Tuesday, October 23, 2012

ወያኔ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን መጨፍጨፉን ቀጥሏል


ከዚህ በታች የቀረበው ጽሁፍ ሶሻል ሚዲያዎችን በመጠቀም ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በማሰራጨት ላይ ያሉት ወቅታዊ ዘገባ ነው።
ሠላማዊ ትግላችን አሁንም አይቀለበስም!!
ትግላችን ወንድሞቻችንን በመግደል አይገታም!!!

በገርባ ከተገደሉ ወንድሞቻችን አስከሬን መካከል
በትናንትናው ዕለት በደቡብ ወሎ በደጋን እና ገርባ ከተማዎች የተፈፀመው ጥቃት ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው እና ለበርካታ ወራት ይዘን የዘለቅነው ፍፁም ሠላማዊውን የመብት ጥያቄ በምንም መልኩ ወደ ሌላ አቅጣጫ አይቀለብሰውም፡፡ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ በአገር አቀፍ ደረጃ በአንድነት ስሜት ህገ መንግስትዊ ስርዓቱን ባከበረ መልኩ ያነሳቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ያገኙ ዘንድ ለተቃውሞ አደባባይ ላይ በዋለባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ሂደቱ መልኩን ቀይሮ ኹከትን እንዲላበስ ብሎም ወደ ብጥብጥ እንዲያመራ ተከታታይ ሙከራዎች ተደርገውበት አልፏል፡፡ በእነዚህ ሙከራዎቻቸው ዛቻ፣ ድብደባ፣ እስራት እና የህይወት መስዋዕትነትን ከፍለናል፡፡ ይህ ሁሉ እየሆነ እያለ ያለ ምንም የአቋም መዋዠቅ ትገሉ ሠላማዊነቱን ጠብቆ እንዲዘልቅ ሙስሊሙ ኡማ ያላሰለሰ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ በመስከረም 27 ምርጫ እንኳን እነሱ ያለ ከልካይ በሕገ ወጥ ድርጊታቸው እንዳሻቸው ሲፈነጥዙ ሙስሊሙ ፍፁም ሠላማዊነቱን አስመስክሯል፡፡ በደቡብ ወሎ ደጋን እና ገርባ አካባቢዎች በትናንትናው ዕለት የተስተዋለውም የመንግስት ጸብ አጫሪነት የዚሁ የትንኮሳ እና ጸረ ሕዝብነት አንዱ ማሳያ ነው፡፡ክስተቱ የመላ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችን ሰላማዊ የመብት ማስከበር ትግል አቅጣጫ በማስቀየር ወደ ብጥብጥ እና ኹከት በመለወጥ ብሎም ሙስሊሞች በዚህ ሂደት ተደናግጠው ከመታሰር፣ ከመደብደብ ብሎም ከመሞት አርፎ መቀመጥን እንዲመርጡ ከያዙትም አቋም እንዲያፈገፍጉ የታለመ መሆኑን በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን፡፡
በአብዛኛው የአገራችን ክፍሎች ሙስሊሙ ከምርጫ ራሱን እንዳገለለ ሁሉ የደጋንና ገርባ አካባቢ ሙስሊሞችም በገቡት ቃል መሰረት በአካባቢያቸው ምርጫ አልተካሄደም፡፡ በዚህ የተበሳጩት የመንግስት አካላት ትናንት የተፈጠረው አደጋ እንዲከሰት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ከርመዋል፡፡ ዕለቱ መልካም አጋጣሚ እንሚሆንላቸው በመገመት እቅዳቸውን ለማሳካት ተንቀሳቀሱ፡፡ የመንግስት የደህንነት አካላት ወደ አካባቢው በማቅናት ከደሴ-ሰመራ መተላለፊያ የሆነውን መንገድ ሕዝቡ በድንጋይ እንዲያጥር ከፍተኛ የማነሳሳት ስራ አከናወኑ ፤ በመቀጠልም ሕዝቡን በቀጥታ ወደ ረብሻ እና ሁከት ማስገባት እንዲያስችላቸው ይህንን ወሬ በማራገብ ከ 10 የማያንሱ የአካባቢውን ታዋቂ ግለሰቦች ከህግ አግባብ ውጪ በሆነ አካሄድ ለማፈን ሙከራ አደረጉ፡፡ የአካባበቢው ህብረተሰብ ይህንን ህገወጥ አፈና ለመቃወም ባደረገው ሙከራና ተቃውሞ የተሰጠው ምላሽም ጥይት ሆኖ የለየለት ኹከት እንዲፈጠር ደህንነቶች ክፉኛ ተሯሯጡ፡፡
በዚህ ሁኔታም የዝሁርን ሶላት ለማከናወን ወደ መስጊድ የገባውን ሰላማዊውን ሕዝብ ከመሬት ተነስተው መደብደብ፣ ማሰር እና በጥይት መቁላት ጀመሩ፡፡ ይሁንና የአካባቢው ነዋሪ


በገርባ ከተገደሉ ወንድሞቻችን አስከሬን መካከል
በከፍተኛ ብስለት ሁኔታው የባሰ እልቂት እንዳያስከትል የተቻለውን ሁሉ ለማድረግ ተረባረበ፡፡ ይህ የተጠና ሴራ በአርሲ አሳሳ ከተፈፀመው ጋር ተመሳሳይ መሆኑ መንግስት ያዘለውን ተንኮል ይበልጥ እንድንረዳ፣ ወደፊትም ከመሰል ድርጊቱ ሊቆጠብ ዝግጁ ያለመሆኑን እንድንገነዘብ ያደርገናል፡፡ ሰላማዊ እና ንፁኃን ዜጎችን በመደብደብ፣ በማቁሰል እና በጭካኔ በመግደል ‹‹የቆሰሉትና የተገደሉት አክራሪዎች ናቸው›› ይለናል፡፡ በገርባ እና በደጋን የሆነውም የዚህ ትክክለኛ መገለጫ ነው፡፡ በአካባቢው መንግስት ራሱ ሆን ብሎ የፈጠረው ትንኮሳና ያነሳሳው ረብሻ የዜጎችን ጉዳት አስከትሏል- የንፁኃንን ሕይወት ቀጥፏል፡፡ ይህም አልበቃ ብሎ የተገደሉት ንፁኃን ዜጎች አክራሪዎች ናቸው ይለናል፡፡ ኢትዮጵያችን ውስጥ የመብት ጥያቄ በማንሳት ሠላማዊ የመብት ትግል እያካሄደ የሚገኝ ዜጋ በሙሉ አክራሪና አሸባሪ የሚል ተቀፅላ ይወጣለታል፡፡
ይህ ፅሁፍ እስከተጠናከረበት ሰዓት ድረስ ከአስር በላይ ወገኖች ቆስለው በደሴና በአካባቢው በሚገኙ የሕክምና ማዕከላት እርዳታ እያገኙ ሲሆን አራት የሚሆኑቱ ደግሞ ሸሂድ መሆናቸውን ድምፃችን ይሰማ አረጋግጣለች፡፡ መንግስት ‹‹አንድ ፖሊስ ተገድሏል›› ብሎ ቢገልጽም እስከአሁን ለዚህ ማረጋገጫ ማግኘት አልቻልንም፡፡ ከዚህ ቀደም በአሳሳ ተከስቶ በነበረው ኹከት መንግስት ‹‹ፖሊስ ተገድሏል›› ብሎ መግለጫ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም በመጨረሻ ሐሰት ሆኖ መገኘቱ ይታወሳል፡፡ መንግስት ዛሬም ተመሳሳይ ድራማ እየፈጸመ እንደሆነና የአሁኑም ክስተት ሕዝቡንም ሰላም አልባ አድርጎ ለመሳል እያደረገ ያለው ጥረት አንድ አካል እንደሆነ እናስባለን፡፡ ይህ አገርንና ህዝብን ከሚመራ መንግስት ፈጽሞ የማይጠበቅ አሳፋሪ ተግባር በመሆኑ ሊወገዝ ይገባዋል፡፡ ይህ ሕገ ወጥና ኃላፊነት የጎደለው ተግባር የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችን ሰላማዊ መብት የማስከበር ትግል አቅጣጫ ወደ ብጥብጥ እና ኹከት በመለወጥ ሙስሊሞች በዚህ ተደናግጠው ከያዙት አቋም እንዲያፈገፍጉ እና ከመታሰር፣ ከመደብደብ ብሎም ከመሞት አርፎ መቀመጥን እንዲመርጡ ለማስፈራራት የታለመ፣ ጭንቀት የወለደው ርካሽ ተግባር ከመሆን የዘለለ አይደለም፡፡
ሁኔታዎች ሳይፈለጉ በግድ መልካቸውን እንዲለውጡ እየተደረገበት ባለበት በዚህ ሰዓት ለመንግስት እና ለመላ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ የሚከተለውን እውነታ በድጋሜ ለማስታወስ እንወዳለን፡፡ መላ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ላለፉት አስር ወራት ይዘውት የዘለቁት የመብታችን ይከበር ጥያቄ በይዘቱ እጅግ ቀላል፣ ግልፅና ፍፁም ሃይማኖታዊ፣ እንዲሁም ከተለጠፈበት የሙስሊም ዜጎችን የአኗኗር ባሕል ግምት ውስጥ ያላስገባ አጓጉል ታፔላ የራቀ መሆኑን ኢትዮጵያዊያን እንዲገነዘቡልን እንፈልጋለን፡፡ መንግስት ጥያቄዎቹን ከጥያቄው ባለቤት ጋር በግልፅ መድረክ በመገኘት እና መፍትሔ በመፈለግ አደባባይ የወጣውን እና ያኮረፈውን የአገሪቱን ግማሽ አካል ህዝብ ቤቱ እንዲመለስ ከማድረግ ይልቅ ህጋዊ ኮሚቴዎቻችንን ማሰር፣ ታዋቂ ዳዒዎቻችንን እና ግለሰቦችን ማሰር እና ክፋት የተሞላባቸውን ከኃላፊነት የራቁ ተግባራት መፈፀምን መርጦ እነሆ ይህንኑ እየተገበረ ይገኛል፡፡
ሙስሊሙ ሕዝብ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ይሟሉና ሃይማኖታዊ፣ ፍትሐዊ፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ይካሄድ›› ቢልም፣ ይህ ባለመሆኑም የተነሳ ሕዝቡ ተአቅቦ ቢያደርግም የመንግስት ካድሬዎች በየግለሰቡ ቤት ሁሉ በመግባትና በማስፈራራት ያልተሳካ ጥረታቸውን አድርገው በሚዲያቸው ‹‹ምርጫ አድርገናል›› ብለውናል፡፡ ህገ ወጥ ድርጊታቸው እንዲህ እንዲህ እያለ በሕጋዊነት ሽፋን ቢገፋም የፈጠረው አዲስ ነገር ግን የለም፡፡ ይልቁንም የሙስሊሙን ሕዝብ ንቃት እና ብስለት ይበልጥ እያሳደገው መሄዱ እሙን ሆኗል፣ በሰላማዊ የመብት ትግል ሂደቱም እንዲገፋበት ሆኗል፡፡ ሆኖም ይህ ሃይማኖት ነው:: ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች እንደመሆናችን መጠን ያገራችንን እና የሕዝቦቿን ሰላም በመጠበቅ ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱ በሚፈቅድልን መርሕ መሠረት ሠላማዊ ትግሉ የሚጠይቀውን ሁሉ በመክፈል እስከመጨረሻው የስኬት ማማ ለመድረስ ዳገቱን በጥፍራችንም ቢሆን እየቧጠጥን እልህ አስጨራሹን ጉዟችንን እንቀጥላለን፡፡
በዚህ ከፍተኛ ፅናትን በሚጠይቅ ሂደት ፍፁም ሰላማዊ ሂደትን ብቻ በመከተል ለመታገል ቁርጠኛነታችንን ስንገልፅ መሠል አስደንጋጭ መሰናክሎችን ማለፍ ግድ እንደሚለን ትምህርት እየወሰድን ታሪክ መስራታችንን እንደጀመርን እንጨርሳለን – ኢንሻአላህ! የአሚሮቻችንን መታሰር የሚያክል የከፋ በደል ተፈፅሞብን እያለ አዲስ አበባን በሚያክል ሰፊ እና ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ባለበት ከተማ ምን ሊፈጠር ይችል እንደነበር መገመት ከባድ የነበረ ባይሆንም ኮሽታ ሳይፈጠር ሰላማዊ ትግላችን ቀጥሏል፡፡ ከዚያም በኋላ ቢሆን አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሰላማዊ ትግላችንን እና ሰላማችንን የሚያደፈርሱ የመንግስት ትንኮሳዎችን በተደጋጋሚ አስተናግደን አልፈናል፡፡ እንደ መንግስት እና የደህንነት አካላት ምኞት ቢሆንማ ኖሮ ሚሊዮኖች ለተቃውሞ አደባባይ በወጡበት አጋጣሚ መቶዎችንነና ሺዎችን በጨረሱ ነበር፡፡ ሆኖም የሙስሊሙ ሕዝብ በሣል እና ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድ ቀዳዳዎችን ሁሉ ያጠበበ መሆኑ ረፍት ነስቷቸዋል፡፡ እስካሁን ያስመዘገብናቸው ድሎች አያሌ ከመሆናቸውም በላይ በሰላማዊነታችን ብቻ ላይ ፀንተን ወደፊት እንድንቀጥል ያገኘነውን ትምህርት ተጠቅመን ታሪክ መስራታችንን እንደጀመርን እንድንጨርስ ግድ ይሉናል-ኢንሻ አላህ፡፡ ሂደታችን ረጅምም በመሆኑና ስር ነቀል ለውጥ የሚጠይቅ በመሆኑ አቋራጭ ኹከት ቀስቃሽ መንገዶች ተመራጭ መፍትሄ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ሕዝቡም ይህንን እውነታ ተረድቶ ላለፉት አስር ወራት የመንግስት የደህነነትና የፀጥታ አካላት ሲያደርጉ የነበሩትን ርካሽ ተግባር የማስቆም ስራዎቻችንንም አጠናክሮ መቀጠል ይገባል፡፡ ይህ ከፍተኛ ትዕግስትን የሚጠይቅ መሆኑ በበደል ላይ እያለን ከመሆኑ ጋር በጣም ከባድ ቢሆንም ያስመዘገብነውን ድል ጠብቀን የተሻለ ተጨማሪ ድል ባለቤት ለመሆን ይህንን በብለሃት ማለፍ ይጠበቅብናል፡፡
በዚህ የታሪክ አጋጣሚ ፍፁም ሰላማዊ ተቃውሞ በማሰማት መብታቸውን ለማስከበር በሚያደርጉት ትግል መስዋዕት የሆኑትን የእምነት ወንድሞቻችንን አላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ በሸሂድነት እንዲመዘግባቸው ዱዓችን ነው፤ አላህ ይቀበለን
ድል ለኢትዮጵያ ሙስሊም!
አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment