኛ የመሆኑ ሃቅ ግንዛቤ ሊያገኝ ይገባል።
ከዓርቡ ትዕይንት በማግሥቱ ቅዳሜ የታየው የጅምላ እስር፣ ድብደባና ወከባ ደግሞ ሊቢያን የሚያስታውስ ነበር። እርግጥ ነው የፀጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ ውስጥ እየተደረገ ስላለው ጉዳይ ነገሬ ብሎም አልተመለከተውም። የፀጥታው ምክር ቤት ለሊቢያ የሰጠውን ትኩረት ለኢትዮጵያም ይሰጣል የሚል ብዥታ የለንም። እኛን የሚያዋጣን በገዛ ራሳችን ኃይል እና ጉልበት መተማመን እንደሆነ አሳምረን እናውቃለን። በዚህም ረገድም ሥራዎች እየተሠሩ ነው።
ንቅናቄዓችን አባል የሆነበት ጥምረት ለነፃነት፣ለእኩልነት (ጥምረት) እና በጄኔራል ከማል ገልቹ ከሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውን የሚገልጽ የጋራ መግለጫ አውጥተዋል። ጥምረት ከሌሎችም የዲሞክራሲ ኃይሎች ጋር እያደረገ ያለው ውይይት ወደ ስምምነት እየቀረበ ነው። እነዚህ  ውይይቶች የትግሉ ራሱን የመከላከል አቅም ያጎለብታሉ ተብሎ ይታመናል።
ይህ የሚያሳየው ትግላችን ወደሚያደርሰን ቦታ በቆራጥነት ለመሄድ መዘጋጀታችን ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብም በእነዚህ ከፍተኛ መነቃቃት እያሳየ ነው። ፍርሃት ተሰብሯል። የመለስ አገዛዝ ማፈግፈግ ጀምሯል። ድልን እስከምንጨብጥ ድረስ ግን ማጥቃታችን ይቀጥላል።
ትግሉ የጠየቀንን ሁሉ ለመክፈል እኛ ዝግጁዎች ነን።
ትግላችን በሰላማዊ መንገድ እንደተጀመረ በሰላማዊ መንገድ ቢያልቅ ምኞታችን ነው። ይህ ምኞት ማሳካት የሚቻለው ግን በተለይም ከዚህ በታች የተዘረዘሩ ወገኖች ተገቢውን እርምጃ አሁኑኑ ከወሰዱ ነው።
  1. ፍትህን፣ ነፃነትን፣ እኩልነትንና እውነተኛ ዲሞክራሲን ስትመኙ የኖራችሁ፤ ሆኖም ግን የሥራ ግዴታ  ሆኖባችሁ በአገዛዙ ሠራዊት አባልነትም ሆነ በአመራር የምትገኙ ወገኖቻችን አገዛዙን በይፋ በመክዳት የሕዝብ አጋር መሆናችሁ የምታረጋግጡበት ወቅት አሁን ነው። ይህን መልካም አጋጣሚ አታሳልፉ። በመውደቅ ላይ ካለ ሥርዓት ጋር አብራችሁ አትውደቁ።
  2. በተመሳሳይ ሁኔታ በጠላት የስለላ መዋቅር ውስጥ የምትገኙ ወገኖቻችንም ራሳችሁን ከአገዛዙ በይፋ የምታገሉበት ወቅት ደርሷል። ከዚህ በላይ ጠላትን ማገልገል ከቀጠላችሁ ውድ ዋጋ ያስከፍላችኋል።
  3. ልቦና ያላችሁ የወያኔ፣ “አጋሬ” የሚላቸው ተለጣፊዎቹ ወይም ደግሞ ኢህአዴግ የሚባለው የይስሙላ ድርጅት አባል የሆናችሁ አሁኑኑ ከእነዚህ ድርጅቶች ለቃችሁ የሕዝብን ትግል በይፋ ተቀላቀሉ።
ይህን ዛሬ ካደረጋችሁ የበደላችሁትን ሕዝብ የመካስ እድል አላችሁ። የኢትዮጵያ ሕዝብን ምህረት ብቻ ሳይሆን የድሉን ፍሬ ተቋዳሾች ትሆናላችሁ። ይህን ዛሬ ማድረግ ካልቻላችሁ ግን ነገ ልታደርጉት አይቻላችሁም። ትግላችን በየእለቱ መልኩን እየቀየረ ነው። ስለሆነም እድላችሁን አታስመልጡ።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት እንዲነሳ ጥሪ ያደርጋል። በጠላት ካምፕ ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻችን እንዲቀላቀሉን ጥሪ ያደርጋል።
ግንቦት 7 መተማመኛችን ኅብረታች እና የገዛ ራሳችን ተነሳሽነት ነው ብሎ ያምናል። ሁላችንም ታጋዮች፣ ሁላችንም አርበኖች፣ ሁላችንም ዲፕሎማቶች እና ሁላችንም ጋዜጠኞች እንሁን።
አገራችንን ከዘረኛ አገዛዝ መንጋጋ መንጭቀን እናወጣታለን።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

No comments:

Post a Comment