Tuesday, April 17, 2012

ጠቅላይ-ሚኒስተሩ-ስለመምህራኑን-ማረሪያ ሰጡ!


ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ዛሬ ማብራሪያ ሰጥተው ነበር።
ብቸኛው የተቀናቃኝ ፓርቲ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በርካታ ጥያቄዎችን አንስተውላቸው ነበር።
ከጥያቄዎቹ መካከልም ስለ ፖለቲካ ምህዳሩ፤
ፓርቲያቸው በይፋ ስብሰባ ባደረገበት ወቅት ኢቲቪ የቀረፀውን ዋቢ በማድረግ “በህቡዕ በማሴር” ተብለው አባላቶቻችን እና ደጋፊዎቻችን ተከሰውበት እስር ቤት መግባታቸውን፣
ስብሰባ ለማድረግ አዳራሽ አከራዮች “ለሰርግ ካልሆነ በስተቀረ አታከራዩ ተብለናል” በሚል  ስለመከልከላቸው።
እንዲሁም በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ደግሞ፤
ከደቡብ ክልል ስለተፈናቀሉ ዜጎች “የክልሉ ፕረዘዳንት “አንድም ሰው አልተፈናቀለም” ብለው ተናግረዋል። በአይናችን ያየናቸው እርስዎ ፅ/ቤት አቤት ለማለት መጥተው ፀሀይ ተንቃቅተው በኋላም በመኪና ተጭነው የተወሰዱ ዜጎች “አንድም ሰው” አይደሉም ወይ?” ያሏቸው ሲሆን፤
ከደምወዝ ጋር በተያያዘ “መምህራን ተቃውሞ ሲያሰሙ ገሚሱ ከስራ ታግዷል ገሚሱ ማስፈራሪያ ደርሶበታል። እንደዚህ አይነት “ሆድ የባሰው” መምህር ይዘን ስለ ትምህርት ጥራት ማውራት እንችላለን ወይ?”
የሚሉ ጥያቄዎችን ጠይቀዋለው።፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩም አብዛኛዎቹን የአቶ ግርማ ሰይፉን ጥያቄዎች በመላ በመላ አልፈዋቸዋል። (የእድሜ እና የስልጣን እኩያዬ ቢሆኑ ኖሮ አጭበርብረው አልፈዋቸዋል እል ነበር)
መምህራኑን በሚመለከት በሰጡት ምላሽ ግን “የማስተማር ስራው በተቋረጠ ወቅት ከወላጆች እና ከተማሪዎች ጋር ውይይት አድርገን ነበር። “በዛን ግዜም መምህራኑ ቀድሞውንም እንዲባረሩልን አቤት ስንል ነበር” የሚል አስተያየት ከወላጆች እና ተማሪዎች አግኝተናል።” ብለዋል። በዚሀም አላበቁም “እነዚህ ከአምስት መቶ እስከ አንድ ሺህ የሚደርሱት መምህራን በመምህርነት አልሳካ ሲላቸው ሌላ አማራጭ ለመሞከር ያሰቡ ናቸው” ሲሉ አብጠልጥለዋቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ግርማ ሰይፉን እንዲሁም መመህራኑን “ጭማሪው የደሞዝ ጭማሪ ሳይሆን የእርከን ማሻሻያ መሆኑ ስላልገባችሁ ነው” ሲሉም ተችተዋል።
በዚህም አንዳንድ አስተያየታቸውን የሰጡ መምህራን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ጠብቀን ማረሪያ አግኝተናል ብለዋል።
በነገራችን ላይ (አዲስ ነገር ጋዜጣ ናፈቀችኝ መስፍኔ በሚፅፋቸው ፅሁፎች ጣልቃ አነስ ያለች “በነገራችን ላይ” የምትል የጨዋታ “ቦነስ” ነበረችው። ሰላም መስፍኔ! ሰላም አዲስ ነገሮች)
ስቀጥልም በነገራችን ላይ
የመምህራኑ ጥያቄ ባለፉት ግዚያት በተደጋጋሚ እንደገፁልን የኢቲቪ የተጋነነ ዘገባ እንጂ የደሞዝ ማሻሻያው አነሰ አላነሰ አይደለም። ኢቲቪ ሆዬ “መምህራኑ ህይወታቸውን የሚቀይር ገንዘብ ተጨመረላቸው” ብሎ በዘገበ በነጋታው አካራዮች አከርካሪ የሚሰብር ጭማሪ አደረጉብን እናም ዘገባው ይስተካከል ነው ያሉት። ካላመናችሁኝ ድጋሚ አንዱን የአዲሳባ ወይም የአማራ ክልል መምህር ጠይቁት።
በመጨረሻም 1
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው የፓርላማ ስብሰባቸው በማሳቁ በኩል ብዙም አልተሳካላቸውም። በዚህም ሳቅ ጨዋታ ጠብቀው የሄዱ የፓርላማ አባላት እጅጉን ተከፍተዋል አሉ። እንደውም አንዳንዶች “ካላሳቁ ይልቀቁ” ሲሉ አጉረምርመዋል ሲል ታማኝ ያልሆነ ምንጭ ሹክ ብሎኛል። እዝችው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ሶማሊያ ሲናገሩ “እኛ ሶማሊያ  እንደገባን የሶማሊያ ህዝብ ጫት መቃም ጀምሯል።” በማለት በኩራት ሲናገሩ የሰማ አንድ ወዳጃችን “እንዴት ነው ነገሩ ለማቃቃም ነበር እንዴ የሄዳችሁት?” ሲል የማይመለስ ጥያቄ ጠይቋል።
በመጨረሻም 2
“የግድብ ስራው ተቋረጠ” በሚል አጭር መረጃ አድርሻችሁ ነበር። እኔማ “እስቲ አንዳንዴ እንኳ ጥሩ ወሬ አውራ መንግስታችንን አመስግንልን” ለሚሉ ወዳጆች ጥሩ አጋጣሚ አገኘሁ ብዬ ተደስቼ ነበር። ምን ዋጋ አለው ዌብ ሳይቶቹ ለሶስት ቀናት ተከፍተው የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት ደግመው ተከርችመዋል። አሉ! በቀደመው ጨዋታዬ ላይ
“…ስለ ኢትዮጵያ የሚያወሩ ድረ ገፆች እንደ ምንጬ አባባል “ፏ” ብለው ይታዩ ነበር። እንዴት ነው ነገሩ መንግስት ተቀየረ… ወይስ ዌብሳይቶችን ሲገድብ የነበረው ሰውዬ ደህና አይደለም?    እነዚህን ጥያቄዎች እርሱ ባለቤቱ ይመልሳቸው።” ብዬ ነበር?
አዎ መልሱን እርሱ ባለቤቱ መልሶልናል። ለሶስት ቀናት ድረ ገፆቹ “ፏ” ብለው የመታየታቸው ምስጢር ገዳቢው ከአመት በዓል ጋር በተያያዘ ጥቂት ጉዳት ደርሶበት ስራውን በአግባቡ ባለመስራቱ ነበር። (ጉዳት የሚለውን ሞቅታ ብሎ መተርጎም አግባብ አይደለም) እናም እንደምንጠረጥረው ልክ  በአሁኑ ሰዓት በ”ኢንሳ” መስሪያቤት  “የዌብሳይት ግደባ እና ቁለፋ ዋና የስራ ሂደት ባለቤት” የሆነው ግለሰብ በግምገማ ቁም ስቅሉን እያየ እንደሚሆን ይገመታል።
source :
http://abetokichaw.wordpress.com/2012/04/17/ጠቅላይ-ሚኒስተሩ-ስለመምህራኑን-ማብራሪ/

No comments:

Post a Comment